የዶናልድ ትራምፕ ዲፕሎማሲ በአፍሪቃ
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 25 2017የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ከአፍሪቃ አኅጉር ጋር ያላቸው ግንኙነት ላይ ቀይ መስመር ማስመር የሚፈልጉ ይመስላል ። አገራቸው የበጀት ቅነሳ መርኅ መሠረት ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በመላው ዓለም 30 ግድም ኤምባሲዎችን እና ቆንስላዎችን መዝጋት ይፈልጋሉ ። አብዛኞቹ ከአፍሪቃ ናቸው ። ለንደን በሚገኘው የቻተም ሐውስ የምርምር ተቋም ኃላፊ አሌክስ ቪኔስ አፍሪቃ በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ዝቅተኛ ሥፍራ እንዳላት ገልጠዋል ።
«አምባሳደሮችን መመደብ በትራምፕ አስተዳደር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም ። እስካሁን ድረስ በአፍሪቃ ሊመደቡ የተመረጡት ሦስት አምባሳደሮች ናቸው ። እነሱም፦ ለደቡብ አፍሪቃ፣ ለሞሮኮ እና ቱኒዚያ ናቸው ። በሌሎቹ አገራት ወይ ቀድሞውኑም ያሉት አምባሳደሮች ሥራቸውን ይቀጥላሉ አለያም ከቦታቸው ይነሳሉ ። »
በፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አፍሪቃ ውስጥ ኤምባሲያቸው ሊዘጋ ዝርዝር ውስጥ ከገቡ አገራት መካከል ሌሶቶ፣ ኤርትራ፣ መካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ፣ የኮንጎ ሪፐብሊክ፣ ጋምቢያ እና ደቡብ ሱዳን ይገኙበታል ተብሏል ። ካሜሩን ዱዋላ እና ደቡብ አፍሪቃ ደርባን ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ቆንስላዎቿንም ዩናይትድ ስቴትስ የመዝጋት እቅድ እንዳላት የተገለጠው ቀደም ሲል ነው ። በደቡብ አፍሪቃ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተቋም የአፍሪቃ ሩስያ ፕሮጄክት ኃላፊ ስቴቨን ግሩዝድ አፍሪቃ በአሜሪካ ትኩረት እንዳልተሰጣት ተናግረዋል ።
«አፍሪቃ በትራምፕ የመጀመሪያ ዘመነ-ሥልጣን ብዙም ቦታ አልነበራትም ። አኅጉሪቱን በመስደብ ዘንግተዋት ነበር ። በዘመነ-ሥልጣናቸው በአጠቃላይ አኅጉሪቱን አልጎበኙም ። በአፍሪቃ ጠቃሚ አገራት ውስጥ የሚገኙ የአምባሳደር ቦታዎች ክፍት መሆናቸው ለእኔ ብዙም አልደነቀኝም ። በትራምፕ አስተዳደር ምን ያህል ዝቅተኛ ሥፍራ እንዳላት ነው የሚያሳየው ።»
የዩናይትድ ስቴትስ ወቅታዊ የአምባሳደሮችን ዝርዝር በሚያሳየው ድረ-ገጽ ላይ፦ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ባላቸው እንደ ናይጄሪያ፤ ኢትዮጵያ፣ እና ግብጽ ባሉ አገራትም የወደፊት አምባሳደር የሚመደብ ስለመሆኑ አልተገለጠም ። በአንጻሩ የትራምፕ አስተዳደር በኢንዱስትሪ ጠንካራ ይዞታ ባላት አፍሪቃዊቷ አገር ደቡብ አፍሪቃ አዲስ አምባሳደር ሠይመዋል ። በፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የተሾሙት አምባሳደር ሌዎ ብሬንት ቦዜል ሣልሳዊ ናቸው ። ሹመታቸው በዩናይትድ ስቴትስ ሴኔት መጽደቅ ይጠበቅበታል ። ሰውዬው እጅግ ወግ አጥባቂ እና መገናኛ ብዙኃን ላይ ብርቱ ትችት የሚሰነዝሩ ከመሆናቸው አንጻር በአምባሳደርነት መሾማቸው ለደቡብ አፍሪቃ «ፈተና» መሆኑን ስቴቨን ግሩዝድ አክለው ተናግረዋል ።
ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በጥር ወር መንበረ-ሥልጣኑን ከያዙበት ጊዜ አንስቶ በርካታ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ የሠራተኞች ቅነሳ እና አንዳንድ ክፍሎችን የማጠፍ ወይም የመዘጋት ርምጃዎችን ወስደዋል ። በኤክስ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር የቀድውሞ ትዊተር ባለቤት የዓለማችን ቢሊዬነር ኤለም መስክ በሚመራው አዲስ መሥሪያ ቤት ርምጃ በርካቶች ሥራቸውን እንዲያቆሙ ተገድደዋል ። የመንግሥት የሥራ ብቃት ክፍል በእንግሊዝኛ ምኅጻሩ (DOGE) የተሰኘው ክፍል ከፍተኛ የሠራተኛ ቅነሳ ርምጃ ወስዷል ።
ከዚያም ባሻገር የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የአገሪቱ ኤኮኖሚ ላይ ጫና ከፈጠሩ ጉዳዮች መካከል በተለያዩ አገራት የሚገኙ ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎች እንደሆኑ ይናገራል ። የትራምፕ አስተዳደር ከአገራት ጋር በተናጠል የሁለትዮሽ ትብብራ ማድረጉ ላይ ማተኮሩንም በፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪቃ ማእከል የአሜሪካ ጥናት ኃላፊ ክሪስቶፈር ኢዚኬ አብራርተዋል ።
«የትራምፕ አስተዳደር ከአፍሪቃ ጋር ባለው ግንኙነት በጋራ ትብብር አያምንም ። በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው በተናጠል ከአገራት ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት ማድረግ ነበር ምርጫቸው ። »
የፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ አጥኚው እንደሚሉት ከሆነ፦ የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከአብዛኛ የአፍሪቃ አገራት ጋር ግንኙነቱ እንደቀድሞ አይሆንም ። ዶናልድ ትራምፕ በተለይ ግን ከደቡብ አፍሪቃ፣ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና ምናልባትም ከናይጄሪያ ጋር የሁለትዮሽ ትብብር የማድረግ ፍላጎት ይኖራቸው ይሆናል እንደ አጥኚው ግምት ። ከእነዚህ አገራት ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማድረግ የሚሹትም አገራቱ ካላቸው እና ዩናይትድ ስቴትስ ከሚያስፈልጋት የተፈጥሮ ማዕድናት ጋር ይያያዛል ብለዋል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ/ ማርቲና ሽቪኮቭስኪ
ፀሐይ ጫኔ