«የጥቁር ህይወትም ዋጋ አለው»ንቅናቄ ተጽእኖ በጀርመን
ማክሰኞ፣ ሰኔ 23 2012በዩናይትድ ስቴትስ የተቀሰቀሰው «የጥቁር ሕይወትም ዋጋ አለው» የሚለው ንቅናቄ በዓለም ዙሪያ ጥቁሮች በየዘመኑ ሲፈጸምባቸው የቆየው የተዳፈነው በደል ዳግም ጎልቶ እንዲሰማና እንዲታይ አድርጓል። በአውሮጳም ተዛምቶ ተጠናክሮ በቀጠለው የንቅናቄው ሂደት በጥቁር ህዝቦች ላይ በደሎች ለፈጸሙና ላስፈጸሙ ግፈኞች የቆሙ መታሰቢያዎችም በንቅናቄው አራማጆችና በአንዳንድ ሃገራት ደግሞ ከአደጋ እንዲጠበቁ በመንግሥታት እየተነሱ ነው።የባሪያ ንግድ በማካሄድ የሚታወቀው እንግሊዛዊው ኤድዋርድ ኮልስተን በትውልድ ከተማው በእንግሊዝዋ በብሪስተል ከተማ ለዘመናት የቆመለት ሐውልት ከሳምንታት በፊት ወንዝ ውስጥ ተወርውሯል። ቦስተን የነበረው አሜሪካንን ያገኘው የክሪስቶፈር ኮሎምበስም ሐውልት አናት ተገንድሶ ከተገኘ በኋላ የከተማው ባለሥልጣናት ከስፍራው አንስተውታል።ቤልጂግም በወደብ ከተማ በአንትወርፕ ይገኝ የነበረውን የቀድሞ ንጉሥ የዳግማዊ ሊዮፖልድን ሐውልት በንቅናቄው ደጋፊዎች ሊገረሰስ ይችላል ከሚል ስጋት አንስታዋለች።ሊዮፖልድ ቤልጂግ ቅኝ በገዛቻት በኮንጎ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ የኮንጎ ዜጎች ግድያ ተጠያቂ የሚደረጉ በጭካኔያቸው የሚታወሱ ንጉስ ናቸው።በብሪታንያም የኮልስተን ኃውልት ወንዝ ውስጥ ከተጣለ በኋላ ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄ የሚነሳባቸውን ኃውልቶች መንግሥት አንስቷል።በአሜሪካና በአውሮጳ የሚገኙ የቅኝ ግዛት እና የዘረኞች ማስታወሻዎች በሚነሱበት ስያሜዎችም እንዲቀየሩ በሚጠየቅበት በዚህ ወቅት ላይ በጀርመንም ተመሳሳይ ጉዳዮች ትኩረት ስበዋል።ጀርመን ቅኝ በገዛቻቸው የአፍሪቃ ሃገራት በአፍሪቃውያን ላይ የደረሱ ዘግናኝ በደሎችን የሚያስታውሱ ኃውልቶች፣የጎዳና ፣የትምሕርት ቤት የተቋማት ስያሜዎችና የሌሎች ልዩ ልዩ ምልክቶች ጉዳይ ማነጋገሩ ቀጥሏል።ነጭ አሜሪካዊ የፖሊስ መኮንን አፍሪቃዊ አሜሪካዊውን ጆርድ ፍሎይድን በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገድል በስልክ የተቀረጸው ቪድዮ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሀን ይፋ ከሆነ በኋላ ጀርመን ቅኝ በገዛቻቸው የአፍሪቃ ሃገራት ግፍ የፈጸሙ የጦር መሪዎችዋ ዘረኛ ማታወሻዎች የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።መንግሥት እና ህዝቡ ለረዥም ዓመታት ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው የተዉት ይህ ጉዳይ እንዴት መፍትሄ ያግኝ የሚለው ማነጋገሩ ቀጥሏል።በእነዚህን መሰል አወዛጋቢ መታሰቢያዎች ላይ በብሪታንያ በበልጂግ እና በዩናትድ ስቴትስ የተወሰደው የማጥፋት እና የማንሳት እርምጃ በጀርመኑ የሀምቡርግ ዩኒቨርስቲ የአፍሪቃ ጥናት አዋቂና የቅኝ ግዛት ታሪክ ምሁር ዩርገን ሲመርማረር የሚገርም አይደለም። ይህን ማንም ሊረዳው የሚችል ጉዳዩ ነው የሚሉት ዚመረር እነዚህን መታሰቢያዎች ይዞ መጓዝም ለነርሱ የተሰጠውን ክብር መቀጠል ማለት እንደሆነም ያስረዳሉ።
«ሰዉ በተወሰኑ መታሰቢያዎች ላይ ያተኮረበትን ምክንያት መረዳት እችላለሁ።ዘረኝነትን በየቀኑ መጋፈጥ ከባድ ነው። በሰዎች ላይ ኢሰብዓዊ ብዝበዛ በማካሄድና በመጨቆን የተሳተፉ በህዝብ አደባባዮች ላከናወኑት ስራ ክብር ሲሰጣቸው ለብዙዎች ይህ እንደ ማሾፍ ነው የሚታየው።የመታሰቢያዎቹን መንሳትን መቃወም ለነርሱ የተሰጠው ክብር እንዲቀጥል ማድረግ ማለት ነው።»
ከሌሎች የአውሮጳ ኃያላን ቅኝ ገዥዎች ጋር ሲነጻጸር ጀርመን የአጭር ጊዜ የቅኝ ግዛት ታሪክ ነው ያላት።ምንም እንኳን አንዳንድ የጀርመን ግዛቶች እና የግል ኩባንያዎች በውጭ ሃገራት የቆዩ የቅኝ ግዛት ፕሮጀክቶች የነበሯቸው ቢሆንም የጀርመን ቅኝ ገዥነት በይፋ የተጀመረው በጎርጎሮሳዊው 1884 ነው።በርግጥ ከዋነኛዎቹ ዓለም አቀፍ የቅኝ ግዛት ታሪኮች አንዱ የተፈጸመው በጀርመን ምድር ነው። በመጀመሪያው የጀርመን መራሄ መንግሥት በኦቶ ፎን ቢስማርክ ግብዣ ከ14 የአውሮጳ ሃገራትና ግዛቶች የተውጣጡ ተወካዮች አፍሪቃን በይፋ የተቀራመቱት ከ1884 እስከ 1885 በተካሄደው የበርሊን ጉባኤ ላይ ነበር።ጀርመን አፍሪቃን ኦሽንያን እና ምሥራቅ እስያን ቅኝ የገዛችበት ዘመንም ከ1884 አንስቶ እስከ አንደኛው የዓለም ጦርነት ብቻ ነው የዘለቀው። ያም ሆኖ ግን የጀርመን የቅኝ ግዛት ስፋት ከዓለም ቅኝ ገዥዎች በአራተኛ ደረጃ ላይ ነበር የሚገኘው።የዚህ ዘመን በርካታ አሻራዎችም እስካሁን በጀርመንም በውጭ ሃገራትም ይገኛሉ።በመላ ጀርመን የሚገኙ ጎዳናዎች እና አደባባዮች አሁንም በቅኝ ግዛት ዘመን የጦር መሪዎች ነው የሚጠሩት።ከመካከላቸው ካርል ፔተር ፣አዶልፍ ሉደሪትዝ እና ጉስታቭ ናህቲጋል ይገኙበታል።ሌቶቭ ፎርቤክ በተባለው የጀርመን የምሥራቅ አፍሪቃ ዘመቻ አዛዥ ስም የሚጠሩ የጦር ሰፈሮች እና ትምህርት ቤቶች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ነበሩ።አሁን ድረስ የቀድሞው የጀርመን የምሥራቅ አፍሪቃ ገዥ የሄርማን ቪስማን ሐውልት ማዕከላዊ ጀርመን ውስጥ በምትገኘው በባድ ላውተርቤርግ ይገኛል።የጀርመን የምዕራብ አፍሪቃ የዛሪዎቹ የካሜሩን እና የቶጎ ኮሚሽነር ለነበረው ለናህቲጋልም በምሥራቃዊቷ በሽቴንዳል ከተማ መታሰቢያ አለ። ታዲያ ጀርመን የቀድሞውን የቅኝ ግዛት ታሪኳን እንዴት ታድስ የሚለው ጥያቄ ለማንሳት ቀላል፣ ለመመለስ ግን ከባድ ሆኗል።እነዚህ ሁሉ ሐውልቶችስ ምን ይሁኑ የጎዳና ስያሜዎችስ?ከዚሁ ጋር ከየሃገሩ ዘርፈው በየቤተ መዝክራቸው ያጠራቀሙት ብዛት ያለው ቅርስስ ምን ይደረግ?የሚሉትና የመሳሰሉት ጥያቄዎች እያነጋገሩ ነው።እነዚህን መታሰቢያዎች ማንሳት ወይም በሌላ መቀየርን ብዙ ማከራከሩ አልቀረም።ታዲያ እነዚህ የጀርመንን የቅኝ ግዛት ዘመን አግዝፈው የሚያስታውሱ ምልክቶች ምን ቢደረጉ ነው የሚሻለው?የቅን ግዛት ታሪክ ምሁሩ ሲመረር ጉዳዩን አስፍቶ በሰከነ መንገድ ማጤን ይገባል ይላሉ። በሀምቡርግ ዩኒቨርስቲ የአፍሪቃ ጉዳዮች አዋቂ እና የቅኝ ግዛት ታሪክ ምሁር ሲመረር ጉዳዩ ብዙ ገጽታዎች ያሉት መሆኑን ገልጸው ሆኖም በርሳቸው እምነት ለነዚህ ሰዎች የቆሙ መታሰቢያዎች የታሪክ ምንጮች ሆነው መጠበቃቸውን እፈልጋለሁ ብለዋል።
«ይህ ሁሉም በተቻለ ሁሉ በስፋት በተለይ የቅኝ ግዛት እና የዘረኝነት ሰለባዎች በሚሳተፍበት የውይይት ሂደት ነው መወሰን ያለበት።እንደ ታሪክ ምሁር ታሪካዊ ቅርሶች እንደ ታሪክ ምንጭነት እንዲጠበቁ ነው ፍላጎቴ።ሆኖም ቅርሶቹ የእነርሱን ጀግንነት እንዲያጎሉ መሆን የለባቸውም።ለምሳሌ መዘቅዘቅ ወይም ማጋደም ይቻላል።በአንድ ወቅት ክብር ተሰጥቷቸው እንደነበር ማየት ይቻላል። ይህ የቅኝ አገዛዝ እና የዘረኝነት ታሪክ አንዱ አካል ነው።ይህም ቅኝ አገዛዝ እና ዘረኝነትን በአጠቃላይ ለመጋፈጥ ጥሩ መንደርደሪያ ይሆናል።»
ከሁሉ ትልቁ ጥያቄ ጀርመን በቅኝ ግዛት ዘመን በደቡብ ምዕራብ አፍሪቃ በናሚብያ በሄሬሮና በናማ በተፈጸሙት ግፎች ፣በምሥራቅ አፍሪቃ ተነስቶ ለነበረው የማጂ ማጂ አመጽ የተወሰደው እርምጃ እንዲሁም ሆነ ተብለው በተፈጸሙ ረሃቦች በሽህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ላለቁባቸው የዘር ማጥፋት ወንጀሎች፣ በይፋ ይቅርታ መጠየቅ አለባት የለባትም የሚለው ሆኗል።ለነዚህ እልቂቶች በርሊን ካሳ ትክፈል አትክፈል የሚለውም እንዲሁ ትኩረት ሊሰጠው የሚስብ ጉዳይ ነው።እነዚህ ሁሉ የጀርመን የቅኝ ግዛት ዘመን ጥላሸቶች ናቸው።
በጀርመን ዋና ከተማ በበርሊን ሰሜናዊ ክፍል አፍሪቃን ክዋርተር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከአፍሪቃ ጋር የተያያዙ ስያሜዎች አሉ።የአካባቢው ሸንጎ በቅርብ ዓመታት ሁለት መንገዶችና አንድ አደባባይ የጀርመን ቅኝ አገዛዝን በተዋጉ አፍሪቃውያን እንዲሰየሙ ወስኗል ።ሆኖም የአካባቢው ነዋሪዎች እና በስፍራው የንግድ ድርጅቶች ያሏቸው ሰዎች ይህን ተቃውመዋል። ምክንያታቸው ደግሞ ፖለቲካዊ ሳይሆን የአካባቢው ስያሜ ሲቀየር ብዙ ችግሮችን ያስከትልብናል ፣ብዙ ዋጋ ያስከፍለናል የሚል ነው።አንዳንዶች ደግሞ ሁሉም ነገር እንደነበረ እንዲቆይ እንፈልጋለን ባይ ናቸው።በዚህ ጉዳይ ላይ for the African ክዋርተር የተባለው ኢኒሽየቲቭ አንድ መፍትሄ ይዞ መጥቷል።የመጀመሪያው የጀርመን የደቡብ ምዕራብ አፍሪቃ ቅኝ ግዛት መሥራች ፍራንዝ አዶልፍ ኤድዋርዶ ሉደሪትዝ ጎዳና ለምሳሌ ተመሳሳይ መጠሪያ ባላት የናሚቢያ ጎዳና እንዲሰየም ፣ቶጎላንድና ካሜሩንን የመጀመሪያዎቹ የጀርመን ቅኝ ግዛቶች ለመሆን ያበቃቸው በጉስታቭ ናህቲጋል የተሰየመው አደባባይ ደግሞ ጆሀን ናህቲጋል በተባለው የስነ መለኮት ምሁር እንዲጠራ አስታራቂ ሃሳብ አቅርበዋል።ምሥራቅ አፍሪቃን በአሰቃቂ ሁኔታ በገዛው በካርል ፔተርስ ተሰይሞ የነበረው የፔተር ጎዳናም በ1986 ናዚ ጀርመንን በተዋጋው
በሃንስ ፔተርስ እንዲተካ ተደርጓል። ይህን ብዙ ሰዎች እንደ መሸንገያ ነው የሚቆጥሩት።እነርሱ እንደሚሉት ይህ በጀርመን የቅኝ ግዛት ዘመን በስፋት የተፈፀመውን ግፍ ጭቆናና ግድያ በአግባቡ ትኩረት እንዲሰጠው አላደረገም። የአፍሪቃ አንበሳ እየተባለ የሚጠራው የጀርመን የምሥራቅ አፍሪቃ ዘመቻ አዛዥ ፓውል ኤሚል ፎን ሌቶቭ ፎርቤክ እና ሎታር ፎን ትሮታ በአፍሪቃ የጀርመን ቅኝ ግዛቶች የሚነሱ አመጾችን በማፈን ትልቅ ሚና የተጫወቱ የጦር መሪዎች ናቸው።የእነዚህ የጦር መሪዎች ማስታወሻዎች የሚገኙበት የጀርመንዋ የሀምቡርግ ከተማ መስተዳድር ለነዚህ የጀርመን ታሪክ የጨለማ ምዕራፎች የተሻለ መፍትሄ እንዲፈልጉ ሃላፊነቱን መጪው ትውልድ እንዲወስድ እንደሚፈልግ አስታውቋል።ሃሳቡ እነዚህን የታሪክ ጉድፎች ማወደስንም ሆነ መታሰቢያቸውንም ደብዛውን ማጥፋትን ይቃወማል።ከዚያ ይልቅ ትኩረቱ ወደ ታሪክ ማስታወሻነት እንዲሆን ነው። ከሀያ በላይ በሚሆኑ የጀርመን ግዛቶች ድህረ ቅኝ ግዛት የተሰኘውና ስለለጉዳዩ ግንዛቤ ለማዳበርና ትኩረት እንዲሰጠውም የሚሰራው ቡድን በጉዳዩ ፤ላይ የሚነሳውን ክርክር አንድ እርምጃ ወደፊት ወስዶታል።ቡድኑ ሀምቡርግ በአጠቃላይ ከቅኝ ግዛት ማስታወሻ እንድትጸዳ የፀረ ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴዎች ታሪኮች እንዲታወቁ የቅኝ ግዛትና የዘረኝነት ሰለባዎችም በክብር እንዲታሰቡ ጠይቋል።በአሁኑ ጊዜ ያለፈው የጀርመን የቅኝ ግዛት ታሪክ እንዴት ቢታወስ ይሻላል በሚል የሚካሄደው ውይይት ቀጥሏል። ጀርመናውያንም ቀድሞውን የቅኝ ግዛት ታሪካቸውን መለስ ብለው እንዲመለከቱ አድርጓል።ሆኖም በዚህ ረገድ ለውጥ ለማምጣት አሁንም ብዙ እንደሚቀር ነው አስተያየት ሰጭዎች የሚናገሩት።
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