የጀርመን ምርጫ ዉጤት እና የትዉልደ ኢትዮጵያዊዉ ምሁር አስተያየት
ሰኞ፣ የካቲት 17 2017የጀርመን ምርጫ ዉጤት እና የትዉልደ ኢትዮጵያዊዉ ምሁር አስተያየት
በጀርመን ምክር ቤት ምርጫ የክርስትያን ዴሞክራት ህብረት አብላጫ ድምፅን በማግኘት አሸናፊ ሆንዋል። የፓርቲዉ መሪ ፍሬድሪክ ሜርስ ፓርቲያችን አሸንፏል እንኳን ደስ ያላችሁ ሲሉ ንግግር ያሰሙት ፤ ምርጫዉ እንደተጠናቀቀ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ነበር። ፍሬድሪክ ሜርስ ቀጣዬ የጀርመን መራሔ መንግስት ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይሁንና ፓርቲያቸዉ በምርጫ መንግሥት ለመመስረት የሚያበቃዉን አብላጫ ድምፅ ባለማግኘቱ መንግሥት ለመመስረት ተጣማሪ ፓርቲ መፈለግ ይኖርበታል። ፍሬድሪክ ሜርስ እንደተናገሩት ለሁለት በመጣመር መንግሥት ለመመስረት ፍላጎት አላቸዉ። ከ20 በመቶ በላይ ድምጽን በማግኘት በምርጫዉ ሁለተኛ አብላጫ ድምፅን ያገኘዉ ቀኝ ዘመሙ (AFD) በጥምር መንግስት ውስጥ እንደማይካተት ሜርስ አስቀድመዉ አስረግጠዉ ተናግረዉ ነበር። ከምርጫ ዉጤትም በኃላ ይህን አረጋግጠዋል። በወጣቶች እንደተመረጠ የሚነገረዉ ግራ ዘመሙ ፓርቲም በዚህ ምርቻ እድል ቀንቶታል። ጀርመንን ይመራ የነበረው በክርስትያን ሊንዴ የሚመራው FDP ፓርቲ በቂ የመራጭ ድምፅን ባለማግኘቱ ሽንፈት ገጥሞታል። በጀርመን ምክር ቤታዊው ምርጫ መካሄድ ከነበረበት ጊዜ አስቀድሞ ለመካሄድ የበቃዉ የጀርመን መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ የሚመሩት የሶሻል ዴሞክራቶች፤ አረንጓዴዎቹ እና ነፃ ዲሞክራቶች የተጣመሩበት የሦስትዮሹ ፓርቲዎች መንግሥት ከሦስት ወራት በፊት በመፍረሱ እንደሆን የሚታወስ ነዉ። ስለ ምርጫዉ እና ስለዉጤቱ እንዴትነት በበርሊን የኤኮኖሚ እድገት መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የኤኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ፤ ከዶክተር ፈቃዱ በቀለ ጋር አጭር ቃለ ምልልስ አድርገናል። #BTW2025
አዜብ ታደሰ
ዮሃንስ ገብረግዚአብሔር