የድሬደዋ አስተዳደር ፖሊስ ከአራት መቶ ኪሎ ግራም በላይ አደንዛዥ እፅ አስወገደ
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 8 2017የድሬደዋ አስተዳደር ፖሊስ በተለያዩ ጊዜያት ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር ከተገናኙ ተጠርጣሪዎች የያዘውን ከአራት መቶ ኪሎ ግራም በላይ አደንዛዥ እፅ አስወግዷል። ከግለሰቦች ተይዞ በቃጠሎ እንዲወገድ ከተደረገው መካከል በአብዛኛው ካናቢስ የተባለው አደንዛዥ ዕፅ እንደሚገኝበት ተገልጧል ። ከአጎራባች እና ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ወደ ድሬደዋ የሚጓጓዘው ዕፅ በተደራጀ ቅብብሎሽ እስከ ጎረቤት ሀገር የሚላክ መሆኑ ፖሊስ አስታውቋል።
በድሬደዋ አስተዳደር ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ዲቪዥን ኃላፊ ኢንስፔክተር ተመስገን ተሰማ እንደገለፁት በቃጠሉ እንዲወገድ የተደረገው አደንዛዥ ዕፅ ከተለያዩ አካባቢዎች በቅብብሎሽ ወደ ከተማው ገብቶ ከተለያዩ አካላት ላይ በቁጥጥር ስር የዋለ ነው።
ዲቪዥን ኃላፊው በከተማዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደነበር የሚገለፀው ዕፅ በከተማዋ በሚገኘው የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎች አካባቢዎች ፖሊስ እያደረገ ባለው ቁጥጥር መሻሻል ታይቶበታል ባይ ናቸው።
በፍትህ ሚንስቴር የድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች አስተባባሪ አቶ ኃይለ አምላክ አወቀ በቃጠሎ እንዲወገድ ከተደረገው ሀሺሽ ጋር በተያያዘ የተያዙ ሰዎች እስከ አምስት አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት የተቀጡበት መሆኑን አስረድተዋል።
አፍሪቃ እና የአደንዛዥ እፅ ዝዉዉር
በቃጠሎ ማስወገድ ላይ በታዛቢነት የተገኙት አቶ ዑመር አብዶሽ በፖሊስ የተሰራውን ስራ በአድናቆት ገልፀዋል። በአደንዛዥ ዕፅ ማስወገድ ስራ ላይ ከተለያዪ ባለድርሻ ተቋማት የተውጣጡ ታዛቢዎች ተገኝተዋል።
መሳይ ተክሉ
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር