ጀርመን በዉጭ የሚገኙ ዜጎችዋን እየመለሰች ነዉ
ረቡዕ፣ መጋቢት 9 2012በዓለም በተዛመተዉ ኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ወደ ሃገራቸዉ መመለስ ያልቻሉ ወደ 100 ሺህ የሚሆኑ ጀርመናዉያን ቱሪስቶችን መንግሥት ወደ ሃገራቸዉ መመለስ መጀመሩ ተመለከተ። የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሃይኮ ማስ ለዶቼ ቬለ በሰጦት ቃለ-ምልልስ እንደተናገሩት ከተጓዙበት ሃገር መምጣት ያልቻሉትን ዜጎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በጀርመኑ ሉፍታንዛ አየር መንገድ እንመልሳለን። ለዚህም ወጪ የሚሆን መንግሥት እስከ 50 ሚሊዮን ኦይሮ መድቦአል። ትናንት ሁለት የሉፍታንዛ አየር መንገድ አዉሮፕላኖች በፊሊፒን የሚገኙትን ጀርመናዉያን ለመመለስ ወደ መዲና ማኒላ ማቅናቱም ተመልክቶአል።
«ባለፉት ቀናት በደረሰን መረጃ እንዳደረጋገጥነዉ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ጀርመናዉያን ቱሪስቶች በተለያዩ ሃገራት ይገኛሉ። እንደሚታወቀዉ በተለያዩ የዓለም ሃገራት ሆቴሎች እየተዘጉ ነዉ ፤ የበረራ መስመሮችም እየተቋረጡ ነዉ። በዚህም ምክንያት በዉጭ ሃገራት የሚገኙ ጀርመናዉያንን በሉፍታንዛ አየር መንገድ ወደ ሃገራቸዉ ለመመለስ ወስነናል። ለምሳሌ በግብጽ ብቻ 35 ሺህ ጀርመናዉያን ቱሪስቶች እንዳሉ አረጋግጠናል። ከነዚህ ገሚሱ መመለስ የሚፈልጉ ናቸዉ፤ ገሚሱ ግን ይህ እድል መጠቀም አይፈልጉም። በሞሮኮም ቢሆን ከ 4 እስከ 5 ሺህ የሚሆኑ ቱሪስቶች ይገኛሉ። ትናንት እንነዚህን ዜጎች መመለስ ጀምረናል። እንደ አርጄንቲና፤ፊሊፒን፤ ማልዲቭስ የሚገኙ በርካታ ጀርመናዉያን ወደ ሃገራቸዉ መመለስ ይፈልጋሉ ። በዚህም ምክንያት ለዜጎቻችን በርግጠኝነት ወደ ሃገራቸዉ መመለስ እንዲችሉ አስፈላጉ ሆኖ አግኝተነዋል። »
የጀርመኑ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃይኮ ማስ ወደ 100 ሺህ ዜጎች ያልዋቸዉ በትዳር ፤ እና በመሳሰሉ ጉዳዮች የጀርመናዉያን ቤተሰቦች የሆኑትን ሁሉ እንደሚጨምር ተናግረዋል። በሌላ በኩል የአዉሮጳ ኅብረት ዛሬ ይፋ እንዳደረገዉ በተለያዩ የአለም ሃገራት የሚገኙ እና ወደ የሃገሮቻቸዉ መመለስ የሚፈልጉ ወደ 80, 000 የሚሆኑ የአዉሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት ዜጎች ይገኛሉ።
አዜብ ታደሰ
ታምራት ዲንሳ