የፕሬስ ነጻነት በኢትዮጵያ ያሽቆለቆለበት ምክንያቱ ምን ይሆን?
እሑድ፣ ግንቦት 3 2017በኢትዮጵያ የዛሬ ሰባት ዓመት ግድም ብሩኅ ተስፋ አንጸባርቆ የነበረው የፕሬስ ነጻነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እጅግ እያሽቆለቆለ መሆኑ ይነገርለታል ። የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በተለያዩ ጊዜያት ይፋ በሚያደርጓቸው የፕሬስ ነፃነት መለኪያዎች በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ከድጡ ወደ ማጡ እየተንሸራተተ መሆኑን አሳስበዋል ።
የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (Reporters Without Borders) ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው ዘገባ፦ ኢትዮጵያ የፕሬስ ምዘና ከተደረገባቸው 180 አገራት መካከል ቁልቁል 145ኛ ላይ ትገኛለች ።
ከጎርጎሪዮሱ ያለፈው 2024 ዓመት መዘርዝር ከ141ኛ ደረጃ በአራት ዝቅ ብላለች ማለት ነው እንደ ዘገባው ። የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቱ አምስት ጋዜጠኞች ኢትዮጵያ ውስጥ በእስር ላይ እንደሚገኙ በዘገባው ጠቅሷል ። በርካታ ጋዜጠኞች እስር እና እንግልትን በመፍራት ከአገር መሰደዳቸው ቀደም ሲል በተደጋጋሚ ተዘግቧል ።
አገር ቤት ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች የተለያዩ ጫናዎች እና እንግልቶች እንደሚደርስባቸው በመጥቀስ እያማረሩ ነው ። የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች ቢሯቸው እንደሚመዘበር፤ ኮምፒውተር፣ ካሜራ እና ስልክን የመሳሰሉ መሣሪያዎቻቸው እንደሚወሰዱም እየተናገሩ ነው ። ለመሆኑ፦ «የፕሬስ ነጻነት በኢትዮጵያ ያሽቆለቆለበት ምክንያቱ ምን ይሆን?»፦ የዛሬው እንወያይ መሰናዶዋችን ዐቢይ ትኩረት ነው ።
ሙሉውን ውይይት በድምፅ ማጫወቻው ማድመጥ ይቻላል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