የCOP 26 ውጤት እና የአዳዲስ ስምምነቶቹ ጥንካሬ
ማክሰኞ፣ ኅዳር 7 2014«ለሁለት ሳምንታት በCOP 26 ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ ፖለቲከኞች፣ ተደራዳሪዎች እና ተሟጋቾች ስለአየር ንብረት ለውጥ እውንነት በመረዳት ዓለማችንን ለመጪው ትውልድ ምቹ መኖሪያ እንዴት ማድረግ ይቻላል በሚለው ላይ ተወያይተዋል። በዚህ ሀገር ከተካሄዱ የፖለቲካ ጉባኤዎች ግዙፉ ስብሰባ ነበር። ለዚህ ደግሞ ምክንያት አለ። እነዚህ ሁሉ የዓለም መሪዎች ወደ ግላስጎው የመጡት ፖለቲከኞቻቸው ርምጃ መውሰድ እንደሚኖርባቸው ስለነገሯቸው ነው።»
የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በግላስጎው ስኮትላንድ የተካሄደው የተመድ የአየር ንብረት ተከታታይ ጉባኤ የተሳካ ውጤት ይዞ ለመውጣት እንዲበቃ ብዙ ጥረት መደረጉን በጉባኤው ማጠቃለያ ወቅት ከወቅቱ የብሪታንያ የCOP26 ሊቀመንበር አሎክ ሻርማ ጋር በመሆን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ለማሳየት ሞክረዋል። በዚህ ጉባኤ ላይ በተለይ በአየር ንብረት ለውጥ መዘዝ የሕዝባቸው የዕለት ተዕለት ኑሮ የተናጋ ሃገራት ችግሩን ለማሳየት ያደረጉት ጥረት የጉባኤውን ተሳታፊዎች ትኩረት መሳቡ ነው የተነገረው። ቦሪስ ጆንሰንም ያንን በንግግራቸው ጠቁመዋል። ይኽን ሁሉ ከግምት በማስገባትም በኢንዱስትሪ ያደጉት ሃገራት መሪዎች ትርጉም ያለው የብክለት ቅነሳ ውሳኔ ለማድረግ እንዲስማሙ ግፊት እንደነበርም ገልጸዋል።
«ትናንት ምሽት ዓለም ለማየት ወደሚፈልገው ጨዋታውን ከሚለውጥ ስምምነት ላይ ደርሰናል። 200 የሚሆኑ ሃገራት ከባቢ አየርን ብከላ በመቀነስ ረገድ ወሳኝ ሚናቸውን ለመጫወት በግላስጎው የአየር ንብረት ስምምነት ላይ ስማቸውን አኑረዋል። እየጨመረ ያለውን የሙቀት መጠን ከ1,5 ዲግሪ እንዳይበልጥ ለማድረግ ግልጽ የሆነ አካሄድ ቀይሰዋል፤ የከሰል የኃይል ምንጭት እንዲቆም የሚያደርግ የመጀመሪያ ርምጃ ወስደዋል። ምክንያቱም ለመጀመሪያ ጊዜ የተመድ የአየር ንብረት ጉባኤ ከከሰል ኃይል ማመንጨት እንዲቆም ጠይቋል።»
ጉባኤው በዚህ ረገድ ትልቅ ርምጃ መውሰዱን በማሳየነት የገለጹት ቦሪስ ጆንሰን ከጠቀሷቸው መካከል ደቡብ አፍሪቃ አንዷ ናት። ደቡብ አፍሪቃ ከከሰል ኃይል ማመንጨት ማቆም እንድትችል እና በርካታ አዳዲስ የሥራ መስኮች እንድትከፍት ከብሪታንያ ጋር በበርካታ ሚሊየን የሚገመት ትብብር መዋዋሏንም አመልክተዋል። ከቡድን 20 ሃገራት ጉባኤ ጋርም በመተባበር የድንጋይ ከሰል የኃይል ማመንጫ ዘርፍን ለመደጎም የሚወጣው ገንዘብ ከመጪው ወር ማለቂያ ጀምሮ እንዲያቆም ከስምምነት መደረሱንም ገልጸዋል። ብሪታንያ፣ አብዛኛውን የአውሮጳ ሃገራት እና ሰሜን አሜሪካ ከቅሪት አካል የሚገኝ የነዳጅ ዘይት ፕሮጀክቶችን ለመደጎም የሚያወጡትን ገንዘብም እስከመጪው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ድረስ ለማቆም ማግባባት መቻሉንም ገልጸዋል። እንደእሳቸው አገላለጽም የከሰል የኃይል ምንጭነት እንዲያበቃ በግላስጎው ጉባኤ ላይ ታውጇል። ቦሪስ ጆንሰንም ሆኑ የወቅቱ የብሪታንያያ የCOP26 ሊቀመንበር አሎክ ሻርማ እንደሚሉት ስለከሰል የኃይል ምንጭነት በጉባኤው ላይ ተነስቶ ወደ ስምምነቱ የመካተቱ ነገር በራሱ ታሪካዊ ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው ነው። በመግለጫው ወቅት ሻርማም ይኽንኑ ነው ያረጋገጡት።
«በመጀመሪያ መግለጽ የምፈልገው ይኽ ታሪካዊ ስኬት ነው ብዬ እኔም እንደማስብ ነው። ይኽንን ለመጠበቅ 1,5 ዲግሪ ልንደርስበት የሚገባው ግብ ነው ብለን ስናቅድ ብዙ ሰዎች ይኽን ተጠራጥረው ነበር። ሆኖም ይኽን በእርግጥ አድርገናል። ይኽ ደግሞ የብሪታንያ መንግሥት የሚለው ብቻ ሳይሆን ከመድረኩም፣ በአየር ንብረት ለውጥ ሰለባ ከሆኑ ሃገራት ሰምታችኋል። ስለዚህ ይኽ ታሪካዊ ነው ብዬ አስባለሁ። ሰዎች ይኽን ቃላቸውን እንዴት ነው መጠበቃቸው የሚረጋፈጠው የሚል ጥያቄም አንስታችኋል፤ የፓሪስ ስምምነት መመሪያ አለ፤ ይኽን እንደዋዛ የሚያዩ ይኖራሉ ሆኖም እውነታው ሃገራት ቃል የገቡትን ማድረግ አለማድረጋቸውን ለማረጋገጥ ክትትልና ምዘናው ከውስጡ ተያይዞ ይገኛል። በዚያም ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰል ከእነዚህ ስምምነቶች አንዱ ሆኖ ሊጠቀስ ችሏል።»
እሳቸው ይኽን ይበሉ እንጂ 200 ሃገራት ተቀብለውታል የተባለው ስምምነት በተለይ ከሰልን አስመልክቶ አንዳንድ ሃገራት የቃላት ጨዋታ ላይ አተኩረዋል በሚል ቅሬታ ቀርቦበታል። በርካታ ሃገራት የትናንሽ ደሴት ሃገራትን ጨምሮ ሕንድ እና ቻይና በዚህ ረገድ ይዘውታል ያሉትን አቋም አጥብቀው እየተቹ ነው። ግንባር ቀደም ከከሰል ኃይል በማመንጨት ከሚጠቀሱት ሃገራት በመጀመሪያው መስመር የሚነሱት ሕንድ እና ቻይና ከሰልን ለኃይል ምንጭነት መጠቀምን ማቆም ከሚለው ይልቅ አጠቃቀሙን መቀነስ ላይ ያተኮረ አቋም ማንጸባረቃቸው የተባለው ውሳኔ ትርጉም ያለው ስምምነት ነው የሚለውን ጥያቄ ላይ ጥሎታል። በካልጋሪ ካናዳ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት የዘርፉ ምሁር ዶክተር ጌታቸው አሰፋ ፣የከሰል የኃይል ምንጭነትን ማቆምን አስመልክቶ የሚታየውን አቋም እንዲህ ይገመግሙታል።
«ለአየር ንብረት ለውጥ ፋይዳ ያለው አይደለም። ምናልባት የቋንቋ የቃላት በፊት ስምምነቶች ላይ ታይቶ የማይታወቅ የከሰል ድንጋይ መጠቀስ ለዛውም ደግሞ ያው እንደተከታተልነው ባለቀ ሰዓት ከጥቅም ውጪ እንዲሆን እንሠራለን የሚለውን በሕንድ እና በቻይና ጥቅሙ እየቀነሰ እንዲሄድ ወደሚል እንዲለዝብ ተደርጓል። አሁንም ቁጥሮቹን በምናይበት ሰዓት ለ1.5 ዲግሪ የሚያስፈልገን እጅግ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ቅነሳ አልተገኘም በዚህ አሁን በተገቡት አዳዲስ ቃልኪዳኖች ማለት ነው።»
በነገራችን ላይ በዓለም ቀዳሚዎቹ ከከሰል ኃይል አምራችና ተጠቃሚ ሃገራት ቻይና እና ሕንድ ዋነኞቹ ሲሆኑ፤ ከእነሱ በመቀጠል ዩናይትድ ስቴትስ እና ጀርመን እንደሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ። ፕሮፌሰር ጌታቸው የጉባኤው አስተናግጅ የሆኑት የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንም ሆነ የወቅቱ የCOP 26 ሊቀመንበር አሎክ ሻርማ በስኬትነት የገለጹትን የጉባኤውን አጠቃላይ ውጤት ጥርስ የሌለው ስምምነት በማለት ነው የተቹት።
