DW-አማርኛ 60ኛ ዓመት ልዩ ዝግጅት፣ የኃላፊዎች የመልካም ምኞች መልዕክት
እሑድ፣ መጋቢት 28 2017የዶቸ ቬለ በአማርኛ ማሰራጨት የጀመረበትን 60ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የጣቢያዉ ኃላፊዎች ለአማርኛዉ ክፍል ባልደረቦች፣ ለተሳታፊዎችና አድማጮች ያስተለለፉት የመልካም ምኞች መልዕክት።
ፔተር ሊምቡርግ፣ የዶቸ ቬለ ዋና ሥራ አስኪያጅ (ኢንቴንዳንት)
«DW-የአማርኛ አገልግሎት በሁሉም ዘመን፣ በሁሉም ሥርዓትና በጨለማ ወቅት ሁሉ ለኢትዮጵያ ምንግዜም፣ አስተማማኝ፣ ዕዉነተኛና ሚዛናዊ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል።የተቃጣበትን ቅድመ ምርመራ ሁሉ በተሳካ ሁኔታ ተቋቋሞታል።ለዚሕም ነዉ ወደ ዲጂታል ለተደረገዉ የተሳካ ሽግግር የክፍሉ ባልደረቦችን አስተዋፅኦ የማደንቀዉ።ከአጭር ሞገድ ወደ ፌስቡክ፣ ዩቱዩብ፣ቴሌግራም፣ቲክ ቶክና ወዘተ (የተደረገዉ ለዉጥ) ስኬታማ ነዉ።የዓለም የፀጥታና የእሴት ሥርዓት በአስገራሚ ሁኔታ መለዋወጡን ከግምት በማስገባት ለወደፊቱም ለኢትዮጵያና ለአፍሪቃ ቀንድ ወጣቶች የሚደርስ ጠንካራ ድምፅ ያስፈልገናል።ለክፍሉ ባልደረቦች እንኳን ለ60ኛዉ ዓመት አደረሳችሁ።»
ዶክተር ናዲያ ሾልስ፣ የዶቸ ቬለ የፕሮግራም የበላይ ኃላፊ
«ዉድ የአማርኛ አዘጋጆች ሆይ!! መልካም ልደት።ማራኪ፣ አስደናቂ ባሕልና ፖለቲካ ለተሰባጠረባት ኢትዮጵያ ነፃና በሳል ዘገባ ለማሰራጨት አስተዋፅ በማድረጋችን እንኮራለን።እዚያ የሚኖረዉ ሕዝብ ገለልተኛ መረጃ ሊያገኝ የሚገባዉም በባሕልም፣ በፖለቲካም የተወሳሰበ በመሆኑ ነዉ።DW በራዲዮ፣ በአምደ መረብና በቴሌቪዥን የሚያሰራጫቸዉ ዝግጅቶች ከየ10ሩ ኢትዮጵያዊ ለአንዱ ይደርሳሉ።ይሕ፣ ዘገባችን በህዝቡ የሚጠቅሙ ርዕሶች ላይ ማተኮሩን ያመለክታል።
ይሕን (ባናደርግ ኖሮ) ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች፣ማሕበራዊ ፈተናዎችና ተስፋዎች ሳይሰሙ በቀሩ ነበር። ግን ለ60 ዓመት አድርገነዋል።በዚሕ ጊዜ ዉስጥ ኢትዮጵያ መጠነ-ሠፊ ፖለቲካዊና ማሕበራዊ ለዉጥ አድርጋለች።ዝግጅታችንም እንዲሁ።ዛሬ የራዲዮ አሰራጭ ብቻ አይደለንም፣ቲክቶክን በመሳሰሉ በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎችም አሰራጭ ጭምርም ነን እንጂ።አቀራረባችን ሊለይ ይችላል። መሠረታዊ መርሐችን ግን አልተለወጠም።ተዓማኒ፣ሚዛናዊና ዕዉነተኝነት።ዝግጅቱ ለዚሕ እንዲበቃ ላደረጉ ለአማርኛ ክፍል ባልደረቦች፣ለተባባሪዎቻችን ከሁሉም በላይ ለአድማጭ-ተከታታዮቻችን ሁሉ ልባዊ ምስጋናዬ ይድረሳቸዉ።የወደፊቱን በበጎ እናማትራለን።»
የዶቸ ቬለ የፕሮግራሞች ዋና አዘጋጅና የኤድቶሪያል የበላይ ኃላፊ
ከሁሉ አስቀድሜ ለDW-አማርኛ ክፍል የሚሰሩ ባልደረቦችን በሙሉ ለሙያዊና ታላቅ ስራቸዉ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ።ቀላል አይደለም።ይሁንና የአማርኛ ዝግጅታችን ለኢትዮጵያ ከዚያም አልፎ በርግጥ ለዓለም አቀፍ ጉዳዮች ሽፋን መስጠቱ ለአድማጭ-ተከታታዮች በጣም አስፈላጊ ነዉ።
በየሥፍራዉ ያሉ ወኪሎቻችን በየአካባቢዉ የሚሆነዉን እንድንገነዘብ ይረዱናል።የፕሬስ ነፃነት ለኛ በጣም አስፈለጊ ነዉ።ለዚሕም ነዉ ምግባራችሁ ለምንጫችሁም ኢትዮጵያ ለሚገኙ አድማጭ-ተከታታዮቻችሁም በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ የሚሆነዉ።ምክንያቱም ዝግጅቶቻችሁ ሌሎች ከሚሰሩት ለየት ያለ ነዉ።ይህ ማለት የዝግጅቶቻችሁ ይዘት ኢትዮጵያ ዉስጥ ሁሉም ሰዉ በቀላሉ የማያገኘዉ ነዉ።የምታቀርቧቸዉ ታሪኮች፣ ዘገቦች፣ ቃለ መጠይቆች፣ ሴት አድማጮችን ያገናዘቡት ርዕሶች በርግጥ በጣም ጠቃሚ ናቸዉ።
DW ባሁኑ ወቅት ለወጣት አድማጮች ተደራሽ መሆን ይፈልጋል።በዚሕ ረገድም በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ጥግጅቶችን በማቅረብ በተገቢዉ መሥመር ላይ ናችሁ።ጥሩ ዉጤት እያሳየ ነዉ።በሥራችሁ ሒደት ከባድ ሁኔታ እንደሚገጥማችሁ ማመን አለብን።ሥለዚሕ ማለት የምችለዉ በተጨባጭ ከባድ ፈተና ባለበትን ሁኔታ ለምትሰጡት አገልግሎት ክብርና ምስጋና ይገባችኋል ብቻ ነዉ።
በየሥፍራዉ ያሉ ወኪሎቻችንና ከወኪሎቻችን የሚደርሱ (ዘገባዎችን) እዚሕ ቦን ላይ የሚያጠናቅሩ ባልደረቦቻችን የሚያደርጉት አስተዋፅኦ ቀላል አይደለም።የዓለም ፖለቲካዊና ምጣኔ ሐብታዊ ሁኔታን ከግምት ሥናስገባ ከደቡባዊዉ የዓለም ክፍልና ከኢትዮጵያ የሚሰሙ ድምፆችን ማዳመጥና መከታተል ይገባናል።ይሕም ለዓለም አቀፍ አድማጮቻችን በጣም አስፈላጊ ነዉ።ይሕንንም እያደረጋችሁ ነዉ።ለታላቅ ሥራችሁ በድጋሚ አመሰግናለሁ።»
ነጋሽ መሐመድ
ልደት አበበ
ኂሩት መለሰ
መልዕክቶቹን ለማድመጥ የድምፅ ማስቀመቻዉን ይጫኑ