የግንቦት 25 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ግንቦት 25 2017በፊላዴልፊያው የ800 እና 1,500 ሜትር የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ድርቤ ወልተጂ በማሸነፍ የግራንድ ስላም ተሸላሚ ሁናለች ። የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ያሸነፈው ፓሪ ሳን ጃርሞ ደጋፊዎች ፓሪስ ውስጥ ባስነሱት ነውጥ ከአምስት መቶ በላይ ሰዎች ታሰሩ ። ኦስማን ዴምቤል የሻምፒዮንስ ሊግ ምርጥ ተጨዋች ተብሎ ተሰይሟል ።
ጀርመናዊው የሜዳ ቴኒስ ተፎካካሪ አሌክሳንደር ዜቬሬቭ በፈረንሳይ የሜዳ ቴኒስ ዛሬ ባደረገው ግጥሚያ ለሩብ ፍጻሜ በቅቷል ።
ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ድርቤ ወልተጂ የግራንድ ስላም ባለ ድል
ፊላዴልፊያ ውስጥ በተከናወነው የ800 እና 1,500 ሜትር የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ድርቤ ወልተጂ በማሸነፍ የግራንድ ስላም የበላይነትን ተቆናጠጠች ።
ድርቤ ትናንት የ800 ሜትሩን ፉክክር በድል ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜ 1:58.94 ነው ። ቅዳሜ ዕለት በ1,500 ሜትርም 3:58.04 በመሮጥ ለድል መብቃቷ የሚታወቅ ነው ። የብሪታንያዋ ጄኦርጂያ ሀንተር ቤል ፤እንዲሁም የኦሎምፒክ የብር ሜዳሊያ ባለድል አሜሪካዊቷ ጄሲካ ሑልን አስከትላ ነው በከፍተኛ ነጥብ ማሸነፍ የቻለችው ። ሩጫው እንዲጀመር ደውሉ ባቃጨለበት ቅጽበት ቀዳሚ የነበረችው ጄሲካ በስተመጨረሻ ለድርቤ እጅ ሰጥታለች ። የግራንድ ስላም ፉክክሮች አሸናፊዎች በየውድድሩ የ100,000 ዶላር ተሸላሚ ናቸው ። ድርቤ ከስምንት ሳምንት በፊትም ጃማይካ ውስጥ በተከናወነው የኪንግስተን ግራንድ ስላም አሸናፊ ነበረች ።
ኢትዮጵያውያን አዳጊ ብቁ የእግር ኳስ ተጨዋቾች
ከአራት ዓመት በኋላ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2029 ኢትዮጵያውያን አዳጊ ብቁ የእግር ኳስ ተጨዋቾችን ለማፍራት ግብ ያደረገው መርኃ ግብር ትናንት ተጠናቅቋል ። በሲዳማ ክልል በሐዋሳ ከተማ ጊዜያዊ ማቆያ አዳጊዎች ከዓርብ ጀምሮ ስልጠና እና ምዘና ሲሰጣቸው መቆየቱም ታውቋል ። እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ተጨዋቾችን በቡድን በመከፋፈል ከሀሁ ታዳጊዎች ፕሮጀክት ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ መደረጉንም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዐሳውቋል ።
በባለሞያዎች አማካኝነትም ለታዳጊዎቹ የተናጠል ቃለ መጠይቅ እንደተደረገ ብሎም አዳጊዎቹ ስለ ጠንካራ እና ሊያሻሽሏቸው ስለሚገባቸው ደካማ ጎኖቻቸው ላይ ውይይት መደረጉም ተጠቅሷል ። በውድድሮቹ ላይ ተስፋ የሚጣልባቸው አዳጊ ተጨዋቾች መታየታቸውም ታውቋል ። እነዚህን አዳጊዎች ከተወሰነ ወቅታዊ እንቅስቃሴ ባሻገር በተከታታይ እና በዘላቂነት ሰብስቦ ማሰልጠኑ ለወደፊቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት ወሳኝ ነው ። አዳጊዎች ላይ ከታች አንስቶ መሥራቱ ሊበረታታ እና ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው እንላለን ።
ብጥብጥ በፓሪስ ከተማ ከፓሪ ሳንጃርሞ ድል ማግስት
በፓሪ ሳንጃርሞ ለተገኘው ድል ፓሪስ ከተማ ሾንዜሊዜ አደባባይ ደስታቸውን ለመግለጥ በተሰባሰቡ 100,000 ደጋፊዎች መካከል ብጥብጥ ተከስቶ በርካቶች ታስረዋል ። ዛሬ ንጋት ላይ ከታሰሩት 79 በጥባጮች በተጨማሪ እሁድ አመሻሹን በነበረው ፈንጠዝያ ብጥብጥ ያስነሱ እና ቃጠሎ የፈጠሩ 560 ሰዎች መታሰራቸው ታውቋል ። 500ዎቹ የፓሪስ ከተማ ነዋሪዎች መሆናቸውም ተዘግቧል ። በጥብብጡ አንድ የ17 ዓመት አዳጊ ቅዳሙሜዕ ለት በጩቤ ተወግቶ ሕይወቱ ማለፉ ተገልጧል ። የፓሪስ ከተማ ነዋሪ ባልደረባችን ሃይማኖት ጥሩነህ ሁኔታውን በቦታው ተመልክታለች ። ከድሉ በኋላ ፓሪስ ድባቡ ምን ይመስል ነበር፤ የብጥብጡ እና የእስሩ ምክንያትስ?
