የጃፓን አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዝግጅት እና የእንግሊዝ ሴቶች ድል
ሰኞ፣ ሐምሌ 21 2017የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የፊታችን መስከረም መጀመሪያ ጃፓን በምታስተናግደው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የሚሳተፉ አትሌቶችን ይፋ አድርጓል። ኢትዮጵያ በዓለማቀፍ ደረጃ ስም እና ዝና ያተረፈችባቸውን ጨምሮ በተለያዩ የውድድር ርቀቶች የሚሳተፉ አትሌቶች እና አሰልጣኞች ይፋ ሲደረጉ ለወትሮ ወቀሳ የማያጣው የፌዴሬሽኑ አሰራር እንዴት ይታያል ? በዝግጅቱ እንጠይቃለን።
በእግር ኳስ የእንግሊዙ ሶስቱ አናብስት የ2025 የአውሮጳ ሴቶች ዋንጫን አነሳ ። እንግሊዝ የስፔይን የሴቶች ብሔራዊ ቡድን አቻዋን በመለያ ምት ስታሸንፍ ለራሷ ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ ማሸነፍ ሲያስችላት የዓለም እና የአውሮጳ ዋንጫን በአንድ የውድድር ዓመት የማሸነፍ ህልም የነበሩውን የስፔይን አቻዋ ሳይሳካ ቀርቷል።
ሌሎችም የወዳጅነት ጫወታዎች እና ወሳኝ የዝውውር መረጃዎች ተካተዋል።
አቴሌቲክስ
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጃፓን ለምታስተናግደው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተመረጡ አትሌቶችን ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል ። ፌዴሬሽኑ በተለይ በማራቶን ውድድር ላይ የሚሳተፉ አትሌቶችን በቅድሚያ ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን በተቀሩ ርቀቶች የተመለመሉትን አትሌቶች ግን አዘግይቶ ነው ይፋ ያደረገው ። በምርጫው አንጋፋ እና ውጤታማ አትሌቶችን ጨምሮ በቅርብ ጊዜ ውጤታማ እየሆኑ የመጡ ወጣት አትሌቶች ተካተውበታል።
ፌዴሬሽኑ እነማንን መረጠ የሚለውን ጨምሮ በአጠቃላይ የምርጫ ሂደቱን አንድምታ በተመለከተ የአዲስ አበባውን ተባባሪ ዘጋቢያችን ኦምና ታደለን በስልክ አነጋግረነዋል።
አትሌት አበባ አረጋዊ ከ13 ዓመታት በኋላ ሜዳሊያ፤ የዓለም ክለቦች ዋንጫ ፍልሚያዎች
በእግር ኳስ ዜናዎች
የእንግሊዝ የሴቶች ብሄራዊ ቡድን ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት የአውሮጳ ዋንጫን አነሳ ። ስዊዘርላንድ ባስተናገደችው የ2025 የአውሮጳ የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫን ያሸነፈችው እንግሊዝ የዓለም ሻምፒዮናዋን ስፔይንን በመለያ ምት 3 ለ 1 በሆነ ዉጤት ነው። ሁለቱ ቡድኖች ትናንት እሁድ ባስል ሴይንት ጃኮብ ፓርክ ስቴድየም ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ጫወታ የመደበኛ የጫወታ ጊዜያቸውን አንድ አቻ ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ ነው። በመደበኛ የጫወታ ጊዜ ግብ የማስቆጠሩን ቅድሚያ የወሰዱት ስፔይኖች ሲሆኑ ኦና ባቴሌ በ25ኛው ደቂቃ ኳሷን ከመረብ ማገናኘት ችላለች ። የመጀመሪያውን አጋማሽ ተችነው የተቻወቱት ስፔይኖች የዓለም ዋንጫ ገድላቸውን ይደግሙ ይሆን ተብሎ ይጠበቅ በነበረ ሰዓት ግን ከዕረፍት መልስ የተቆጠረባቸውን ጎል ለመቀልበስ ገፍተው የተጫወቱት ሶስቱ አናብስ በኋላ ቀንቷቸው በ57ኛው ደቂቃ ሩሶ አማካኝነት የአቻነት ጎላቸውን ማስቆጠር ችለዋል።
