የኢትዮጵያ የውጪ ምንዛሪ ሥርዓት ለውጥ በዓመቱ ምን አሳካ?
ረቡዕ፣ ሐምሌ 23 2017የኢትዮጵያ የውጪ ምንዛሪ ፍሰት ከሐምሌ 22 ቀን 2016 ወዲህ 33 በመቶ ጨምሮ 32 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል። ከዚህ ውስጥ የሸቀጦች የወጪ ንግድ ገቢ 8.3 ቢሊዮን ዶላር፣ የአገልግሎቶች የወጪ ንግድ 8.5 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም የግል ሐዋላ 7.1 ቢሊዮን ዶላር ድርሻ እንዳላቸው ብሔራዊ ባንክ ባለፈው አንድ ዓመት የወሰዳቸውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በማስመልከት ሐምሌ 22 ቀን 2017 ያወጣው መግለጫ ይጠቁማል።
ላለፉት 14 ዓመታት ሀገሪቱ ከሸቀጦች የወጪ ንግድ በዓመት ታገኝ የነበረው ገቢ ከ3 ቢሊዮን ዶላር ብዙም ከፍ ሳይል መቆየቱን የሚያስታውሱት የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ጌታቸው ተክለማርያም ብሔራዊ ባንክ ይፋ ያደረገው መረጃ “የተረጋገጠ እና ትክክለኛ ከሆነ ለውጡ በጣም ከፍተኛ የሆነ ልዩነት ነው” ሲሉ ይናገራሉ።
ከሸቀጦች የወጪ ንግድ እና ሐዋላን ከመሳሰሉ ዘርፎች ኢትዮጵያ ያገኘችው ገቢ እንዲያድግ በሐምሌ 2016 ተግባራዊ የተደረገው የውጪ ምንዛሪ ሥርዓት ለውጥ ከፍ ያለ ሚና እንዳለው የመንግሥትን የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር የሚያስፈጽሙ ሹማምንት ይሞግታሉ። ለረዥም ዓመታት ሥራ ላይ የቆየው እና በብሔራዊ ባንክ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግበት የነበረው የምንዛሪ ሥርዓት በመደበኛው እና በትይዩው ገበያ መካከል እስከ 100% የሚጠጋ ልዩነት የሚታይበት ሆኖ ቆይቷል።
ገበያው በቂ የውጪ ምንዛሪ ማቅረብ ባለመቻሉ ምክንያት የተፈጠረው ልዩነት ሸቀጦች ከኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡ ነጋዴች “በውድ ገዝተው በውድ እንዲሸጡ” ሲያስገድድ፤ አስመጪዎች በፊናቸው “በርካሽ ገዝተው ከፍ ባለ ትርፍ እንዲሸጡ” ዕድል የከፈተ እንደነበር አቶ ጌታቸው አስረድተዋል። ይህ የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ከባንኮች በቂ የውጪ ምንዛሪ ማግኘት የተሳናቸው ነጋዴዎች ትይዩውን ገበያ እንዲያዘወትሩ የሚያስገድድ ነበር።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ባለፈው ሣምንት በተካሔደ ጉባኤ ላይ የውጪ ምንዛሪ ሥርዓት ለውጥ ሲደረግ “በሕገ-ወጥ መንገድ መገበያየት አዋጪነቱ ቀንሷል” ሲሉ ተናግረዋል። በለውጡ ምክንያት “በጣም ብዙ ውጤት እየመጣ ነው” ያሉት አቶ አሕመድ ሀገሪቱ ባለፉት 12 ወራት ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና እና ወርቅ በዓለም ገበያ መሸጧን በማሳያነት ጠቅሰዋል። በመንግሥት መረጃ መሠረት ሀገሪቱ ከወርቅ 3.5 ቢሊዮን ዶላር፤ ከቡና 2.6 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች።
ኢትዮጵያ ለአንድ ዓመት የተከተለችው የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት የሸቀጦችን የወጪ ንግድ በተወሰነ መንገድ እንዳበረታታ አቶ ጌታቸው ይስማማሉ። ይሁንና በሸቀጦች የወጪ ንግድ ላይ የታየው የገቢ ዕድገት ሙሉ በሙሉ የማሻሻያው ትሩፋት ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም የሚል አቋም አላቸው።
“የኢትዮጵያን የኤክስፖርት መዋቅር አሁን እንደሚባለው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትም እንደሚመክረው የገንዘብ የምንዛሪ ለውጥ በማምጣት ይሻሻላል ብዬ አላስብም” የሚሉት አቶ ጌታቸው “የምርት ሰንሰለቱ ከዝቅተኛ ምርታማነት ጀምሮ በጣም የተለያዩ ውስብስብ ችግሮች ያሉበት” እንደሆነ ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት “በዚህ ዓመት የተፈጠረውን የኤክስፖርት ገቢ መዋቅራዊ ለውጥ አምጥተናል ወደሚል መተርጎም በጣም ከባድ ነው” ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
የኢትዮጵያ የውጪ ምንዛሪ ክምችት እንዲጨምር፣ የሸቀጦች የወጪ ንግድ ገቢ እና ሐዋላ እንዲያድግ የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ላይ የተደረገው ለውጥ አስተዋጽዖ እንዳበረከተ የፋይናንስ ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ ይስማማሉ።
ኢትዮጵያ “በከፍተኛ ሁኔታ” ሸቀጦች በዓለም ገበያ ልትሸጥ የምትችለው በማምረቻው ዘርፍ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር አብዱልመናን “መዋቅራዊ ችግሮች ካልተፈቱ በስተቀር አሁንም ከዚህ የዘለለ ብዙም ነገር ማምጣት አንችልም” የሚል ሥጋት አላቸው። ዘርፉ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚካሔዱ ግጭቶች የሚፈተን፣ ሙስና፣ የኤሌክትሪክ አቅርቦት፣ የኃይል መቆራረጥ እና የፋይናንስ አቅርቦትን የመሳሰሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች “የተተበተበ” መሆኑ ደግሞ ትልቅ ተግዳሮት ነው።
የውጪ ምንዛሪ ሥርዓት ለውጥ የኢትዮጵያ መንግሥት ላለፉት ሰባት ዓመታት ገደማ ተግባራዊ ሲያደርግ የቆየው የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር አካል ነው። ብር ዶላርን ከመሳሰሉ መገበያያ ገንዘቦች አኳያ ያለውን የምንዛሪ ተመን ያዳከመው ውሳኔ በመጀመሪያው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ውስጥ የተካተተ ቢሆንም ሀገሪቱ ደም አፋሳሽ የርስ በርስ ጦርነት እና ግጭት ውስጥ ስትዘፈቅ ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል።
ብርን በኃይል ያዳከመው እርምጃ ከሐምሌ 22 ቀን 2016 ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ከረዥም ድርድር በኋላ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በሚበደረው 3.4 ቢሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ሁለተኛ ምዕራፍ ተግባራዊ ማድረግ ሲጀምር ነው። “የውጪ ምንዛሪ ክምችት ሊጨምር ይችላል። ከሸቀጦች የወጪ ንግድ የሚገኝ ገቢ ሊጨምር ይችላል። ሐዋላ ሊጨምር ይችላል” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን መንግሥት የወሰደው እርምጃ አዎንታዊ ለውጥ እንዳመጣ ቢስማሙም ያስከተለው ጉዳት ሊዘነጋ እንደማይገባ ይሞግታሉ።
ነዳጅ፣ መድሐኒት እና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ብዙ ዕቃዎች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመራቸውን ማሻሻያውን በቅርብ የሚከታተሉት የፋይናንስ ባለሙያ ያነሳሉ። “ከዚያም ባሻገር ግን ንግድ ባንክን ለከፍተኛ ኪሳራ፣ ብሔራዊ ባንክ በታሪኩ አይቶት የማያውቀው ኪሳራ ዳርጓል” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን “የኢትዮጵያ መንግሥት ዕዳ በብር በጣም በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጋነን አድርጓል” ሲሉ ዳፋውን ዘርዝረዋል።
የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት በብሔራዊ ባንክ አገላለጽ “በገበያ ኃይሎች” እንዲመራ ቢደረግም በይፋዊው እና በትይዩው ገበያ መካከል ያለው ተመን አልተዋሀደም። ከሐምሌ 21 ቀን 2016 በፊት በባንኮች በ58 ብር ገደማ ይመነዘር የነበረው አንድ ዶላር በብሔራዊ ባንክ አማካኝ ዕለታዊ የምንዛሪ ተመን ጠቋሚ መሠረት ዛሬ ወደ 138 ብር አሻቅቧል። በብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ተሰጥቷቸው ገበያውን የተቀላቀሉት የውጪ ምንዛሪ ግብይት ተቋማት በአንጻሩ በዛሬው ዕለት አንድ ዶላር በ154 ብር ገደማ ገዝተው በ157 ብር ገደማ ይሸጣሉ። በትይዩው ገበያ በአንጻሩ ዶላር እስከ 164 ብር ድረስ እየተመነዘረ ይገኛል።
በውጪ ምንዛሪ ሥርዓት ለውጡ ምክንያት ይፋዊው እና በትይዩው ገበያ ይዋሃዳሉ ወይም በመካከላቸው ያለው የተመን ልዩነት ይጠባል ተብሎ ቢጠበቅም እስካሁን አልተሳካም። ዶክተር አብዱልመናን የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ሁለቱን ገበያዎች ማዋሐድ ወይም ማቀራረብ “አልተሳካላቸውም ” ሲሉ ይተቻሉ።
አቶ ጌታቸው በበኩላቸው በመደበኛ እና በትይዩ የውጪ ምንዛሪ ገበያዎች መካከል ያለ ልዩነት ከዚህ በኋላ በአቅርቦት እና በፍላጎት አለመጣጣም የተፈጠረ ነው ብሎ መቀበል ይቸግራቸዋል።
በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ የተንሠራፉ የአሠራር ግድፈቶች እና ሌብነትን የመሳሰሉ ችግሮች ብር ከዶላር አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን እንዳይረጋጋ እያደረጉ እንደሚገኙ የሚያምኑት አቶ ጌታቸው የብሔራዊ ባንክን ቁርጠኛ እርምጃ የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውን አስረድተዋል። ከዚህ በተጨማሪ የገንዘብ ሽሽት (capital flight) የትይዩው ገበያ እንዲፋፋ ሚና እንዳለውም ጠቅሰዋል።
የዐቢይ መንግሥት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የሀገሪቱ ዜጎች በከፍተኛ የኑሮ ውድነት በሚፈተኑበት ወቅት ነው። የውጪ ምንዛሪ ሥርዓት ላይ የተደረገው ለውጥ ነዳጅ እና የምግብ ማብዘያ ዘይት የመሳሰሉ ሸቀጦች ዋጋ እንዲንር አድርጓል። የመንግሥትን ገቢ ለማሳደግ ተግባራዊ እየተደረጉ የሚገኙ የግብር ዐይነቶች ብዛት፣ የአገልግሎት ክፍያ ጭማሪዎች የሸማቾችን አቅም እየተፈታተኑ ይገኛሉ። ለመንግሥት ሠራተኞች የተደረገ የደመወዝ ጭማሪ ቢኖርም ከዋጋ ውድነት አንጻር የሚያመረቃ ፋታ የሚሰጥ አልሆነም።
የዋጋ ግሽበት በሰኔ ወር ወደ 13.9 በመቶ ዝቅ እንዳለ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል። የዋጋ ግሽበትን የመቆጣጠር ኃላፊነት የተጣለበት ብሔራዊው ባንክ ባለፈው አንድ ዓመት ተግባራዊ የተደረጉ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ውጤት “የሚደነቅ ቢሆንም ገና መሠራት ያለበት ብዙ ሥራ አለ” የሚል ዕምነት አለው። ከዚህ ውስጥ ኢትዮጵያውያንን የሚፈታተነውን የኑሮ ውድነት ለማቃለል የዋጋ ግሽበትን በ2018 ወደ ነጠላ አሐዝ የማውረድ ዕቅድ ይገኝበታል።
የትይዩ ገበያው ማንሠራራት፣ የለጋሾች ድጋፍ መቀነስ እና የሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ ለኢኮኖሚ ማሻሻያው ትግበራ እና ኢትዮጵያ ከአበዳሪዎቿ የምትሻው የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ሥጋት ሊሆኑ እንደሚችሉ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) አስጠንቅቋል። ማሻሻያው ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ እና በኢኮኖሚው ላይ ቀጥተኛ ዳፋ ያሳደሩ ግጭቶች መፍትሔ ሳይበጅላቸው ነው። በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በመካሔድ ላይ የሚገኙ ግጭቶች መቋጫ አላገኙም። ደም አፋሳሹ የትግራይ ጦርነት ዳግም ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ሥጋት አገርሽቷል።
“በማክሮ ኢኮኖሚ ረገድ ያለ ዝንፈት መፍታት ዘላቂ ግብ አይደለም” የሚሉት አቶ ጌታቸው ዝንፈቱን ማረቅ “ወደ ቀጣይ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲሔድ የሚያስችሉት መዋቅራዊ ሁኔታዎች ሊሠሩ የሚችሉት የተረጋጋ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ሲኖር ነው” ሲሉ አስረድተዋል። የሀገሪቱ መረጋጋት ለኢኮኖሚ ማሻሻያው “ስኬት ቁልፍ ጉዳይ ነው። ያለ እሱ የምንፈልገውን ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ማምጣት እንችላለን ብዬ አላስብም” ሲሉ ተናግረዋል።
አርታዒ ታምራት ዲንሳ