የጎርፍ አደጋ፣ የመድን ሽፋን እና የመንግሥት ኃላፊነት
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 19 2017ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ የጣለው ከባድ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ በውል ያልታወቀ የንብረት ጉዳት አድርሷል። በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው አንድ የመድን (ኢንሹራንስ) ሽፋን ባለሙያ "ጎርፍ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ እና አውሎ ንፋስን የመሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎች በተለየ ሁኔታ ካልተረጋገጠ በስተቀር በመድን ሽፋን አይካተቱም" ብለዋል። መሠረተ ልማቶች በአግባቡ ሳይገነቡ ቀርቶ በግለሰቦች ንብረት ላይ መሰል ጉዳት ቢደርስ የመንግሥት ካሳ የመክፈል እና አለመክፈል ኃላፊነትን የጠየቅናቸው ባለሙያ "እስካሁን የታዩ ነገሮች የሉም" ሲሉ መልሰዋል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ በአዲስ አበባ ለጎርፍና ተያያዥ አደጋዎች ተጋላጭ የሆኑ የተባሉ 247 ቦታታዎች መለየታቸውንና 731 ሰዎች በዘላቂነት ከቦታቸው እንዲነሱ መደረጉን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል። ሰሞነኛው በአዲስ አበባ የደረሰው አይነት ከባድ የጎርፍ አደጋ ሲከሰት በሀገሪቱ ያሉት 18 የኢንሹራንስ ድርጅቶች ይህንን የመድን አገልግሎት በምን መልኩ ያስተናግዱታል የሚለውን ለ21 ዓመት በኢንሹራንስ ዘርፍ በካሳ አከፋፈል እና ውል ክፍል በኃላፊነት ጭምር ያገለገሉትን ባለሙያ አቶ ሰለሞን ኦሊን ጠይቀናቸዋል።
የኢንሹራንስ ድርጅቶቹ ሁሉም በሚባል ደረጃ "ለአደጋ፣ ለእሳት፣ ለስርቆት እና ለሶስተኛ ወገን ተጠያቂነት ሽፋን" ከመስጠት በዘለለ ለተፈጥሮ አደጋዎች ሽፋን ሰጪ እንዳልሆኑ የገለፁት ባለሙያው ለምን ለሚለው ጥያቄ "ከዕድገታችን ጋር የሚያያዝ ነው" ሲሉ መልሰዋል። "ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የሞተር ኢንሹራንስ እስካሁን ድረስ ሽፋን አራዝሞ [የመድን ሽፋን] ከሚሸጥ አንድ የኢንሹራንስ ኩባንያ በስተቀር ሌሎቹ በፖሊሲያቸው ላይ ተፈጥሯዊ ነገሮችን አይሸፍንም፣ አያካትትም"።እንደ ባለሙያው ይህ ማለት ግን በፖሊሲ የተደገፈ ባይሆንም ይህንን አገልግሎት የሚፈልግ ደንበኛ የውል ሥምምነት ከሚገባበት ተቋም ጋር ተነጋግሮና ተጨማሪ ክፍያዎችን በመክፈል ተጠቃሚ መሆን አይችልም ማለት አይደለም። ንብረት ለጉዳት እና አደጋ ሲጋለጥ ዋስትና የሚሰጥ የመድን ሽፋን (ኢንሹራንስ) ውስጥ የመግባት ልማድ እንዴት ይታያል የሚለውም ሌላኛው ጉዳይ ነው።
"ማኅበረሰባችን ምን ያህል በራስ ተነሳሽነት ለመጠቀም [የመድን ሽፋን ለመግባት] ፍላጎት አለው የሚለው ነገር ገና ነው አሁንም። አልበሰለም።ኢንሹራንስ-የመኪና ዋጋዎች ጨምሯል። ግን እንደ ወር ወጪ አድርገው አያስቡትም"። በዚሁ ሳምንት የተከሰተው ጎርፍ ጥቂት የማይባሉ ተሽከርካሪዎችን አጥለቅልቆ ታይቷል። የመንገድ እና የፍሳሽ መሠረተ ልማቶች በሚከናወኑበት እና ለአገልግሎት ክፍት ከሆኑ በኋላ መሰል አደጋዎች ሲከሰቱ የመንግሥት ካሳ የመክፈል እና ያለመክፈል ኃላፊነት ምን ይመስላል የሚለውንም የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ መታገስ ውለታውን ጠይቀናቸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያወጣው አዋጅ ቁጥር 74/2014 የአስፈጻሚ አካላት ተግባርና ኃላፊነት መደንገጉን ጠቅሰው በቅድሚያ ግን የደረሰው ጎርፍ ተፈሯዊ ነው ወይስ የመንግሥት እካላት ሥራቸውን በአባቡ ባለመሥራታቸው የመጣ ነው የሚለው መለየት አለበት ብለዋል።
የኢንሹራንስ ባለሚያውን አቶ ሰለሞን ኦሊም በዚሁ ላይ ምላሽ ሰጥተዋል። "ከመንግሥት ወይም ደግሞ ከሌላ ተቋም ባጋጠመ ችግር የሚመጡ ችግሮችን ካሳ ይከፈላሉ አይከፈሉም እስካሁን የታዩ ነገሮች የሉም"። ከዚሁ ጋር በተገናኘ በአዲስ አበባ ለጎርፍና ተያያዥ አደጋዎች ተጋላጭ የሆኑ የተባሉ 247 ቦታታዎች መለየታቸውን፣ 731 ሰዎች በዘላቂነት ከቦታቸው እንዲነሱ መደረጉንና በ64 ቦታዎች የጎርፍ መከላካያ ግንብ መሠራቱን ትናንት መግለጫ የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ተናግረዋል።
ሰለሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር