ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ የተሰኘ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ተመሰረተ
በእነ አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራ ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ የተሰኘ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግዚያዊ የምዝገባ ፍቃድ አገኘ። በሁለት ተከፍለው ለረዥም ግዜ ሲወዛገቡ ከነበሩት ከህወሓት ቡድኖች መካከል የነበረዉ በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ክንፍ አስቀድሞ ሲገልፀው እንደነበረ አዲስ ፓርቲ በመመስረት፥ በሌላ መንገድ ወደ ትግራይ ፖለቲካ መቀላቀሉ ተመልክቷል። ህወሓት የማሻሻል እና ማዳን ጉዳይ የማይቻልበት ሁኔታ ሲደርስ በአዲስ ፓርቲ ለመምጣት መቻላቸው ከአዲሱ ፓርቲ ምስረታ አስተባባሪዎች መካከል የሆኑት አቶ ረዳኢ ሓላፎም ለዶቼቬለ ገልፀዋል። ከዚህ በተጨማሪ ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ለረዥም ግዜ በህወሓት ላይ በተለይም ከምዕራባውያን ይቀርብ የነበረ ትችትን የሚመልስ ጭምር ነው የተባለ ሲሆን በቅርቡ መስራች ጉባኤውን እንደሚያደርግም ተገልጿል።
ጀርመን ያቀረባበትን ክስ መሠረተ ቢስ ስትል አጣጣለች
ጀርመን በዩጋንዳ በሚገኙት አምባሳደሯ ላይ ያቀረባበትን ክስ መሠረተ ቢስ ስትል አጣጣለች። ይህ እርምጃ የተሰማዉ በካምፓላ የጀርመን አምባሳደር “በአስፈሪ ተግባራት” ውስጥ እጃቸው እንዳለበት የዩጋንዳዉ መንግሥት ትናንት መክሰሱ ከተሰማ በኋላ ነው። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በበኩላቸው ክሱ “የማይረባ እና ምንም ጥቅም የሌለው ” ብለዉታል። ሚኒስቴር መስርያ ቤቱ ክሱን “አይቀበለዉም“ ሲሉም ቃል አቀባዩ አክለዋል። ይሁንና ቃል አቀባዩ ስለ ክሱ ምንነት ተጨማሪ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በሁለቱ ሀገራት መካከል መደበኛ የሆነ ወታደራዊ ትብብር አለመኖሩን ግን አጽኖት ሰተዋል። ዩጋንዳ ወታደሮቿ በሶማሊያ በአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ውስጥ ይገኛሉ። ይህ ኃይል በከፊል ድጋፍ የሚያገኘዉ ጀርመን አባል ሃገር በሆነችበት በአውሮጳ ህብረት ነዉ።
የኮሌራ ወረርሽኝ በጦርነት በተመሰቃቀለችዉ ሱዳን በከፍተኛ ፍጥነት ይዛመታል
በጦርነት በተመሰቃቀለችዉ ሀገር ሱዳን በኮሌራ በሽታ የተያዘዉ ሰዉ ቁጥር መጨመሩን የሱዳን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዛሬ አስታወቀ። የፈረንሳዩ ዜና አገልግሎት እንደዘገበዉ በሱዳን በአንድ ሳምንት ውስጥ 2,700 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ተገኝተዋል። 172 ሰዎች ደግሞ በኮሌራ በሽታ ሞተዋል። ሚኒስትር መስርያ ቤቱ ባለፈዉ ሳምንት ሃሙስ ባወጣዉ መግለጫ 2300 ሰዎች በኮሌራ ወረርሽኝ መያዛቸዉን እና 51 ሰዎች ደግሞ ፤ በበሽታዉ መሞታቸዉን አሳዉቆ ነበር። የሱዳን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ 90 በመቶው የኮሌራ በሽታ የተመዘገበበት አካባቢ መዲና ካርቱም ነዉ። ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በካርቱም የውኃ እና የመብራት አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ ተስተጓጉሏል፣ ይህ የዉኃ አቅርቦት እና የኤሌትሪክ መጥፋት በከፍተኛ ሁኔታ ሲከሰት በሱዳን የእርስ በእርስ በርስ ጦርነት ከጀመረ ከመጋቢት 2023 ዓመት ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ነዉ። ይህ በእንዲህ እንዳለ የኮሌራ ወረርሽኝ በደቡባዊ እና በሰሜናዊ ሱዳን መከሰቱም ታዉቋል። በከፍተኛ ፍጥነት የሚዛመተዉ የኮሌራ ወረርሽኝ በጦርነት በተመሰቃቀለችዉ ሱዳን በከፍተኛ ፍጥነት ይዛመታል የሚል ስጋት አሳድሯል።
ጀርመን እና የሌሎች ቁልፍ ምዕራባዉያን ሃገራት ደጋፊዎች ለየዩክሪን የዞር መሳርያ
ጀርመን እና ሌሎች ቁልፍ ምዕራባዉያን የዩክሬን ደጋፊዎች ዩክሬን ሩስያን ለመዉጋት ለኪይቭ የሚልኩትን የጦር መሳርያ ገደብ እንደሚያነሱ አስታወቁ። ሩስያ በበኩልዋ እርምጃዉን አደገኛ ማለትዋ ተሰምቷል። የጀርመኑ መራሔ መንግስት ፍሪድሪክ ሜርስ ጀርመን፤ ከፈረንሳይ፤ እንግሊዝ እና አሜሪካ ጋር በመሆን ወደ ዩክሬን በምትልከዉ የጦር መሳሪያዎች ገደብ መነሳቱን አስታውቀዋል። መራሔ መንግስት ፍሪድሪክ ሜርስ WDR Europaforum 2025 በተሰኘ ዲጂታል ጉባኤ ላይ ትናንት እንደተናገሩት “ከእንግዲህ ለዩክሬን በሚላኩ የጦር መሳሪያዎች ላይ ምንም አይነት ገደብ አይኖርም። ይህ በእኛ፤ በብሪታንያ፤ በፈረንሳይ እንዲሁም በአሜሪካዉያንም የተደረሰ ዉሳኔ ነዉ ሲሉ አክለዋል። ይህ ማለት ዩክሬን አሁን እራሷን መከላከል ትችላለች ያሉት የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ዩክሬይን እስከዛሬ አነስተኛ ጥቃት ከመጣል በቀር ያልፈፀመችዉ፤ ለምሳሌ በሩሲያ ወታደራዊ ቦታዎችን ማጥቃት ትችላለች ሲሉ ሜርስ ገልፀዋል። የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ፍሪድሪክ ሜርስ በ X ገጻቸዉ ባስቀመጡት ሌላ የጽሑፍ መረጃ «ዩክሬንን በቀጣይነት ለመደገፍ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን» ሲሉ አቋማቸዉን ገልፀዋል።
የጀርመኑ መራሔ መንግሥት በጋዛ እየፈፀመች ድርጊት ወቀሱ
የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ፍሬድሪክ ሜርስ እስራኤል በጋዛ እየፈፀመች ያለዉ ድርጊት «ትክክል ያልሆነ» ሲሉ ወቀሱ። እስራኤል በጋዛ እየፈፀመች ስላለዉ ወታደራዊ ዘመቻ የጀርመኑ ቻንስለር የሰጡት ህዝባዊ ወቀሳ ያልተለመደ መሆኑም ተመልክቷል። መራሔ መንግሥቱ ከጀርመን መገናኛ ብዙኃን WDR ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አሁን ያለው የእስራኤል ጥቃት ደረጃ ከሃማስ ጋር የሚደረግ ውጊያ ሊሆን አይችልም፤ እስራኤል በዚህ ድርጊት ምን ለማግኘት እየሞከረች እንደሆን አልገባኝም" ብለዋል።
«በሳምንቱ መጨረሻ በጋዛ ሰርጥ የህፃናት መኖሪያ ቤት ወይም መዋለ ህፃናት ላይ ጥቃት ተፈፅሟል። ይህ የሰው ልጅ አሳዛኝ ታሪክ እና ፖለቲካዊ ውድመት ነው። ከእስራኤል መንግስት ጋር በጣም የቅርብ ግንኙነት አለን። እኔም በዚህ ሳምንት ከኔታንያሁ ጋር እናገራለሁ። ይህን የምናደርገው በዝግ በሮች ጀርባ ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት ሁለት ጊዜ አግንቼው ነበር። በዝያን ወቅት ነገሮች ከመጠን በላይ እንዳታደርግ ብዬ በዝግ በር ዉይይት ነግሪዋለሁ። አሁን የእስራኤል ጦር በጋዛ ሰርጥ እየፈፀመዉ ስላለው ነገር በጥቂቱ በግልፅ እናገራለሁ። እውነቱን ለመናገር፣ ለምን በዚህ መንገድ ሰላማዊውን ህዝብ እንደሚጎዱ አልገባኝም። ከቅርብ ቀናት ወዲህ ሁኔታዉ እየጨመረ መጥቷል፣ ይህ ደግሞ ከሃማስ ሽብርተኝነት ጋር የሚደረግ ትግል ነው ሊባል አይችልም። የኔ እይታ ይህ ነው።» በዚህ ሳምንት ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር በቀጥታ ለመነጋገር ማቀዳቸዉን የተናገሩት መራሔ መንግሥት ፍሬድሪክ ሜርስ እስራኤል ከጥቃት እንድትታቀብም አሳስበዋል። ጀርመን በእስራኤል ላይ የወሰደችውን ጥንቃቄ የተሞላበት አቋም መቀበላቸዉን የተናገሩት ሜርስ፤ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ህግ ጥሰቶች ግን መነገር ይኖርባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል። ይህ የጀርመኑ ቻንስለር አስተያየት የተሰማዉ እስራኤል በሰሜናዊ ጋዛ በሚገኝ መጠለያ ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ የጀርመኑ የገንዘብ ሚኒስትር ፤ መራሔ መንግሥት ሜርስ በእስራኤል መንግስት ላይ ያቀረቡትን ትችት እንደሚደግፉ ተናግረዋል። በርሊን የሚገኘዉ የጀርመን መንግሥት፤ እስራኤል በጋዛ ላይ የምታካሂደዉን ጥቃት አጠናክራ በቀጠለችበት በዚህ ወቅት የበርሊኑ መንግሥት ፖለቲካዊ ጫናውን ለመጨመር እንዳሰበ የጀርመኑ የገንዘብ ሚኒስትር ላርስ ክሊንባይል ተናግረዋል።
ፊንላንድ የሩሲያ ወታደራዊ አውሮፕላኖች አየር ክልሌን ጥሰዋል በሚል የሩሲያን አምባሳደር ጠራች
ባለፈው ሳምንት ሁለት የሩሲያ ወታደራዊ አውሮፕላኖች የፊንላንድን የአየር ክልል ጥሰዋል ከተባሉ በኋላ በፊንላንድ የሩሲያን አምባሳደር ለጥያቄ ጠራች። ሄልሲንኪ የኔቶ ውህደትን እያጠናከረ ባለበት በዚህ ወቅት ይህ ክስተት ውጥረቱን ከፍ እንዳደረገዉ አስግቷል። የሩሲያ ወታደራዊ አውሮፕላኖች የአየር ክልል መጣሳቸዉ የተጠረጠረው ከፊላንድ መዲና ሄልሲንኪ በስተምስራቅ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የፖርቮ የባህር ዳርቻ አካባቢ መሆኑን እና የፊንላንድ ባለስልጣናት ምርመራ ላይ መሆናቸዉ ተመልክቷል። የፊላንድ መከላከያ ሚኒስቴር ስለድርጊቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የዘገበዉ ባለፈዉ አርብ መሆኑ ይታወሳል። ፊንላንድ በጎርጎረሳዉያኑ 2023 ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች እና ጥቃት ከጀመረች በኋላ የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ሃገራት «ኔቶን» መቀላቀልዋ ይታወቃል። ሰሜናዊ አዉሮጳዊት ሃገር ፊላንድ ከሩሲያ ጋር 1,340 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለዉ ድንበርን ትጋራለች። ፊላንድ ኔቶን ከተቀላቀለች ወዲህ ሄልሲንኪ የሚገኘዉ መንግሥት የፀጥታ ስጋት እየጨመረ እንደሚሄድ ማስጠንቀቁ እና የመከላከያ ዝግጁነቱን ለማሳደግ ቃል መግባቱ ይታወቃል።
ብሪታንያ የሊቨርፑል የካስ ክለብ እና የመኪና ግጭት
የብሪታንያ ፖሊስ የሊቨርፑል እግር ኳስ ክለብ የፕሪምየር ሊግ ድልን እያከበሩ ባሉ ሰዎች ላይ መኪና ነድቶ በርካታ ሰዎችን የጨፈላለቀ ግለሰብን ትናንት ምሽት በቁጥጥር ስር አዋለ። ፖሊስ እንዳለዉ አንድ የ53 ዓመት ነጭ እንግሊዛዊ በሊቨርፑል አካባቢ በቁጥጥር ስር ዉሏል። ፖሊስ አክሎ ጥቃቱ ግን ከሽብርተኝነት ጋር የተያያዘ አይመስልም ፤ ሰዎችን ለመግደል የተነሳሳ ሲል መጠርጠሩን ገልጿል ሲል ገልጿል። የተጎዱትን ያነሳዉ የአምቡላንስ አገልግሎት ቢያንስ 27 ሰዎች ሆስፒታል መግባታቸዉን እና ከነዚህ መካከል ሁለት ሰዎች ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸዉ አስታዉቋል። በጉዳቱ ከቆሰሉ መካከል አራት ህጻናት እንደሚገኙበት እና አንድ ሕጻን «ከባድ ነው » የተባለ ጉዳት እንደደረሰበት ተመልክቷል። ሆስፒታል ከገቡት በተጨማሪ 20 ሰዎች የመኪና ግጭት በደረሰበት አካባቢ የመጀመርያ ህክምና ተደርጎላቸዋል። በሊቨርፑሉ የመኪና ጥቃት መደንገጣቸዉን የገለፁት የብሪታኒያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ኬይር ስታርመር ለጉዳተኞች የመጀመሪያ እርዳታ የሰጡትን ሁሉ አመስግነዋል። የሊቨርፑል እግርኳስ ክለብ የውድድር ዘመን ድሉን ለማክበር በከተማው ውስጥ ጣርያዉ ክፍት በሆነ አዉቶቡስ የደስታ ፈንጠዝያ ሰልፍ ሲያካሂድ፤ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ህዝብ ተገኝቶ ነበር።