የጀርመን ምርጫ 2025
እሑድ፣ የካቲት 16 2017
በጀርመን ዛሬ ምክር ቤታዊ ምርጫ ተካሄደ ። ለ 21ኛው የጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ቡንደስታግ) ምርጫ ድምፃቸውን እንዲሰጡ ከ 59 ሚሊዮን በላይ መራጮች ጥሪ ቀርቦላቸዋል። የምርጫ ጣቢያዎች በሀገሪቱ አቆጣጠር ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት አንስተው እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ ክፍት ነበሩ። ምርጫው በ 65 ሺ የምርጫ ጣቢያዎች የተካሄደ ሲሆን ለዚህም 675 ሺ የሚጠጉ ምርጫ አስፈፃሚዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
አማራጭ ለጀርመን ፓርቲ ከወግ አጥባቂው ሲዲዮ ፓርቲ ጋር ለመጣመር ፍላጎቱን አሳይቷል
አማራጭ ለጀርመን የተባለዉ የቀኝ ፅንፈኛ ፓርቲ (AFD) ከክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት ፓርቲ (CDU) ጋር ጥምር መንግሥት ለመመስረት ፍላጎቱን አሳይቷል። የፓርቲው ተባባሪ መሪ እና የመራሔ መንግሥት እጩ አሊስ ቫይድል በዘንድሮው የጀርመን ምክር ቤት ምርጫ ከፍተኛ የመራጭ ድምፅ ካገኘው ፓርቲ ጋር ጥምር መንግሥት ለመመስረት ፍላጎታቸውን የገለፁት ከጀርመን የቴሌቪዥን ጣቢያ ARD ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ነው። ቫይድል «ለጥምር መንግሥት ድርድር እጃችንን እዘረጋለን» ቢሉም የክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት መራኂተ መንግሥት እጩ ፍሬደሪሽ ሜርዝ ግን ገና በምርጫው ዘመቻ ወቅት ከአማራጭ ለጀርመን ጋር ጥምረት ፍፁም የማይታሰብ መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል። እስካሁን ይፋ በሆነው የጀርመን ምክር ቤት ምርጫ የመጀመሪያ ውጤት ትንበያ መሠረት አማራጭ ለጀርመን 20 በመቶ የሚሆነው የመራጭ ድምፅ አግኝቷል።
ሜርዝ ጀርመንን በአግባቡ መምራት የሚችል ጥምር መንግሥት ለመመስረት « በፍጥነት ስራ እንደሚጀምሩ ተናግረዋል። የጀርመን ወግ አጥባቂ እሕትማማች ፓርቲዎች የክርስቲያን ዴሞክራት ሕብረት (CDU)ና የክርስቲያን ሶሻል ሕብረት (CSU) በጋራ ከ28 በመቶ በላይ ድምጽ አግኝተዋል። መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ የፓርቲያቸውን ሽንፈት ተቀብለዋል።
በጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ቡንደስታግ) መቀመጫ የሚያገኙት የህዝብ ተወካዮች ቁጥር እንደ ከዚህ በፊቱ ከ700 በላይ ሳይሆን ዘንድሮ 630 ነው የሚሆነው። ይህም በስልጣን ላይ የነበረው መንግሥት ባደረገው የሕግ ማሻሻያ ምክንያት ነው።
ከምርጫ በፊት የተካሄዱ መጠይቆች እንደሚጠቁሙት ከሆነ የቀድሞዋ የጀርመን መራሔ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ፓርቲ ወይም የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ እጩ ፍሬድሪሽ ሜርዝ ቀጣዩ የጀርመን መራሔ መንግሥት የመሆናቸው እድል ሰፊ ነው።
በጀርመን ምክር ቤታዊው ምርጫ መካሄድ ከነበረበት ጊዜ አስቀድሞ ዛሬ እንዲካሄድ ምክንያት የሆነው የጀርመን መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ የሚመሩት የሶሻል ዴሞክራቶች፤ አረንጓዴዎቹ እና ነፃ ዲሞክራቶች የተጣመሩበት የሦስትዮሹ ፓርቲዎች መንግሥት ከሦስት ወራት በመፍረሱ ነው። ምርጫው በ 65 ሺ የምርጫ ጣቢያዎች ተካሂዷል። የጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች እንደ ከዚህ በፊቱ ከ700 በላይ ሳይሆን ዘንድሮ 630 ነው የሚሆኑት።
ልደት አበበ
ኂሩት መለሰ