ደቡብ ሱዳን ወደ የርስ በርስ ጦርነት ዳግም እየተንሸራተተች ይሆን?
ሰኞ፣ መጋቢት 1 2017በአፐር ናይል ግዛት እየጨመረ የመጣው ግጭት፣ በጁባ የተባባሰው ውጥረት እና ፖለቲካዊ ሴራ ከሰባት ዓመታት በፊት የተፈረመውን የደቡብ ሱዳን የሰላም ሥምምነት ሊያኮላሽ እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት የደቡብ ሱዳን የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስጠንቅቋል። የኮሚሽኑ ሊቀ-መንበር ያስሚን ሶካ ብርቱ ማስጠንቀቂያ የሰጡት ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ሚያርዲት የሚመሩት መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና ከሪየክ ማቻር ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ታጣቂ ቡድኖች ደም አፋሳሽ ግጭት ውስጥ ከገቡ በኋላ ነው።
የቀውሱ መነሾ ከኢትዮጵያ ድንበር በ30 ኪሎ ሜትር ገደማ በምትርቀው ናስር የተባለች ከተማ የደቡብ ሱዳን ጦር ሠፈር ላይ የተፈጸመ ጥቃት ነው። ከተማዋ የምትገኝበት ግሬተር አፐር ናይል ግዛት ከኢትዮጵያው ጋምቤላ ክልል ይዋሰናል።
በተባበሩት መንግሥታት የደቡብ ሱዳን የብአዊ መብቶች ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ያስሚን ሶካ በናስር የተከሰተው ወታደራዊ ግጭት “እስከ የጦር ወንጀል” ሊደርስ እንደሚችል ገልጸዋል። በቦታው የተባበሩት መንግሥታት ባልደረቦች ጭምር ተገድለዋል። ያስሚን ሶካ ደቡብ ሱዳን የምትገኝበት ሁኔታ ለዓመታት በተደረገ ጥረት የተገኘውን መሻሻል የሚፈቅ እንደሆነ ሥጋት አላቸው።
“ነጩ ጦር” ማን ነው?
በናስር በሚገኝ የደቡብ ሱዳን የጦር ሠፈር ላይ ባለፈው ሣምንት ጥቃት የፈጸመው ዋይት አርሚ ተብሎ የሚጠራ የኑዌር ጎሳ ታጣቂ ቡድን ነው። በአብዛኛው ወጣቶችን በአባልነት ያቀፈው ታጣቂ ቡድን የደቡብ ሱዳን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንት ሪየክ ማቻር ከሚመሩት ተቃዋሚ ጋር በጎርጎሮሳዊው ከ1990ዎቹ ጀምሮ ትሥሥር እንዳለው በክራይስስ ግሩፕ የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ተንታኝ የሆኑት ዳንኤል አኬች ይናገራሉ።
“ማቻር ራሳቸው ዋይት አርሚን ባይመሠርቱትም ፍላጎቶቻቸው የተስማሙት በደቡብ ነጻ አውጪ ንቅናቄ ውስጥ ክፍፍል በተፈጠረበት ወቅት ነበር” የሚሉት ዳንኤል አኬች በ2013 ግጭት ሲቀሰቀስ ታጣቂ ቡድኑን ከመደበኛ ኃይላቸው ጎን በማሰለፍ ማቻር እንደተጠቀሙበት አስረድተዋል። በ218 የሰላም ሥምምነት ሲፈረም ማቻር እና ተቃዋሚዎች በጁባ መንግሥትን ሲቀላቀሉ የዋይት አርሚ አባላት ግን ወደ መንደሮቻቸው ተመለሱ።
ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ሚያርዲት እና ምክትላቸው ሪየክ ማቻር በጎርጎሮሳዊው 2018 የተፈራረሙት የሰላም ሥምምነት ለአምስት ዓመታት የዘለቀ የርስ በርስ ጦርነት አቁሟል። በምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) አመቻችነት የተፈረመው የሰላም ሥምምነት ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች ታጣቂዎቻቸውን አዋሕደው አንድ ብሔራዊ ጦር እንዲመሠርቱ፣ አዲስ ሕገ-መንግሥት እንዲጻፍ እና በደቡብ ሱዳን ምርጫ እንዲካሔድ ያቀደ ነበር። ይሁንና በሥምምነቱ የተካተቱ ጉዳዮች አንዳቸውም ተግባራዊ ሳይሆኑ በአካባቢያዊ እና የጎሳ ታጣቂ ቡድኖች ግጭት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሲታዩ ቆይተዋል።
ቀድሞም የሻከረውን የኪር እና የማቻር ግንኙነት ወደሌላ ውጥረት የመራው በአፐር ናይል ግዛት በምትገኘው ናስር ካውንቲ ግጭት ሲደጋገም ነበር። በግዛቲቱ የሚገኙ ታጣቂዎችን የመንግሥት ወታደሮች በግዳጅ ትጥቅ ሊያስፈቱ ነው የሚል ጉምጉምታ ሥጋት ፈጥሮ እንደነበር የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ ሒውማን ራይትስ ዎች አስታውቋል። በተለይ ከየካቲት አጋማሽ ጀምሮ በታጣቂዎቹ እና በደቡብ ሱዳን ጦር መካከል ተደጋጋሚ ግጭቶች ተከስተዋል።
ውጥረት ባየለበት ወቅት ፕሬዝደንት ሪየክ ማቻር ተግባራዊ ያደረጓቸው እርምጃዎች ለቀውስ መባባስ አስተዋጽዖ እንዳላቸው በክራይስስ ግሩፕ የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ተንታኝ የሆኑት ዳንኤል አኬች ይናገራሉ። ካለፈው ዓመት የካቲት ጀምሮ ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር የጸጥታ መዋቅሩን መልሰው እያደራጁ እንደነበር የገለጹት ዳንኤል አኬች “በየካቲት ቁልፍ የመንግሥት ባለሥልጣናትን አባረሩ። የተወሰኑት ባለሥልጣናት መባረር የሱዳን ሕዝቦች ነጻ አውጪ ንቅናቄ በተቃውሞ (SPLM-IO) መሪ በሆኑት ሪየክ ማቻር የ2018 የተፈረመው የሰላም ሥምምነት እንደጣሰ ተቆጥሯል” ሲሉ አስረድተዋል።
ኪር የጥምር መንግሥቱ አካል የሆኑት ማቻርን ሳያማክሩ የወሰዷቸው ለውጦች በምዕራብ ባሕር ኢል ጋዛል ግጭት ቀስቅሷል። ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ ቦታዎች የሠፈሩ የጦር አባላትን ለመቀያየር ያሳለፉት ውሳኔ ተቀባይነት አላገኘም። በአንድ የጦር ሠፈር የሚመደቡ ወታደሮችን ወደ ሌላ ማዛወር በጦር ሠራዊቱ ውስጥ የተለመደ አሠራር እንደሆነ የተናገሩት ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር “ፖለቲካዊ” ሆኖ ግጭት ለመቀስቀስ መብቃቱን ተናግረዋል።
በተለይ የዛሬ ሣምንት ማክሰኞ ዕለት ሪየክ ማቻ ከሚመሩት ተቃዋሚ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የሚነገርላቸው የኑዌር ታጣቂዎች የፈጸሙት ጥቃት ቀውሱን አባብሶታል።
“ናስር ወታደሮች ከሚቀያየሩባቸው ቦታዎች አንዷ ሆና ተመርጣ ነበር” የሚሉት በክራይሲስ ግሩፕ የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ተንታኝ “ወደ ቦታው የተላኩት ቀድሞ ከሱዳን ሕዝቦች ነጻ አውጪ ንቅናቄ በተቃውሞ ጋር ግንኙነት የነበራቸው እና ከ2013 እስከ 2018 በተካሔደው የደቡብ ሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ወቅት አሰላለፋቸውን በመቀየር ከመንግሥት ጎን የተሰለፉ አዛዦች እና ጄኔራሎች ናቸው” ሲሉ ይናገራሉ። ይህ ደግሞ የአካባቢው ማኅበረሰብ አባላት በጥርጣሬ የሚመለከቱት ነው። “በናስር እና በኡላንግ የሚገኙ የኑዌር ማኅበረሰብ አባላት ይዋጉዋቸው የነበሩ የቀድሞ ጄኔራሎች ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው ሊመጡ መሆኑን ሲሰሙ ተቃውሞ በረታ” ሲሉ ዳንኤል አኬች ያስረዳሉ።
ከጥቃቱ በኋላ የሳልቫ ኪር ሚያርዲት መንግሥት ለማቻር ቅርበት ያላቸው በርካታ ባለሥልጣናትን በቁጥጥር ሥር አውሏል። በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል ለማቻር ታማኝ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የደቡብ ሱዳን ጦር ሠራዊት ምክትል አዛዥ ጄኔራል ጋብርዬል ዱፕ ይገኙበታል። የማቻር አጋር እና የየፔትሮሊየም ሚኒስትሩ ፖት ካንግ ቾል ከነጠባቂዎቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው በቁጥጥር ሥር ውለዋል። የሰላም ግንባታ ሚኒስትሩ ስቴፈን ፓር ኮል ባለፈው ሐሙስ ከቢሯቸው በወታደሮች ከተወሰዱ በኋላ አርብ ዕለት ተለቀዋል። በኬንያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ሞኒካ አቾል አቤል በአንጻሩ ተባረዋል።
የሱዳን ሕዝቦች ነጻ አውጪ ንቅናቄ በተቃውሞ (SPLM-IO) ቃል አቀባይ ፓል ማይ ዴንግ የፕሬዝደንት ኪር እርምጃዎች “በሰላም ሥምምነት ፈራሚዎቹ መካከል የነበረውን እምነት ሸርሽሯል” ሲሉ ከሰዋል። የደቡብ ሱዳን የውኃ ሐብት ሚኒስትር ሆነው የሚያገለግሉት ፓል ማይ ዴንግ “የኪር እርምጃዎች አጠቃላይ ሥምምነቱን አደጋ ላይ ጥለዋል” በማለት አስጠንቅቀዋል።
በአፐር ናይል ግዛት በሚገኘው የጦር ሠፈር ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ በቦታው የሚገኙ ወታደሮችን ለማውጣት የተደረገው ጥረት በርካታ ፈተናዎች ገጥመውታል። ኪር እና ማቻር በጦር ሠፈሩ ውስጥ የቀሩ ወታደሮች ስለሚወጡበት ሁኔታ ቢነጋገሩም ጥረቱ ስኬታማ አልነበረም። የደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ጦር አባላትን ባለፈው ሣምንት በሁለት ሔሊኮፕተሮች ለማውጣት ሲሞከር አንድ የጦር ጄኔራል እና በርካታ ወታደሮች መገደላቸውን በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮ (UNMISS) አስታውቋል።
የጦር ጄኔራሉን እና የወታደሮቹን ሞት ለሀገራቸው ሕዝብ ያረዱት ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ለተፈጠረው ኩነት ምክትላቸውን ወንጅለዋል።
“ወገኖቼ እንድትረጋጉ እማጸናለሁ። ደጋግሜ እንዳልኩት ሀገራችን ተመልሳ ወደ ጦርነት ተመልሳ አትገባም” ያሉት ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር “ማንም ሕግን ወደ እጁ ሊያስገባ አይገባም። እኔ የምመራው መንግሥት ይኸን ቀውስ ይወጣዋል። በሰላም መንገድ በጽናት እንቆማለን” በማለት ከቀውስ አፋፍ የምትገኘው ሀገራቸውን ለማረጋጋት መሞከራቸው አልቀረም።
ኪር የሀገራቸው ሕዝብ እንዲረጋጋ ጥሪ ማስተላለፋቸው መልካም እንደሆነ የሚናገሩት ዳንኤል አኬች ጥፋቱን ሙሉ በሙሉ በማቻር ላይ ማላከካቸው “አሳዛኝ” ሆኖባቸዋል። አኬች እንደሚሉት በናስር ለተባበሩት መንግሥታት ባልደረቦች፣ 27 ወታደሮች እና ለሜጀር ጄኔራል ማጁር ዳክ ግድያ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንቱ ቢወነጀሉም ማቻር ግን ዋይት አርሚ ተብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን ላይ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችሉበት ተሰሚነት ያላቸው አይመስልም። ጉዳዩን የሚያወሳስበው በናስር ከተከሰተው ግጭት በኋላ አንጻራዊ መረጋጋት ቢታይም “ሌሎች ኹከት ሊፈጥሩ የሚችሉ በርካታ ጉዳዮች” መኖራቸው ነው።
ዳንኤል አኬች “ከፕሬዝደንቱ እና ምክትል ፕሬዝደንቱ ቁጥጥር ውጪ የሆኑ በርካታ ጉዳዮች አሉ” ሲሉ ይናገራሉ። “መሪዎቹ ሁሉንም የሚያስማማ ብሔራዊ አጀንዳ ስለሌላቸው ብዙ ጊዜ ወደ ማኅበረሰባቸው በመሮጥ የተለመደ የጎሳ ፖለቲካ መጫዎቻ ካርዶችን ይመዛሉ። ከዚያ ማኅበረሰቦቻቸውን ሥልጣን ለመያዝ ወይም ለማስጠበቅ እንደ መደራደሪያ ይጠቀሙባቸዋል” የሚሉት የክራይስ ግሩፕ ተንታኝ “የበለጠ ይባባስ እንደሁ ለጊዜው የምናውቀው ነገር የለም። ይሁንና በጁባ ያለው ሁኔታ በውጥረት የተሞላ ነው” በማለት ሥጋታቸውን አጋርተዋል።
ባላንጦቹ ኪር እና ማቻር
የደቡብ ሱዳን ጦር ሠራዊት ቃል አቀባይ ሜጀር ጄኔራል ሉል ሩዋይ ኩዋንግ በተፈጠረው ውጥረት ምክንያት ወደ ብሔራዊው ጦር የተቀላቀሉ የማቻር ታማኞች ሸሽተው መደበቃቸውን ለራዲዮ ታማዙጅ አረጋግጠዋል። ቃል አቀባዩ የሸሹት እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል። ችግሩ ብሔራዊ እንጂ በጎሳዎች መካከል የተፈጠረ እንዳልሆነ ማስተማመኛ ለመስጠት የሞከሩት ሜጀር ጄኔራል ሉል ሩዋይ ኩዋንግ “ሕዝቡ የበቀል እርምጃ እንዳይወስድ” ተማጽነዋል።
