ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ከጤና ባለሙያዎች ጋር ያደረጉት ውይይት
ሰኞ፣ ሰኔ 16 2017ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከጤና ባለሙያዎች ጋር ያደረጉት ውይይት
የጤና ባለመያዎች ያነሱት የደሞዝ ጭማሪ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ ተገቢ ቢሆንም የተጠየቀበት መንገድ ትክክል እንዳልሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐበይ አሕመድ ተናግሩ።
ጥያቄው በሙያቸዉ በቅንነት በሚያገለግሉ ነገር ግን ኑሮ በከበዳቸው፣ "የፖለቲካ ኪሳራ በገጠማቸው እና ሀኪም መሳይ ጋዎን ለባሽ" ባሏቸው ሰዎች ተጠልፎ መልኩን መቀየሩንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
ይህንኑ የሕክምና ባለሙያዎችን ጥያቄ ደግፈሃል በሚል በሰቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን መታገዱን የገለፀው የኢትዮጵያ ሕክምና ባለሙያዎች ማሕበር ወይይቱን ተከትሎ "መልካም ነገሮች ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል" ሲል አወንታዊ ምላሾች እንደሚኖሩ ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከመላዉ ኢትዮጵያ የተዉጣጡ ከተባሉ የጤና ባለመያዎች ጋር ሰሞኑን ዉይይት አድርገዋል። ባለሙያዎቹ የሕክምና ተቋማት ደረጃ ይሻሻል፣ እድሳት ይደረግላቸው፣ ፍትሓዊ የመድኃኒትና የግብዐት ክፍፍል ይኑር፣ የጤና ባለሙያዉ ደሞዝ የትምህርት ዝግጅቱን፣ የሥራውን ዋጋ የሚመጥን ይሁን፣ ክፍያችን ሊያኖረን አልቻለም የሚሉ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።የጤና ባለሞያዎች የሥራ ማቆም አድማ፤ የውጭ ዜጎችን የመሬት ባለቤት የሚያደርገው ረቂቅ ሕግ፤ የተጠናከረው የጋዛ ጦርነት
በተጨማሪም የተጋላጭነት ክፍያ፣ የትራንስፖርት እና የመኖሪያ ቤት ችግር ለዘርፉ ባለሙያ ፈተና ስለመሆኑ፣ ስለሆነም መሬትና የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ብድር እንዲመቻችላቸው፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያ የባለሙያውን ድካም የሚመጥን እንዲሆን፣ የጤና ተቋማት በባለሙያዎች እንዲመሩ ጠይቀዋል።
መንግሥት ለጤና ዘርፍ ትኩረት ይስጥ የሚለዉ ጥያቄ ተገቢ መሆኑን በማብራራት ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የጤና ባለሙያዎች ወደ ሥራ ማቆም እርምጃ የገቡበትን ኹኔታና የጥያቄያቸውን አቀራረብ በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል።እንወያይ፤ የኢትዮጵያ ህክምና ባለሞያዎች ጥያቄ እንዴት መልስ ያግኝ?
"ጥያቄዉ ትክክል ቢሆንም የምንጠይቅበት መንገድ ትክክል ካልሆነ ይበላሻል። ኢትዮጵያ ውስጥ ሀኪሞች ለምን የደሞዝ ጥያቄ አነሱ ብሎ የሚያስብ ሰው አለ ብየ አልገምትም። ግን ጥያቄው ለምንድን ነው እንደዚህ እንደ ጦርነት የሆነው የሚለውን አስቡበት" በማለት ጥያቄው በሌሎች አካላትና ፖለቲከኞች ጭምር መጠለፉን አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመሩት የጤና ባለሙያዎች ዉይይት ላይ አለመጋበዛቸውን የተናገሩት የትግራይ ጤና ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍስሃ አሸብር ደሞዝ ላይ ድርድር ሊኖር ይገባ ነበር ብለዋል።
"ቀጣይ በሚደረገው ውይይት ላይ የጤና ባለሙያዎች ማህበር አመራች፣ በተለይ ዋናው ትግሉ ላይ የነበሩ" ይሳተፋሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ማሕበር የባለሙያዎችን እንቅስቃሴ ደግፈሃል በሚል እገዳ እንደተጣለበት የማሕበሩ ዋና ፀሐፊ ድሪባ ቶሎሳ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። በዚህ ወቅት ምንም አይነት መግለጫ ማውጣት እንደማይችሉ እንደተነገራቸው ሆኖም በቅርቡ ጠቅላላ ጉባኤ በማድረግ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርጉም ገልፀዋል። ከዚህ አስቀድሞ ከጤና ሚኒስቴር እና ከአዲስ አበባ ከተማ አመራሮች ጋር ውይይት መደረጉን በመግለጽ በጎ ምላሽ ይኖራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልፀዋል።የቀጠለው የጤና ባለሞያዎች ጥያቄና የጤና ሚኒስቴር ምላሽ
ለጤናው ዘርፍ የሚመደብ በጀት ማደጉንና ለጤና ሚኒስትር 130 ቢሊዮን ብር ፈሰስ እንደሚደረግ በዉይይቱ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይህም ሆኖ ግን በቂ ነው የሚባል እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።
የመንግሥት 22 ሺህ የጤና ተቋማት እና ቀጥሮ የሚያሠራቸው 520 ሺህ የጤና ባለሙያዎች እንዳሉም ተናግረዋል። ባለሙያው የጤና መድህን ተጠቃሚ እንዲሆን ይደረጋል ሲሉም ገልፀዋል። "አሁን ሁላችሁም የአገልግሎት ክፍያ ያንሳል ብላችኋል። ማህበረሰቡ ጋር ደግሞ ብንሄድ ውድ ነዉ ነጻ ይሁን ብላችኋል። ከየት ነው ደሞዝ የሚጨመረው ግብር ካልተሰበሰበ?"
የኢትዮጵያን የጤና ዘርፍ ከጎረቤት ሀገራት በንጽጽር ማቅረብ እንደማይገባ ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የጤና ባለማዎች ያነሱትን ቤትን የተመለከተ ጥያቄ ከክልሎች ጋር እየተወያዩበት መሆኑን፣ ሆኖም ሁሉም ባለሙያ በአንድ ጊዜ የቤት ባለቤት ሊሆን እንደማይችል እና በሂደት እየተፈታ የሚሄድ መሆኑን ገልፀዋል።
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
ዮሃንስ ገብረግዚአብሔር