የእስራኤል ኢራን ግጭት እና የደቀነው ብርቱ ስጋት
ሰኞ፣ ሰኔ 9 2017የተፈራው ጊዜ ደረሰ
ያ የተፈራው ፤ ያ እንዳይመጣ የተሰጋው ቀንና ሰዓት ደረሰ። ለአራት አስርት ዓመታት የዘለቀው የከፋ ጠላትነት ገነፈለ ፤ በመጨረሻም እስራኤል ክብሪቱን ለኮሰች ፤ የኢራን እስራኤል የአየር ላይ ጦርነት የእሳት ኳስ እያወራወረ አራተኛውን ቀን አስቆጠረ ፤ ሀገራቱ በታሪካቸው አይተው ያማያውቁትን ውድመት እና የሰብአዊ ቀውስ እያስተናገዱ ነው ። የዓለምን ቀልብ ሰቅዞ የያዘው
የመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ መጣፊያ ይገኝለት ይሆን ?
ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ለአርብ አጥቢያ እስራኤል ኢራን ላይ ወታደራዊ ጥቃት መፈጸሟ ሲሰማ የሁለቱ ሃገራት ፍጥጫ ጫፍ ደርሶ መፈንዳቱን ለመገመት በርግጥ የጦር አዋቂ እና ተመራማሪ መሆን አይጠበቅም ። ይልቁኑ በዚያ ውድቅት ሌሊት የእስራኤል የተጠና የአየር ጥቃት በርካታ እና ቁልፍ የኢራን ወታደራዊ አዛዦች እና የኒኩሊየር ተመራማሪዎችን በአንድ ጊዜ የመግደሉ ዜና መሰማቱ የከፋ ሁኔታ ተከትሎ እየመጣ ስለመሆኑ ግን አመላካች ነበር ።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ዛቻ
እስራኤል ዘመን ባፈራቸው አሜሪካ ሰራሽ የጦር አውሮፕላኖች በኢራን ሰማይ ላይ እየተመላለሰች የኢራንን የኒኩልየር ማብላያ እና የሚሳኤል ማምረቻ እንዲሁም ማከማቻ ናቸው ያለቻቸውን ተቋማት ኢላማ ማድረጓን አስታውቃለች። በተጨማሪም መዲናዋ ቴህራን የሚገኘውን የአየር መቃወሚያ ስረዓትን ጨምሮ በምዕራብ እና በደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ማጣሪያ እና ማከማቻ ስፍራዎችን አጥቅታለች። የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔትያናሁ «የሚነሳው አንበሳ» ባሉት ወታደራዊ ዘመቻቸው በኢራን ላይ ካደረሱት ጥቃት ባሻገር መጭው ጊዜ የከፋ እንደሚሆን ተናግረዋል።
«ባለፉት 24 ሰዓታት ከፍተኛ የጦር አዛዦችን ፣ ዋና የኒኩልየር ሳይንትስቶችን ፣ ቁልፍ የኑኩልየር ማብላያ ጣቢያዎች እንዲሁም በርካታ የባለስቲክ ሚሳኤል ማምረቻ እና ማከማቻ ስፍራዎችን አጥቅተናል ፤ ከዚህ የባሰው እየመጣም ነው። »
እስራኤል እና ኢራን አንዳቸው በሌላቸው ላይ በፈጸሟቸው ጥቃቶች የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ጨመረ
የኢራኑ መንፈሳዊ መሪ ዛቻ
ኢራን በእስራኤል ለደረሰባት የአየር ጥቃት እና ለተገደሉባት ከፍተኛ ወታደራዊ የጦር አዛዦች ምትክ አዛዦች ለመሾም ሰዓታት ብቻ ነበር የወሰደባት ። ለደረሰባት ጥቃትም በወሰደችው የአጸፋ ርምጃ ፈጣን እና ተከታታይ የድሮን እና ሚሳኤል ጥቃቶች እስራኤል ከእስከዛሬው ሁሉ የከፋ ጉዳት እንዳደረሰባት ተዘግቧል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስም ሃያ ያህል ሰዎች ሲገደሉ ፤ ሌሎች ከሶስት መቶ የሚልቁት ደግሞ መቁሰላቸው ተዘግቧል። ቴል አቪብ፤ አይፋ እና ሌሎች በሰሜናዊ እስራኤል የሚገኙ ከተሞች የኢራን ሚሳኤል ጥቃት ብርቱ ጉዳት ያስተናገዱ ናቸው ። የኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አያቶላ አሊ ሃሚኒ ባለፈው ቅዳሜ በሰጡት መግለጫ እስራኤል ምህረት የማይሰጠው ስህተት መሳሳቷን ነበር የተናገሩት ።
«ጽዮናዊው መንግስት ትልቅ ስህተት ሰርቷል። ከባድ ስህተት ሰርቷል። የግድ የለሽ ተግባር ፈጽሟል። በፈጣሪ ምህረት ይህ መንግስት ይፈራርሳል። »
የእስራኤል ኢራን ጦርነት አራተኛ ቀኑ ላይ ደርሷል። ኢራን ከምዕራባዉያን ጋር ስታደርግ የነበረው እና ዓመታት ያስቆጠረው የኒክልየር መርሃ ግብር ንግግር እና ድርድር አሁን የጨለመ መስሏል። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በድጋሚ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ተስፋ ሰጥቶ የነበረው ድርድርም በመሃል ተገትቷል።
እስራኤል ኢራንን መደብደቧ የፈጠረዉ ድንጋጤና የዩናይትድ ስቴትስ ተቃራኒ አቋም
የእስራኤል ኢራን ጦርነት እና ተጽዕኖው
የእስራኤል ኢራን ጦርነት በርግጥ ዓለምን አስጨንቋል ። የእነርሱ ዳፋ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ በተቀረው ዓለም ላይ ብርቱ ጫና ማሳደሩ አይቀርም ። ልክ የሩስያ ዩክሬን ጦርነት ያደረሰውን አይነት ። ጦርነቱ በአይነት እና በይዘት እየሰፋ ከሄደ የዓለማችን አንድ አራተኛው የነዳጅ ዘይት የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ሰርጥ የመዝጋት ዕድልን ጨምሮ አጋር ልዕለ ኃያሏን ሀገር አሜሪካን ጨምሮ ሀገራትን በጎራ ከፍሎ ወደ ጦርነቱ ጎትቶ ሊያስገባ የሚችልበት ዕድልም ዝግ አይደለም። እስካሁን ባለው ሁኔታ የእስራኤል ዋነኛ አጋር አሜሪካ በቀጥታ በጦርነቱ ባትሳተፍም ለእስራኤል ጥቃቶች ቡራኬ መስጠቷ ታይቷል። ፈረንሳይ እና እንግሊዝን ጨምሮ ምዕራባዉያን በፊናቸው እስራኤልን ከኢራን ጥቃት መከላከል ከሚያስችሉ ተግባራት እስከ የጦር አውሮፕላን ማሰማራት ሊሳተፉ የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለ እየታየ ነው።
ኢራን በበኩሏ ምዕራባዉያን ለእስራኤል ድጋፍ ካደረጉ በየትኛውም ሀገር በሚገኙ ወታደራዊ ጥቅሞቻቸው ላይ ጥቃት ልታደርስ እንደምትችል ዝታለች። አሜሪካ በተናጥል ኢራን በጥቅሞቿ ላይ ጥቃት ካደረሰች በቀጥታ በጦርነቱ ተሳታፊ እንደምትሆን አስጠንቅቃለች። እነዚህ ነገሮች ሲደማመሩ ለኢራን አጋርነታቸውን እየገለጹ የሚገኙ ሃገራትም ራሳቸውን ከጦርነቱ ስለማራቃቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም።
ከሶስት አስርት አመታት በላይ የመካከለኛው ምስራቅ እና የባህረ ሰላጤ ሀገራትን ማህበረ ፖለቲካ ሲከታተል እና ሲዘግብ የኖረው የዶቼ ቬሌው ነጋሽ መሐመድ እንደሚለው ጦርነቱ የማቆም ዉሳኔው በአሜሪካ እና እስራኤል እጅ ነው።
ማሕደረ ዜና፣ የአሜሪካና የኢራን ፍጥጫ-የመካከለኛዉ ምሥራቅ ምሥቅልቅል ሌላ ገፅታ
የሁለቱ ሃገራት ቅድመ ታሪክ
