የኢትዮ ኤርትራ ፍጥጫ፤ የኦነግ ኦፌኮ የሽግግር መንግሥት እና የጀርመን ምርጫ
ሐሙስ፣ የካቲት 20 2017
ሰሞኑን በተለይ የኢትዮጵያ መንግሥትና የኤርትራ መንግሥት እሰጥ አገባ ለዘመናት ሁለቱን ወገኖች ወዳደቀቀው ጦርነት እንዳያመራ ብዙዎችን ማስጋቱን የሚሰነዝሯቸው አስተያየቶች ያሳያሉ። ከትግራይ በኩል ከኤርትራ ጋር ግንኙነት ለመፍጠር የሚጥሩ ኃይሎች አሉ ሲሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን መናገራቸው፤ የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ሙላቱ ተሾመም የኤርትራ መንግሥት በጠብ አጫሪነት የሚከስ ጽሑፍ በአልጃዚራ ማስነበባቸውን ለእሱ ደግሞ ከኤርትራ ወገን የተሰጠውን ምላሽ የተመለከቱ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተጠቃሚዎች መካከል፤ ቴድሮስ ተስፋዬ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ «ባለፈው በፓርላማ ሲሞገስ ሲደነቅ ነበረ የኤርትራ መንግሥት ከጎናችን ባይኖር ከባድ ችግር ዉስጥ እንገባ ነበረ እናመሰግናለን አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ዛሬ ደሞ የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ ሰላም እዳይኖር የሚሠራ ነው አሉን። ማነው ሾርት ሚሞ» በማለት ጠየቁ። ያደታ አዲሱ በበኩላቸው ሃሳባቸውን በአንዲት ቃል ነው የገለጹት፤« ኖቤሉ» ብለው በሳቅም አጅበውታል። በጎርጎሪዮሳዊው 2018 መስከረም ወር በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል እርቀ ሰላም መውረዱን ተከትሎ የኢትዮጵያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር የተሸለሙትን የኖቤል ሽልማት አስታወሱ። ናይታኤል ካሣዬ፤ «ሶማሌ ክልል ከሶማሊያ: አፋር ከጂቡቲ: ኦሮሚያ በተመሳይ ከጎሮቤት ሃገራት ጋር ሲገናኙ የተቀደሰ ሆኖ የትግራይና ኤርትራ ለዛውም የክፉ ጊዜ ወዳጃችን ስትባል ከነበረች ሀገር ጋር ሲሆን ያልተቀደሰ ጋብቻ እስከመባል ደረሰ:: ጊዜ ብዙ ያሳየል::» ነው ያሉት።
ሙሼ በየነ፤ ደግሞ፤ «ወይኔ መደመር.... ቡሉኮ፤ ፈረስ፤ ቀለበት በቃ እንደ ቀልድ» በማለት ሃሳባቸውን ገልጸዋል። ገሠሠ ዘመንም አከሉ፤ «ከምኔው ከምኔው፤ ቀለበቱ ይመለስ በሉ» በማለት። መላኩ ገበየሁ፤ «ያስቃልኮ፤ የእኛ ጎረቤቶች እኮ ብዙ ዓመት አብረው የኖሩት ቸኩለው አይስሙ ፤ተጣድፈው አይነክሱ። ሁሉን በሚዛን እየለኩ ስለሚይዙት ነው። መንግሥት ደግሞ ከግለሰቦች ማነስ የለበትም።» በማለት መከሩ።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የወደብ ጥያቄም ጎን ለጎን እየተነሳ በመሆኑ፤ ይህን አስመልክተው ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል፤ እንዳሻው እስራኤል ካሎ የወደብ ጉዳይ፤ «የሁሉም ኢትዮጵያውያን ወቅታዊ ጥያቄ ነው እንጅ የፓለቲካ አጀንዳ አይደለም» ይላሉ፤ ዳንኤል ጥላሁን ታደሰ ደግሞ፤ «የአሰብ ወደብ በሕግም በመልክዓ ምድርም በሞራልም በታሪክም ለኢትዮጵያ ይገባታል። ይህ በሰላማዊ መንገድ እውን ይሆን ዘንድ ሁሉንም አማራጮች አሟጦ መጠቀም ያስፈልጋል። ሰላማዊ መንገዶች ውጤማ ካልሆኑ ግን «አሰብን እንደ ክሪሚያ» የሩሲያን መንገድ መከተል ለኢትዮጵያ ግደታዋ ይሆናል።» ባይ ናቸው። ነጃ ዳሪ ሉቹሮም፤ «የባሕር በር አስፈላጊነት ምንም ለድርድር የሚቀርብ ጥያቄ አይደለም። መጀመሪያም ኢትዮጵያ በተለያየ አይነት ተጽዕኖ እና ሴራ ነው የባሕር በር እንድታጣ የተደረገው።» ነው የሚሉት። አዲስ ዘመዴ ግን፤ «ወሬ ብቻ ፡ አሰብ አሰብ የምትሉ ሰዎች ጤነኛ ናችሁ? አሰብ እኮ ከሱቅ ተሄዶ የሚገዛ ዓሣ አይደለም። መንግሥት በመጀመሪያ አገር ውስጥ ያሉ ባለሥልጣናት ጥጋባቸውን በልክ እንዲያደርጉ ይሥራ። የሀገር ውስጥ ሰላም ይመለስ፡ ከዚያም የወደብ ጥያቄው በመንግሥት ሳይሆን በሥዝብ ተነሳሽነት ይቀጥላል።» ባይ ናቸው።
አበበ ዲታ፤ «የሚገኝ ከሆነ በሰላማዊ መንገድ በንግግር መሆን አለበት። በጦርነት ከሆነ እንኳን ሕዝብ ወታደሩም ሰልችቶታል።» ይላሉ። ጃፌዝ አሰፋም እንዲሁ፤ «የባሕር በር ያስፈልገናል። እንዴት ከተባለ ግን ጥንቃቄ በተሞላበት ባላሰለሰ ድርድርና የዲፕሎማሲ ጥረት ነው መሆን ያለበት። ድጋሚ እልቂት ውስጥ የሚከት ቀጠናዊ ሰላምን የሚያጠፋ ጦርነት ውስጥ መግባት አያስፈልግም። በሰጥቶ መቀበል መርህ የኢኮኖሚ ትስስር ፈጥሮ ይህንን ማድረግ ይቻላል።» በማለት ዘርዘር ያለ አስተያየታቸውን አጋርተዋል። አፈንዲ ሙተቂም፤ «ለዕድገት ወሳኙ ነገር የባሕር በር ቢሆን ኖሮ ሶማሊያ፣ ፓኪስታን፣ ስሪላንካ፣ ቺሊ፣ ሞዛምቢክ፣ የመን፣ ሀይቲ፣ ወዘተ የትና የት በደረሱ ነበር። የትግራይ
ጦርነት በመከራ ቆሞልን ሌላ ጦርነት አይናፍቃችሁ።» ብለዋል። ጆን ስፌር ደግሞ፤ «የሚያስፈልገን የባሕር በር ሳይሆን ባሕር የሚያክል ሰላም ነው።» በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ሌላው የሰሞኑ የብዙዎች መነጋገሪያ የሆነው በኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ እና በኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ኦፌኮ የቀረበው የሽግግር መንግሥት ምክረ ሀሳብ ነው። ጃገማ አበበ፤ «በኦሮሚያ ክልል የሽግግር መንግሥት መመሥረት በክልሉ ሰላማዊ፣ ፍህታዊ፣ ዴሞክራሳዊ ፖለቲካን፣ ኢኮኖሚን እና ማኅበራዊ መሻሻሎችን ከመፍጠር አስፈላጊነቱ በተጨማሪ በክልሉ መንግሥት የተፈጠሩ ሕገወጥ የቡድን አደረጃጀቶችን ለማፍረስ ይጠቅም ይሆናል።» ነው የሚሉት። በይቅርታ ተደመር በፍቅር ተሻገር የሚል የፌስቡክ ስም ያላቸውም፤ «ብሔራዊ ምክክሩ ከወዲሁ እንዲሳካ የሚያደርግ የተሻለ ጅምር ይመስለኛል። በዕውቀት የተሞላ የ21ኛው ክፍሌ ዘመን አካሄድ ነው። በርቱ እላቸዋለሁ!» ብለዋል። ተስፉ መኮንን ግን፤ «የሽግግር መንግሥት ኦሮሚያን ብቻ ነው እንዴ የሚመለከተው? ይህቺ ነገር የሆነ ነገር አላት የምር አልተዋጠልኝም ሌሎችስ መመካከር መወያየት የለባቸውም ማለት ነው? ወይስ ሌሎች ክልሎችን ለመሰልቀጥ የታሰበ ሳይሆን አይቀርም ባይ ነኝ።» ይላሉ። መኩሪያ በቀለ ደግሞ ይጠይቃሉ፤ «አልገባኝም የሽግግር መንግስት ሲመሰረት ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ብልፅግና ከሰመ ማለት አይደል? ወይስ ምንድ ነው የሚባለው?» በማለት፤ እንቆጳ ዝዮንም ጠያቂ ናቸው፤ «የገባው የሚያስረዳኝ» በማለት። ደጀኔ ዘሪሁንም ጠያቂ ናቸው፣ «ሽግግር ነው ወይስ ሽርሽር ?» ብለው። ዓለሙ ታደለ ደግሞ፤ «ተሻጋሪውስ አለ አሻጋሪውን ነው ያልለየነው(ያላመንነው)!!!» ይላሉ። ንፍታሌም ንፍታሌም ታዲያ፤ የሽግግር መንግሥቱን ሃሳብ፤ «ሪፖብሊክ ምስረታ» ነው ብለውታል።