ክራይስስ ግሩፕ ግጭቱ ሊባባስ እና ሊሰፋ እንደሚችል ሥጋቱን ገልጿል። ከማቻር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎች ማላካል የተባለችውን ከተማ ሊቆጣጠሩ እንደሚችሉ በጁባ ሥጋት መኖሩን የገለጸው ክራይሲስ ግሩፕ ከተማዋ የተለያዩ ጎሳዎች መኖሪያ በመሆኗ በዘር ላይ ያተኮረ የጅምላ ፍጅት ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቋል። በሌላ በኩል የደቡብ ሱዳን ጦር ናስርን በእጁ ለማስገባት ከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻ ሊከፍት ይችላል። በዚህም ምክንያት ደም አፋሳሽ እና ለመቆጣጠር የሚቸግር ውጊያ በደቡብ ሱዳን ሊቀሰቀስ ይችላል። የኪር እና ማቻር ግንኙነት እንዲህ አይነቱን ሥጋት ለማስቀረት የሚችል አይደለም።
የፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና ምክትላቸው ሪየክ ማቻር “ግንኙነት ብዙ ጥርጣሬዎች እና አለመተማመን” የሞላበት ሲሉ ዳንኤል አኬች ይገልጹታል። ግንኙነታቸውን አዎንታዊ አድርገው ያሻሽሉታል የሚል ዕምነት የሌላቸው አኬች “ግንኙነታቸው ጠበኛ ነው። ይሁንና በጁባ አብረው እንዲቀመጡ በሰላም ሥምምነት ተሳስረዋል። የዚያ መዘዝ ደግሞ ሥምምነቱ ተግባራዊ እንዳይሆን አድርጓል” ሲሉ አስረድተዋል። ሁለቱ ፖለቲከኞች “በወረቀት ላይ ውጥረቱን ለማርገብ ቢስማሙ እንኳ ያንን ተግባራዊ ማድረግ ፈታኝ ነው።”
ውጥረት ሲበረታ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማኅማት ግጭቱ በአፋጣኝ እንዲቆም፣ የተኩስ አቁም እንዲከበር እና የተፋጠጡት ኃይሎች በብሔራዊ ውይይት ችግራቸውን እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ወደ ጁባ አቅንተው ከፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ሚያርዲት ተገናኝተዋል። ወጣቱ ዲፕሎማት ወደ ጁባ ሲያቀኑ የብሔራዊ መረጃ እና ደሕንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሬድዋን ሑሴን እና የፌድራል ፖሊስ ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረሚካኤልን ማስከተላቸው ጉዳዩ ከኢትዮጵያ በኩል የተሰጠውን ከፍ ያለ ትኩረት የሚያሳብቅ ነው። የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ማሕሙድ እና የኬንያው ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ኪር እና ማቻርን ካነጋገሩ በኋላ ሁለቱም መሪዎች ሰላም ለማውረድ እንዲነጋገሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት እንዲቆም ግፊት ያደረገው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኪር እና ማቻር የተፈራረሙትን የሰላም ሥምምነት ተግባራዊ በማድረግ ምርጫ እንዲካሔድ ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል። ይሁንና በፍላጎት እና አዎንታዊ መሻሻል መጥፋት በመጠኑም ቢሆን ባለፉት ዓመታት ቸል የማለት አዝማሚያ አሳይቷል። ለዚህ ትኩረት የሚሹ ዓለም አቀፍ ቀውሶች መበራከት አስተዋጽዖ ማበርከቱ አልቀረም። ዳንኤል አኬች በተለይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቀውሱ የበለጠ እንዳይባባስ በመከላከል እና የሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት ከጥቃት ለመጠበቅ ሚና ሊጫወት እንደሚችል ያምናሉ።
አሜሪካ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ ውጪ መቀመጫቸውን በጁባ ያደረጉ የመንግሥት ሠራተኞች ከደቡብ ሱዳን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጥታለች። አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና ብሪታኒያን ጨምሮ መቀመጫቸውን በጁባ ያደረጉ የምዕራቡ ዓለም ኤምባሲዎች ግጭቱን አውግዘው ኪር እና ማቻር የሚመሯቸው ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።
እሸቴ በቀለ