እስራኤል እና ኢራን የዛሬን አያድርገው እና ወዳጅ ሀገራት ነበሩ ። ከአራት አስርታት ዓመታት በፊት እስራኤል ሀገር ለመሆን እና በአንድ እግሯ ለመቆም ስትጣጣር በነበረበት ወቅት ለእስራኤል የሀገርነት እውቅና ለመስጠት ቀዳሚ ከነበሩ ሁለት የእስልምና እምነት ተከታይ ሀገራት መካከል ኢራን አንዷ ነበረች። በጎርጎርሳዊው 1948 እስራኤል እንደ ሀገር ስትመሰረት ዕውቅና በመስጠት ከዐረብ እስላማዊት ሀገር ግብጽ ቀጥላ ኢራን ተጠቃሽ ነበረች ። ኢራን ለእስራኤል እውቅና መስጠት ዋናው ምክንያት ደግሞ የወቅቱ የኢራን መንግስት ከአሜሪካ ጋር የነበረው የጠበቀ ግንኙነት በምክንያትነት የነሳል። ይህ ግን የቆየው እስከ ጎርጎርሳዊው የ1970ዎቹ መጨረሻ የኢራን እስላማዊ አብዮት የመንግስታዊ ለውጥ እስኪያስከትል ድረስ ብቻ ነው።
ጸረ ኢምፔሪያሊዝም አቋም ይዞ ብቅ ያለው የአያቶላ ኸሚኒ አዲሱ መንግስት ከአሜሪካ እና አጋሮቿ በተቃራኒው ሲቆም ከእስራኤል ጋር የነበረውን ግንኙነት በይፋ አቋርጦ ኤምባሲዋን ዘግቷል። ይህ ወደ ከፋ ጠላትነት ደረጃ የደረሰው እና በቀጣናው የበላይነት የመያዝ እና ህልውና የማስጠበቅ የሁለቱ ሃገራት ፍጥጫ በቀጥታ ግጭት ውስጥ ከመግባት ይልቅ ለዓመታት በእጅ አዙር ሲዋጉ ቆይተዋል።
መካከለኛው ምስራቅ አዲሱ የጦር አውድማ ወይስ ?
በጠላትነት መፈላለግ
እስራኤልን በሚያጎራብቱ ሃገራት ዉስጥ የሚገኙ ታጣቂ ቡድኖችን በማስታጠቅ ኢራን ስሟ ጎልቶ ይነሳል። በዚህም እስራኤል ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ያለፉትን ሁለት ሶስት ዓመታት ከፍልስጥኤማዉያኑ ታጣቂ ቡድን ሃማስ ፣ ከሊባኖሱ ሄዝቦላ እና ከየመኑ ሁቲ አማጽያን ጋር የአየር እና የምድር ጦርነት ውስጥ ትገኛለች ። እስራኤል በዙሪያዋ ጋሉ ታጣቂዎች ጋር እያደረገች ያለውን ሁለንተናዊ ጦርነት ሳትቋጭ በራሷ ቀስቃሽነት ከኢራን ጋር ይፋዊ ጦርነት ውስጥ ገብታለች ። ጋዜጠኛ ነጋሽ መሐመድ እንደሚለው የእስራኤል ጦርነቱን ማስጀመር ምክንያታዊነት ሩቅ ነው።
መብት እና ህልውና እንዴት ይታረቁ?
እስራኤል የህልውናዬ ስጋት ስትል የምትገልጸው የኢራን የኑክልየር መርሃ ግብር የኒክልየር የጦር መሳሪያ የማምረት ደረጃ ላይ አድርሷት ይሆን ብለን መጠየቃችን አይቀርም። ሃገራቱ አንዱ መብቱ አንዱ ህልውናው አድርገው የሚወስዱት ቁልፍ ጉዳያቸው እንደመሆኑ መጠን ለዓመታት በጠላትነት ከመፈላለግ ባሻገር ጉዳዩን ቀረብ አድርጎ መመልከትም አስፈላጊ መሆኑ አይቀርም።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ኢራን በኒኩልየር መርሃ ግብሯ እስካሁን 60 ከመቶ የበለጸገ ከ400 ኪግ በላይ የዩራንየም ክምችት እንዳላት ነው። መረጃውን በግርድፉ ከተመለከትን በዚህ መጠን እና ደረጃ ለጊዜው የጦር መሳሪያውን የመስራት አቅም ላይ የደረሰች አይመስልም። ነገር ግን እስራኤል ይህንን ሃሳብ አትቀበልም ። እስራኤል እንደምትለው ኢራን እስካሁን ባበለጸገችው የዩራንየም ክምችት እና ደረጃ በትንሹ እስከ 10 የሚደርሱ ቦምቦችን በሳምንታት ዕድሜ ውስጥ መስራት ያስችላታል ። እንደዚያም ሆኖ እስራኤል በአራቱ ቀናት የአየር ጥቃቷ በኢራን የኑኩልየር ማብላያ ጣቢያዎች የላይኛው ክፍል የመሰረተ ልማቶችን ከመጉዳት ባሻገር ከምድር በታች በተመሸጉ ዋነኛ የማብላያ ጣቢያዎች ላይ እስካሁን የከፋ ጉዳት አለመድረሱ እየተዘገበ ነው።
በርግጥ እስራኤል እንደምትለው ኢራን በድብቅ የኒኩልየር የጦር መሳሪያ መገንባት የሚስችላት ደረጃ ላይ ደርሳ ይሆን ?
ኢራን በእስራኤል ላይ የሰነዘረችው ጥቃት አላማና ግቡ
የዓለማቀፉ ማህበረሰብ ጥሪ
ሀገራት እና ዓለማቀፍ ተቋማት እስራኤል እና ኢራን ጦርነቱን እንዲገቱ ውትወታ እያደረጉ ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊን ጨምሮ ፣ ሩስያ እና ቻይና ፣እና በርካታ የአረብ ሀገራት የመጀመሪያውን ቀን የእስራኤል ጥቃት አውግዘዋል። ምዕራባዉያኑ በፊናቸው ሁለቱም ሀገራት ውጥረቱnr እንዲያረግቡ እና ለመፍትሁሔ እንዲቀመጥ እያሳሰቡ ነው። በእስራኤል እና ኢራን መካከል በተቀሰቀሰው ጦርነት የሀገራቸው እጅ እንደሌለበት ያስታወቁት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ነገር ግን ኢራን የኑኩልየር የጦር መሳሪያ ባለቤት እንድትሆን እንደማይፈቅዱ ነው የተናገሩት።
«ነገሩ ውስብስብ አይደለም ። ባጥም ቀላል ነው። ኢራን የኒኩልየር የጦር መሳሪያ ባለቤት መሆን አትችልም !»
ጦርነቱ በተለምዶ እንደሚታወቁ በእግረኛ ሰራዊት ተደግፎ ምድር ለምድር የሚደረግ አይነት ዉጊያ አይደለም ። ይልቁኑ ዓለማችን የደረሰችበት የቴክኖሎጂ ደረጃ በወለዳቸው አውዳሚ የጦር አውሮፕላኖች እና አህጉር አቋራጭ ባላስቲክ ሚሳኤሎች የሚደረጉ ናቸው። በአራቱ ቀናት ጦርነት ብቻ እንኳ ብንመለከት ሁለቱም ሃገራት ብርቱ ውድመት አስተናግደዋል። ኢራን በታሪኳ አይታ በማታውቀው መልኩ ቁልፍ የጦር እና የሳይንስ ሊቃውንቶቿን በአንድ ጀምበር ከማጣት ባሻገር ከ300 በላይ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለውባታል ። ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ቆስለዋል። እስራኤልም ብትሆን ቀላል የማይባል በትር ነው ያረፈባት የመኖሪያ አካባቢዎችን ጨምሮ ረዣዥም ህንጻዎቿ ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል።
እስራኤል ከኢራን ከደረሰባት መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃት በኋላ «በእሳት መካከል ነው ያለነው»
የኢራኑ መንፈሳዊ መሪ ቀጣዩ በነብስ ተፈላጊ ሰው?
ለዚህም ይመስላል ። ዛሬ የወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት እስራኤል የኢራን ቁልፍ የጦር ሰዎችን እያደነች ከማደን አልፋ ዋነኛው የመንፈሳዊ መሪውን የመግደል ዕቅድ እንዳላት የተሰማው ። ይህ በርግጥ ሊሳካላት ይችል ይሆን ? የሚያስከትለውስ አንድምታ ምን ይሆን ? ነጋሽ ምልከታውን ያጋራል ።
ኢራን በይፋ እስራኤል ጥቃቷን ካቆመች እርሷም አጸፋዉን ልታቆም እንደምትችል በቅጭ ጉዳይ ሚንስትሯ አባስ አራጋች በኩል አሳውቃለች። እስራኤል ግን ጥቃቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል በተደጋጋሚ እየገለጸች ነው። ይህ ከሆነ ጦርነቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ የመቆም አዝማሚያ አይኖረውም ማለት ነው። በዚህ ውስጥ ግን አንድ ነገር ግን አይሸሸግም ። ልክ እንደ ጋዛ ሁሉ ፣ ልክ እንደ ሊባኖስ ሁሉ ኢላማ የተደረጉ የኢራን እና የእስራኤል ከተሞች ወደ ፍርስራሽነት መቀየራቸው አይቀርም። ህጻናት እና ሴቶችን ጨምሮ ሰላማዊ ሰውም ፍልስጥኤማዉያን ያዩትን መከራ ላለማየታቸው ዋስትና የለም። ሰላም ግን ዋጋው ስንት ነው ?
ታምራት ዲንሳ