በራ ሲሳይ ጌታቸው፤ «ውይይቱ ከመንግሥት ጋር በጋራ ስምምነት ላይ የተደረሰበት ከሆነ ግልጽነት መኖር አለበት ። ግልጽነት ይጎድለዋል ። ግልጽነት የጎደለው ከሆነ ደግሞ ከአሁን በፊት በለውጡ ኃይሎች የተሰሩ ስህተቶችን ይደግማል። ከአሁን በፊት ሰላም ለመፍጠር ተብሎ የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ ኃይሎች እስከ ትጥቃቸው እንዲገቡ መደረጉ ኢመደበኛ የታጠቁ ኃይሎች እንዲስፋፋ አድርጓል።» በማለት ሰፋ ያለ አስተያየት አጋርተዋል። ዘውድዓለም ጌታቸውም፤ «የፌዴራልና የኦሮሞ (ክልላዊ) መንግሥት ሕግ በሚከለክልበት ሁኔትና የክልሉ ገዢ ፓርቲ መንግሥት ባልተሳተፈበት ሁኔታ እንዴት ሊሆን ይችላል? ስለዚህ ክልላዊ የሽግግር መንግሥት የሚባል የለም፣ ይህንን መመስረት ሕገ ወጥ ድርጊት ስለሆነ የፌዴራል መንግሥቱ ሊያስቆመው ይገባል። በዚህ ጉዳይ ላይ የተሳተፉ አካላትም በአስቸኳይ ሕግ ፊት ሊቀርቡ ይገባል።» ባይ ናቸው። ኃይለማርያም የተዋህዶ ልጅ ፤ «ወይ አንቺ ኢትዮጵያ ምኑን ታሰሚኛለሽ?» ሲሉ፤ ዋዳ ኦሮሞ ሁንዳ በበኩላቸው፤ «እንደ እርግብ የዋህ እንደ እባብ ልባም መሆን ጥሩ ነው።» በማለት መክረዋል።
ባሳለፍነው እሑድ ዕለት ጀርመን ያካሄደችው ወቅቱን ያልጠበቀ ምርጫ በተለይ የውጪ ዜጎችን ስጋት ላይ በጣሉ የምርቻ ቅስቀሳ አጀንዳዎች ታጅቦ ነበር ከርሟል። የምርጫው ውጤት ከታወቀ በኋላ ነገሮች የተረጋጉ መስለዋል። የጀርመንን ምርጫ ከተከታተሉ ወገኖች አንዱ፤ አሚ ሰለሀዲን ሱላማኒ፤ «በጣም ደሰ የሚል ውጤት ነዉ። የጀርመን ሕዝብ አርቆ አሰተዋይነቱን ያሳየበት እጅግ ነፃና ፍትሀዊ ምርጫ ነዉ። ይህን ዉጤት ለመቀየር ከአሜሪካዉ ትራምፕ ኤለን መሰክ እሰከ ራሺያዉ ፑቲን በጥምረት ቢረባረቡም ዲሞክራሲ አቸነፈ።» ነው ያሉት። ኦሞድ አፔክ ኦኬሎ ደግሞ፤ «ጀርመን ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አድርጋል። ሀገራችን ከጀርመን ዲሞክራሲ ምርጫ በምን ይማራል?» ሲሉ ጠይቀዋል። ሰይድ አህመድ ደግሞ፤ «የምር በዴሞክራሲያዊ ምረጫ በሚያረጉ አገሮች እቀናለሁ የእኛስ አፍሪቃውያን መቼ ይሆን ከጥይት ወደ ምርጫ የምንመጣው!!!??» በማለት ጥያቄ አቅርበዋል። ሀለፎም ኢትዮጵያዊ ፤ «እኛ አንድ መሪ ሳይንቀይር ሁለቴ ቀየሩ፤ ይህ ነው ዴሞክራሲ» አሉ፤ ዳስታ ቄሮ ታዲያ፤ «አምባገነን መንግሥት እና ጀርመንን ማወዳደር አይቻልም። ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የሚባል በዐይኗ አይታ አታቅም።» ሲሉ መለሱ። አሚ ሳላዲን ደግሞ፤ «አንቀፅ 1 የጀርመን ሕገመንግሥት የሰው ልጅ መብት ለድርድር የማይቀርብ የማይገሰስ ነው ይላል፤ ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ የብሔረሰብ መብት ይላል።» በማለት ልዩነን ጠቆሙ። ደስታው መንግሥተአብ አሰግድም፤ «የጀርመኑ ምርጫ ጥሩ ውጤት ነው የጥምር መንግሥት በቅርቡ እንደሚመሰረት ተስፋ አለኝ።» በማለት አስተያየታቸውን አጋርተዋል።
ሸዋዬ ለገሠ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር