ጀርመን፤ ፍሬድሪሽ ሜርዝ የጀርመን 10ኛዉ መራሄ መንግሥት ሆነዉ ተመረጡ
የክርስቲያን ዴሞክራቶች ኅብረት ፓርቲ መሪ ፍሪድሬሽ ሜርስ አዲሱ የጀርመን መራኄ መንግሥት ሆነዉ ተመርጡ። ሜርስ ምርጫዉን እንዳሸነፉ ሥልጣኑን በይፋ ለመቀበል ወደ ጀርመኑ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ቫልተር ቤተመንግስት ቤሊቪዉ አቅንተዋል። ከቀትር በፊት በተካሄደዉ ምርጫ ሜርስ አብላጫ ድምፅ ባለማግኘታቸዉ ምርጫዉ ዛሬ ከቀትር በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ከተካሄደ በኋላ ነበር 10ኛዉ የጀርመን መራሄ መንግሥት ሆነዉ ፍሬድሪሽ ሜርስ የተመረጡት። የጀርመን ፓርላማ ቡንደስታግ ፕሬዚዳንት ዩልያ ክሎክነር የምርጫዉን ዉጤት እንዲህ ነበር ያወጁት።
«አሁን የምርጫውን ውጤት ዐሳውቃለሁ፡ የአባላት ብዛት፡ 613፣ የተሰጠዉ ድምፅ 618 ነዉ። በምርጫዉ ዋጋ ያጣው ድምፅ ሦስት ሲሆን። የይሁንታ ድምፅ የሰጡት 325 አባላት ናቸዉ። '289 መራጮች ድምፅ የነፈጉ ሲሆን አንድ ድምፀ ታቅቦ አለ። የፓርላማ አባሉ ፍሬድሪክ ሜርዝ በመሰረታዊ ሕግ አንቀፅ 63 አንቀፅ 2 መሰረት የሚፈለገውን አብላጫ ድምፅ አግኝተው የፌዴራል ጀርመን መራኄ መንግሥት ሁነው ዛሬ ተመርጠዋል።»
ሜርስ በሁለተኛው ዙር ምርጫ በመራኄ መንግስትነት የተመረጡት ከምክር ቤቱ አባላት የ325ቱን ድጋፍ አግኝተው ነው። ዛሬ ጠዋት በተካሄደው የመጀመሪያው ዙር ምርጫ ሜርስ አብላጫ ድምጽ ባለማግኘታቸው ነበር ከሰዓት በኋላ ሁለተኛ ዙር ምርጫ የተካሄደው። በጠዋቱ ምርጫ ሜርስ 310 የድጋፍ ድምጽ ብቻ ነበር ያገኙት። ሜርስ መራኄ መንግሥት ለመሆን ከ630 የጀርመን ምክር ቤት አባላት ቢያንስ የ316ቱን ድምጽ ማግኘት ነበረባቸው። በጀርመን የመራኄ መንግስት ምርጫ ይህን ዓይነቱ ክስተት ሲፈጠር የዛሬው የመጀመሪያው ነው። የምርቻዉ ዉጤት ከተነገረ በኋላ የጀርመን ፓርላማ ቡንደስታግ ፕሬዚዳንት ዩልያ ክሎክነር ሜርዝን ምርጫዉን ይቀበሉ እንደሆን ጠይቀዋቸዉ ነበር። "ሚስተር ሜርዝ ምርጫዉን ይቀበላሉ ስል መጠየቅ እወዳለሁ። « ዉድ ፕሬዚዳንት ለተሰጠኝ የመተማመኛ ድምፅ አመሰግናለሁ። ምርጫዉን ተቀብያለሁ።
ትናንት በይፋ በክብር የተሸኙትን የቀድሞዉን መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልስን የሚተካው መራኄ መንግስት በጀርመን መሠረታዊ ሕግ መሠረት የጀርመን የሕዝብ እንደራሴዎችን አብላጫ ድምፅ ማግኘት አለበት። ጥምር መንግሥት ለመመስረት የተስማሙት ወግ አጥባቂ ፓርቲዎች እህትማማቾቹ የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረትና የመሃል ግራዉ የሶሻል ዴሞክራቶች ኅብረት በምክር ቤቱ ያላቸው ድምጽ በአጠቃላይ 328 ነው። ይሁንና ሜርስ በዛሬ ጠዋቱ ምርጫ የ310 ሩን ድምፅ ሲያገኙ 18 አባላት ግን ሜርስን አልመረጡም ነበር። የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረትና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርታዎች እንዲሁም የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ በሁለተኛው ዙር ድምጽ አሰጣጥ ፍሪድሪሽ ሜርስን ለመደገፍ መወሰናቸውን አስታውቀዉ ነበር። በዚህ ምርጫ በእንግድነት ከተገኙት የጀርመን የቀድሞ መሪዎች መካከል የቀድሞዋ መራኄ መንግሥት አንጌል ሜርክል ይገኙበታል። የምርጫዉን ዉጤት ተከትሎ የዩክሬይኑ ፕሬዚዳንት ቮላድሚር ዜሌንስኪን ጨምሮ የተለያዩ የዓለም ሃገራት መንግሥታት እና ተጠሪዎች የደስታ መግለጫቸዉን እያያስተላለፉ ነዉ።
ኢትዮጵያ፤ ከመተማ ጎንደር ያለው መንገድ ከተዘጋ አንድ ወር ሆነዉ
በአማራ ክልል ከመተማ ጎንደር ያለው መንገድ ከተዘጋ አንድ ወር በማስቆጠሩ በአካባቢው ነዋሪዎች የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ጫና ማሳደሩን ነዋሪዎች ተናገሩ፣ የምዕራብ ጎንደር አሰተዳደር በበኩሉ በመንገዱ በሚመላለሱ መኪኖችና ተሳፋሪዎች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ያላቸው ኃይሎችን ከአካባቢው ለማስወገድ መንገዱ ለጊዜው አገልግሎት ባይሰጥም በቅርቡ አገልግሎቱ ይመለሳል ብሏል፡፡ መንገዱ ከመጋቢት 2017 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ ባለመሆኑ የመተማና ጭልጋ ወረዳ ነዋሪዎች ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ተዳርገዋል፡፡
ከ160 ኪሜ የማይበልጠው የጎንደር መተማ መንገድ በመቋረጡ ለህክምናና ሌሎቸ አስቸኳይ ስራዎች በአማራጭ፤ መንገድ 5 ወረዳዎን በማቆራረጥና እስከ 1500 ብር የትራንስፖርት ወጪ በመክፈል ለመጓዝ የሚገደዱ ሠዎች እንዳሉም አስተያይት ሰጪዎች አስረድተዋል ሲል የዶቼ ቬለዉ ዓለምነዉ መኮንን ዘግቧል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አወቀ አስፍሬ መንግስት በይፋ መንገዱን እንዳልዘጋው ተናግረዋል። ሆኖም ነዋሪው በመንገዱ ላይ ባለው ሥጋት ምክንያት አገልግሎቱ መቋረጡን አመልክተዋል፡፡ መንግዱን መኪና እያስቆሙ ከሚዘርፉ ኃይሎች የማፅዳት ሥራ እየተሠራ በመሆኑ በቅርብ ቀን መንገዱ ወደ አገልግሎት ይመለሳል ብለዋል፡፡
ሱዳን ፤ ፖርት ሱዳን ላይ የድሮን ጥቃት ደረሰ
ፖርት ሱዳን ላይ በደረሰ የሰዉ አልባ አዉሮፕላን ማለትም የድሮን ጥቃት አዉሮፕላን ጣብያ እና የከተማዋ የኤልትሪክ ማሰራጫ መመታቱ ተመለከተ። አካባቢዉ ላይ የሚገኙ ባለሥልጣናት ለፈረንሳይ የዜና አገልግሎት አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደገለፁት፤ የመንግሥት በጦር ሰራዊት መቀመጫ የሆነችዉ ከተማ በተከታታይ ጥቃት ሲደርስባት ዛሬ ለሦስተኛ ቀን ነዉ። በሱዳን ጦር ሰፈር ላይ ያነጣጠረው የዛሬዉ ጥቃት የመጣው የሱዳን ዋነኛ የነዳጅ ማከማቻ ከተመታ ከአንድ ቀን በኋላ መሆኑ ነዉ። ለሁለት ዓመት በዘለቀዉ ጦርነት፤ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ የተፈናቀሉ ሰዎች አስተማማኝ መጠለያ ተደርጎ ይታሰብ የነበረው ፖርት ሱዳን ከተማ ባለፈዉ እሁድ በደቡባዊ ምሥራቅ ከፍተኛ ቃጠሎ አስከትሎ እንደነበር ይታወቃል። ከካርቱም ወጣ ብሎ 650 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኘዉ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ለጥቃቱ ኃላፊነቱን አልወሰደም። የሱዳን ጦርነት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድሏል፣ 13 ሚሊዮን ሰዎችን ደግሞ ከቤት ንብረታቸዉ አፈናቅሏል። በዚህም ሱዳን በዓለም ላይ ከሚገኙ ሃገራት መካከል ከፍተኛ ቁጥር ረሃብተኛ ተፈናቃዮች የሚገኙባት ሃገር ሆናለች። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዛሬ ይፋ እንዳደረገዉ ከሆነ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው የሱዳን ስተፈናቃዮች ከምዕራብ ዳርፈር ክልል ወደ ጎረቤት ቻድ እየሸሹ ነው። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ወደ 20,000 የሚጠጉ የሱዳን ነዋሪዎች ቻድ ገብተዋል።
የተመድ፤ በዓለማችን የእርዳታ መቀነስ እድገት እንዲያሽቆለቁል ምክንያት ሆኗል