«ምናልባት እንዳለ ጨለማ ነው ላለማለት ስምምነቱ የሚቀጥለው ዓመት የሚደረገው ጉባኤ የበለጠ ጥርስ ያለው የሚያደማ፤ ጥልቅ የቅነሳ ቃልኪዳኖችን ይዘው ሊመጡ ስምምነቶች ስለተደረገ በዚያ ተስፋ እናደርጋለን። በገንዘቡ በኩል እንደዚሁ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በፊት 100 ቢሊየን ዶላር በዓመት ይሰበሰባል ተብሎ የከሸፈው፣ አሁን ወደ 500 ቢሊየን ይሰበሰባል በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የሚለው እና ለአዳጊ ሃገራት የማጣጣሚያ ፕሮጀክቶች እንዲውል የታሰበው እሱም ያው እንደበጎ ልናየው እንችላለን። አጠቃላይ ግን እንዳልኩት የአየር ንብረት ለውጥ እሚፈልገው ይታወቃል፤ ሳይንሱ የታወቀ ነው፤ ከዚያ አንጻር እዚህ ግባ የማይባል ስምምነት ነው ብዬ ነው የምገልጸው።»
በዚህ ጉባኤ በርካታ ሃገራት ወደ ከባቢ አየር የገባውን ሙቀት አማቂ ጋዝ በተፈጥሮ መንገድ ለማስወገድ ለደን ክብካቤ ትኩረት ሰጥተው ለመሥራት መግባባታቸው ተነግሯል። ከአንድ መቶ የሚበልጡ ሃገራት እስከ ጎርጎሪዮሳዊው 2030 ዓ.ም ድረስ በየበኩላቸው የደን ውድመትን ለማስቆም ተስማምተዋል። ይኽን ውሳኔ በተመለከተም ዶክተር ጌታቸው ሃሳባቸውን አጋርተውናል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት የዓለምን 85 በመቶ የደን ሃብት መያዛቸው የሚነገርላቸው ካናዳ፣ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ኢንዶኔዢያ፣ ዴሞክራቲክ ኮንጎ፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና ዩናይትድ ኪንግደም ናቸው።
ይኽ ጉባኤ ባለፈው ዓመት በኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽን መስፋፋት ምክንያት ተስተጓጉሎ ዘንድሮ የተካሄደ መሆኑ ከወትሮው የሚለየው ሲሆን፤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት በተለይ ታሪካዊ ኃላፊነት ያለባቸው መንግሥታት የሚጠበቅባቸውን ያህል በቂ ርምጃ አልወሰዱም በሚል በሚተቿቸው ወገኖች ዘንድ ሌላ ግርምት የፈጠረ ክስተትም ያስተናገደ ነበር። ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀው ሙቀት አማቂ ጋዝ ቅነሳ እያወዛገበ ባለበት በዚህ ወቅት ብክለት የሚያባብሱ ስልቶችን ተጠቅመው በየግል ጀት ሳይቀር ወደ ጉባኤው የሄዱ ተሳታፊዎች የብዙዎችን ትኩረት መሳባቸውን ፕሮፌሰር ጌታቸው አንስተዋል። COP 26 ከባዶ ፍጻሜ ቢያንስ በረዥም ጊዜ ውስጥም ቢሆን ተግባራዊ ከሆነ ሃገራት የተስማሙበትን አንዳች ስምምነት ይፋ አድርጎ ባለፈው ቅዳሜ ተጠናቅቋል። በመጪው ዓመት በዚህ ወቅት የሚካሄደው COP27 አስተናጋጅ ግብጽ ናት።
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