ዩናይትድ ስቴትስ በየመን ሁቲዎች ላይ የከፈተችው የአየር ድብደባ
ዓርብ፣ መጋቢት 12 2017ዩናይትድ ስቴትስ በየመን ሁቲዎች ላይ ባለፈው ቅዳሜ የጀመረችውን የአየር ጥቃት በዚህ ሳምንትም አጠናክራ ቀጥላለች ሁቲዎችም ከትናት በስተያ በቀይ ባህር የአሜሪካን የጦር መርከብ ላይ ጥቃት ፈጽመናል ሲሉ አስታውቀዋል። አሜሪካ በበኩልዋ ሁቲዎች በመርከብ ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት እስካላቆሙ ድረስ የአየር ድብደባዋን እንደምትቀጥል አስጠንቅቃለች።
አማጽያኑ የየመን ሁቲዎች የሚቆጣጠሩት አል ማሲራህ የተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደዘገበው የትናንት በስተያው ጥቃት የመን ዋና ከተማ ሰንዓን ጨምሮ በተለይ በአማጽያን ይዞታ ስር ባሉ ሌሎች አካባቢዎችም ላይ ያነጣጠረ ነበር ። የዓይን ምስክሮች ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ዩናይትድ ስቴትስ ከትናንት በስተያ በየመን ባካሄደችው የአየር ድብደባ ከተጠቁት ውስጥ አል ጃራፍ የተባለው ሰንዓ ውስጥ ያለ የከተማዋ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ የሚገኝ ወረዳ ይገኝበታል።
የየመን ሁቲዎች በቀይ ባህር የሚፈጽሙት ጥቃትና ያገኛሉ የሚባሉት ጥቅሞች
የየመን ቴሌቪዥን ጣቢያ እንደዘገበው ከሰንዓ ሌላ ሰሜን የመን የሚገኘው ሰዓዳ የተባለው ከተማ አካባቢ እና ከሰንዓ በስተደቡብ ምሥራቅ የሚገኘው የአል ሳውድያ ወረዳም የአየር ድበዳባ ተካሂዶበታል። የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ካነጋገራቸው የሰንዓ ነዋሪዎች መካከል አንዱ አሲም ሙታር እንዳሉት እንዲህ ዓይነት ድብደባ ይፈማል ብለው አልጠበቁም ነበር።
«ፍንዳታው በፈጠረው ድምጽ በጣም ደንግጠን ነበር። ይህ በኛ አካባቢ ይደርሳል ብለን አልጠበቅንም ምክንያቱም አካባቢው በሰላማዊ ሰዎች የተሞላ ሲሆን የማናቸውም ቡድኖች ወታደራዊ ይዞታም ሆነ ጦር ሰፈሮች አይገኙበትም። ቤታችን በቦምብ በመደብደቡ ተገርመናል። እኛም ሴቶች ህጻናትም በድንጋጤ ሸሽተን ወጣን። ሰባት ሴቶችና ሁለት ህጻናት ቆስለዋል። »
ሌላው የሰንዓ ነዋሪ አኬል አል ሳኬፍ እንደተናገሩት ጥቃቱ በርካታ ነዋሪዎች ባሉበት ስፍራ ያለማስጠንቀቂያም ነው የተፈጸመው።
« ሰዎች በብዛት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ እነዚህ ወንጀሎች እና ጭካኔ የተሞላባቸው የቦምብ ድብደባዎች በተንኮል ያለ አንዳች ማስጠንቀቂያ ነው የተካሄዱት። ሰዎቹ ከጾም በኋላ አፍጢራቸውን በማገባደድ ላይ ሳሉ ነበር ጥቃቱ የደረሰው። በዚህ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ባነጣጠረው የአሜሪካን የአየር ጥቃት የአካባቢው ነዋሪዎች ተደናግጠዋል።»
የቀይ ባህር የንግድ መስመር የታወከባቸው ምክንያቶች
ዩናይትድ ስቴትስ በየመኖቹ አማጺ ቡድን ሁቲዎች ላይ ከባድ የአየር ድብደባ የከፈተችው ካለፈው ቅዳሜ አንስቶ ነው። ይህም በጦርነት በተመሰቃቀለችው በየመን መጠን ሰፊ ተቃውሞ አስነስቷል። በቀይ ባህርና በኤደን ባህረ ሰላጤ በሚጓዙ መርከቦች ላይ ጥቃት የመጣል ዛቻም ተጠናክሯል።ባለፈው ቅዳሜው የዩናይትድ ስቴትስ ድብደባ የሁቲ የጤና ሚኒስቴር 53 ሰዎች መገደላቸውንና ቁጥራቸው መቶ የሚደርስ ደግሞ መቁሰላቸውን ተናግሯል። ዩናይትድ ስቴትስ በበኩልዋ በጥቃቱ አንዳንድ ዋና የሚባሉ የሁቲ ባለስልጣናት መገደላቸውን አስታውቃለች። ዋሽንግተን እንዳለችው አማጽያኑ ቁልፍ በሆነው የመርከቦች መጓጓዣ መስመር ላይ መተኮስ እስከሚያቆሙ ድረስ ከፍተኛ ኃይል መጠቀሙን እቀጥላለሁ ስትል ዝታለች።
ይህ የአየር ጥቃት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በጥር ወር ዳግም ስልጣን ከያዙ ወዲህ የተካሄደ ትልቁ ዘመቻ ነው። ሁቲዎች ለሚያደርሱት ጥቃት ኢራንን ተጠያቂ ያደረጉት ትራምፕ ወደፊት በኢራን ላይ መዘዞች እንደሚከተሉም አስጠንቅቀዋል። የኢራን አብዮታዊ ዘብ በበኩሉ ሁቲዎች ነጻ እና የራሳቸውን ስልታዊ የዘመቻ ውሳኔዎች ነው የወሰዱት ሲል ሞግቷል።
ዩናይትድ ስቴትስ አየር ጥቃቱን አጠናክራ ብትቀጥልም ሁቲዎች ግን እነርሱም በአጸፋው በእስራኤል ላይ ጭምር ጥቃታቸውን አባብሰው ማካሄዳቸውን እንደማያቆሙ ነው የተናገሩት። ማክሰኞ የረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳይል ወደ እስራኤል መተኮሳቸውን የተናገሩት ሁቲዎች የጥቃት አድማሳቸውን እንደሚያሰፉም አስታውቀዋል ። እስራኤልን የሚያጠቁትም ከሳምንታት አንጻራዊ መረጋጋት በኋላ እስራኤል በጋዛ እንደገና ለጀመረችው ጥቃት አጸፋ ነው።
ሁቲዎች ከጎርጎሮሳዊው 2023 መጨረሻ አንስቶ በቀይ ባህር በሚተላለፉ ከ100 በሚበልጡ መርከቦች ላይ ጥቃቶችን አድርሰዋል። ይህን የሚያደርጉትም ለለፍልስጤማውያን ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ መሆኑን ይናገራሉ። ጥቃቱ ዓለም አቀፍ ንግድን ያስተጓጎለና የዩናይትድ ስቱትስ ጦርንም ከየመን የሚተኮሱ ሚሳይሎችን ለመመከት ብዙ ገንዘብ የሚያስወጣ ዘመቻ ውስጥ የከተተ ነው።
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