ለአውሮጳ እግር ኳስ ጨዋታ ውድድር የጀርመን ቡዱን ዝግጅት
ሁለቱም ቡድኖች አንዱ በአንዱ ላይ ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ያደረጓቸው ጥረቶች ባለመስመራቸው ወደ መለያ ምት ለማቅናት ተገደዋል። በዚህ የስፔይን የሴቶች ብሄራዊ ቡድን አባል ልክ እንደወንዶቹ ሁሉ ለዋንጫ የሚደረገው የመለያ ምት ሳይቀናቸው ቀርቶ ድሉን ለእንግሊዞች አሳልፈው ለመስጠት ተገደዋል።
በዚህም እንግሊዝ ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ የአውሮጳን ዋንጫ ማንሳት አስችሏታል። በጎርጎርሳዉinኡ 2022 ከጀርመን ጋር ለፍጻሜ የደረሰችው እንግሊዝ በተመሳሳይ የመለያ ምት 2 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፋ የዋንጫው ባለቤት መሆኗ አይዘነጋም። በጎርጎርሳዉያኑ 1984 የተጀመረው የአውሮጳ የሴቶች የእግር ኳስ ዋንጫን 7 ጊዜ በማንሳት ጀርመን ቀዳሚ ናት። ኖርዌይ እና እንግሊዝ ሁለት ሁለት ጊዜ አንስተዋል። ኔዘርላንድስ እና ስዊዲን አንድ አንድ ጊዜ ዋንጫውን ስመዋል።
የቅድመ ውድድር ዘመን ዉጤት
ከሰሞኑ ትኩረት ካገኙ መረጃዎች መካከል የአውሮጳ ኃያላን ክለቦች የቅድመ የውድድር ዘመን የወዳጅነት ጫወታዎች እና የተመዘገቡ ውጤቶች ተጠቃሾች ናቸው ። የ2025 /26 የውድድር ዘመን ከመጀመሩ አስቀድሞ ክለቦች አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ከሚያደርጓቸው ሩጫዎች በተጨማሪ አቅማቸውን የሚፈትሹባቸው የወዳጅነት ጫወታዎች ትኩረት ስበዋል። በርካቶች ከተከታተሏቸው እና ትናንት እሁድ ከተደረጉ የወዳጅነት ጫወታዎች መካከል ወደ አሜሪካ አቅንተ ው በኒው ጀርሲ የተገናኙት ማንችስተር ዩናይትድ እና ዌስትሃም ጫወታ በዩናይትድ 2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ወደ ደቡብ እሲያዊቷ ሃገር ሲንጋፖር ተጉዘው ጫወታቸውን ያደረጉት አርሴናል እና ኒውካስትል በአርሴናል የ3 ለ 2 አሸናፊነት ተጠናቋል። ወደ ሩቅ ምስራቋ ሀገር ጃፓን የተጓዘው የስፔይኑ ኃያል ባርሴሎና ከጃፓኑ ቪዝልኮቤ ጋር ባደረገው ቻወታ 3 ለ 1 ማሸነፍ ችሏል።
የዝውውር ዜናዎች
በዝውውር ዜናዎች የእንግሊዙ ሊቨርፑል የክንፍ አጥቂ የነበረው ሊውዝ ዲያዝ የቡንደስሊጋውን ሃያል ባየር ሙንሽንን ለመቀላቀል ከቻፍ መድረሱ ተሰምቷል። ዲያዝ በዓመት እስከ 12 ሚሊዮን ዩሮ ደሞዝ ሊያስገኝለት በሚችል የዝውውር ማዕቀፍ ውስጥ በርካታ ጥቅማጥቅሞች ተካተውለታል። ባየር ሙንሽን ለተጫዋቹ ዝውውር ለሊቨርፑል የ75 ሚሊዮን ዩሮ ማዕቀፍ ማቅቡን እና ከመጀመሪያ ስምምነት መድረሳቸው ታውቋል። ይህንኑ ተከትሎ ዲያዝ ከሊቨርፑል የቅድመ ውድድር የወዳጅነት ጫወታዎች ውጭ ሆኖ ቆይቷል። በሌሎች መረጃዎች የጣልያኑ ናፖሊ የማንችስተር ሲቲውን አጥቂ ጋርሌሽን ለመውሰድ ፍላጎት አሳይቷል።
ሊቨርፑል በበኩሉ የኒውካስሉን የጎል አዳኝ አሌክሳንደር ኢሳቅን ምናልባትም ክብረወሰን በሆነ ዋጋ ሊያስፈርመው እንደሚችል የወሬ ጭምጭምታዎች ተሰምተዋል። አሌክሳንደር ኢሳቅ ከሳኡዲው ክለብ አልሂላል የቀረበለትን አጓጊ ረብጣ ዶላር ትቶ ወደ ሊቨርፑል መጓዝ እንደመረጠም ተሰምቷል። ሊቨርፑል በተጨማሪ ወደ ሙንሽን የሚሸኘውን ሊዊስ ዲያዝን ለመተካት አይኑን በሪያል ማድሪዱ አጥቂ ሮድሪጎ ላይ ማሳረፉ ሲገለጽ ማንችስተር ዩናይትድ የአስቶን ቪላውን በረኛ የአርጀንቲናው ኢንተርናሽናል ማርቲኔዝን ለማዘዋወር እንቅስቃሴ መጀመሩ ተሰምቷል።
ታምራት ዲንሳ