ስፔናዊው አሰልጣኝ ሉዊስ ኤንሪኬ ፓሪ ሳንጃርሞ የመጀመሪያ ዋንጫ እንዲያነሳ አስችለዋል ። በአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ፓሪ ሳንጃርሞ የጣሊያኑ ኢንተር ሚላንን 5 ለ0 አንኮታኩቶ ዋንጫውን ካነሳ በኋላ የቡድኑ ስኬት ምክንያቱ እሳቸውም ናቸው ይባላል በዋናነት ።
ፓሪ ሳንጃርሞ በፈረንሣይ ታሪክ ጽፏል
በፓሪ ሳንጃርሞ ዝነኞቹ እነ ሊዮኔል ሜሲ፣ ኔይማር እና ኬሊያን እምባፔ ማሳካት ያልቻሉትን እነ ኦስማን ዴምቤሌ እና ሌሎች ወጣት ተጨዋቾች እውን አድርገውታል ። እንደውም እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ1993 ወዲህ ዖሎምፒክ ማርሴይ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ካነሳ ወዲህ ፓሪ ሳንጃርሞ በፈረንሳይ ሁለተኛው ቡድን በመሆን ታሪክ መሥራት ችለዋል።
የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ምርጥ ተጨዋች የተሰኘው እየፓሪ ሳንጃርሞ አጥቂ ዖስማን ዴምቤል የበባሎን ደኦር የወርቅ ኳስ እንዲሸልም ሲል የቡድን አጋሩ እና አምበሉ ማርኩዊኞስ ፊፋን ጠየቀ ። በሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች ፈረንሳዊው አጥቂ ኦስማን ዴምቤል ስምንት ግቦችን በማስቆጠር በርካታ ግብ የሚሆኑ ኳሶችንም ማመቻቸት የቻለ ድንቅ ተጨዋች ነው ።
ወደ ሪያል ማድሪድ ባቀናው ስፔናዊው አሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ ምትክ ኤሪክ ቴን ሐግ የባዬር ሌቨርኩሰን አሰልጣኝ ሁነዋል ።
አሌክሳንደር ዜቬሬቭ ዛሬ በሜዳ ቴኒስ ለሩብ ፍጻሜ ደረሰ
ጀርመናዊው የሜዳ ቴኒስ ተፎካካሪ አሌክሳንደር ዜቬሬቭ ዛሬ በተከናወነው የፈረንሳይ የሜዳ ቴኒስ ፉክክር ያለ ብዙ ልፋት ወደ ሩብ ፍጻሜ አለፈ ። ኔዘርላንዳዊው ተፎካካሪ ታሎን ክሪክስፑር ከ51ኛው ደቂቃ በኋላ በውድድሩ መቆየት አልቻለም ። ያለፈው ዓመት የፍጻሜ ተፎካካሪ አሌክሳንደር ዜቬሬቭ የዛሬ ተፎካካሪው መጉዳቱ ጠቅሞታል ። ኔዘርላንዳዊው ተፎካካሪ ከ6:4 እና 3:0 መመራት በኋላ ሆዱ አካባቢ በነበረው ሕመም መቀጠል አልቻለም ። በዚህም አሌክሳንደር ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል ። ሠርቢያዊው ኖቫክ ጄኮቪችም በ100ኛ ድሉ ዛሬ ለሩብ ፍጻሜ በቅቷል
ከጆርጅ ሩሴል ጋር በተሽከርካሪ የተላተመው ማክስ ፈርሽታፐን ይቅርታ ጠየቀ
ትናንት በነበረው የስፔን ሽቅድምድም የፎርሙላ አንድ የአራት ጊዜያት የዓለም ባለድሉ ማክስ ፈርሽታፐን ከጆርጅ ሩሴል ጋር በመጋጨቱ ይቅርታ ጠየቀ ። የትናንቱ ሽቅድምድም ሊጠናቀቅ ሁለት ዙር ሲቀረው ማክስ በመጋጨቱም 10 ሰከንድ ተቀጥቷል ። ጆርጅ ሩሴል ትናንት ግጭቱ የተፈጠረው በማክስ ሆን ተብሎ ነው ሲል ቅሬታ አቅርቦ ነበር ።
በትናንቱ ፉክክር የማክላረኑ አሽከርካሪ ዖስካር ፒያስትሪ ሲያሸንፍ፤ ሌላኛው የማክላረን አሽከርካሪ ላንዶ ኖሪስ ሁለተኛ ደረጃ አግኝቷል ። የፌራሪው አሽከርካሪ ሻርል ሌክሌርክ ሦስኛ ሲወጣ፤ የመርሴዲሱ ጆርጅ ሩሴል አራተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቅቋል ። የፌራሪው አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን ከኪክ ዛውበር አሽከርካሪው ኒክ ሁይልከንበርግ ቀጥሎ በስድስተኛ ደረጃ አጠናቅቋል ። በአጠቃላይ ነጥብ ዖስካር ፒያስትሪ አንደኛ፤ ላንዶ ኖሪስ ሁለተኛ፤ ጆርጅ ሩሴል ሦስተኛ ናቸው ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