ለሃገራት የሚሰጠዉ ሰብዓዊ ርዳታ መቀነስ በዓለም አቀፍ ደረጃ እድገት እንዲቀዛቀዝ ምክንያት ሆኗል ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (HDI) ዛሬ ማክሰኞ ይፋ ባደረገው ዘገባ መሠረት ከባለፈዉ የጎርጎረሳዉያን 2024 ዓመት ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታየዉ የሰብዓዊ እርዳታ እየቀነሰ ነዉ። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የወሰደዉ ርዳታን የመቀነስ ርምጃ በማደግ ላይ ባሉ አገራት ላይ ከፍተኛ ተፅኖ ይኖረዋል ሲልም ድርጅቱ አስጠንቅቋል። በዘገባዉ መሰረት በዓለማችን የሰብዓዊ ልማት እርዳታን በማድረግ አይስላንድ በቀዳሚነት የተቀመጠች አገር ስትሆን ጀርመን በአምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ያወጣው ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያሳየው ከሆነ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ በጎርጎረሳዉያኑ 2023 የሚደርሰዉ እርዳታ እየጨመረ መሆኑ ቢታይም በአሁኑ ወቅት ግን እርዳታ እየቀነሰ ነዉ። ይህ "አስደንጋጭ" የሆነ ርዳታ መቀነስ ጉዳይ የሰው ልጅ እድገትን ለአሥርተ ዓመታት እንዲያሽቆለቆል የሚያደርግ፣ ዓለማችን አስተማማኝነቱ እንዲቀንስ፤ ይበልጥ መከፋፈል እና የኢኮኖሚና ሥነ ምህዳራዊ ቀውስ ይበልጥ ተጋላጭ እንድንሆን የሚዳርግ" ነዉ ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ኃላፊ አኪም ስታይነር አስጠንቅቀዋል። በዩናይትድ ስቴትስ በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሚመራው አስተዳደርን ጨምሮ በዓለምአቀፍ ደረጃ የሚሰጠዉ እርዳታ መቀነስ ጉዳቱን ይበልጥ ከባድ ከማድረግ በቀር የሚፈይደዉ አንዳች ነገር ይኖርም ሲሉ ስታይነር አክለዋል።
አሜሪካ፤ የሰብዓዊ እርዳታ እገዳዎች የዩናይትድ ስቴትስ ሕግን ሊጥሱ እንደሚችሉ መነገሩ
የእስራኤል እና ሌሎች የዉጭ መንግሥታት በሰብዓዊ ርዳታ አቅርቦት ላይ የሚያካሂዱት ቁጥጥር እና እገዳ የዩናይትድ ስቴትስን ሕግ መጣስ አለመጣሱን የአሜሪካ ምክር ቤት እንዲመረምር እንደሚፈልጉ የዩናይትድ ስቴትስ ሴናተሮች በደብዳቤ ጠየቁ። ሮይተርስ አየሁት ባለዉ እና በስድስት ሴናተሮች ለሂሳብ ጉዳይ አጣሪ ጀነራል ለሆኑት ገኔ ዶዳሮ በጻፉት ደብዳቤ፤ የሰብዓዊ ርዳታዎች አቅርቦትን የሚመለከተዉ የዩናይትድ ስቴትስ ሕግ አተገባበር በገልተኝነት እንዲጣራ ጠይቀዋል። በኢትዮጵያ ሱዳን፣ ዩክሬን፣ በርማ፣ ሶሪያ፣ በናጎርኖ-ካራባህ እና ጋዛ እንደ ምግብ፤ የህክምና መሣሪያዎች፤ የንጹህ መጠጥ ዉኃ ዝርጋታ ስርዓት እና ሌሎች ሕይወት አድን ቁሳቁሶችን የመሳሰሉ ወሳኝ የሰብአዊ ርዳታዎች፤ በመንግሥትም ሆነ በሀገር ውስጥ ባልሆኑ ተዋናዮች፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፣ እንዳይገቡ መሆናቸዉ አልያም መታገዳቸዉ በደብዳቤ ዉስጥ ተጠቅሷል። የሰብዓዊ እርዳታን በተመለከተ ከቅርብ ጊዜ በጋዛ ያለዉ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑንም ተመልክቷል። እስራኤል ከጎርጎረሳዉያኑ ከመጋቢት 2 እለት ጀምሮ ወደ ጋዛ ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይገባ ካገደች ወዲህ እና ለ2.3 ሚሊዮን የፍልስጤም ነዋሪዎች እርዳታ ከተቋረጠ በኋላ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የፍልስጤም ተወካዮች በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት እስራኤልን የዓለም አቀፉን ሕግ በመጣስ መክሰሳቸዉ ይታወቃል።