የኢትዮጵያ የባህር ኃይል ዋና መስሪያ ቤትን የማስመረቅ አንድምታ?
ሰኞ፣ ጳጉሜን 3 2017የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ዋና መሥሪያ ቤትን ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ መርቀው ስከፍቱ ባደረጉት ንግግር፤ “ግዙፍ እና ውብ የሆነው የባሕር ኃይል ዋና መሥሪያ ቤት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አስጠባቂ ተቋም እውን የማድረግ ብቃት” ሲሉ መግለጻቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበውታል።
ኤታማዦር ሹሙ “የባሕር ኃይል አመራር እና አባላት ከ33 ዓመት በኋላ ቁጭት ሻሪ ኃይል ሆናችሁ በመምጣታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ” በማለትም “በማንኛውም ጊዜ የባሕር ስፍራችሁን ለመያዝ ዝግጁ ሁኑ” ሲሉ መመሪያ ሰጥተዋልም።
ይህ የአገሪቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ንግግር የተሰማው ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅን በተመለከተ በሰጡት ዘለግ ባለው ቃለምልልሳው መሃል ስለባህር በር አንስተው በሰጡት ጥቆማ “የቀይ ባህር ወደብ ማስመለስ ጉዳይ ቀላል” መሆኑን ፍንጭ መስጠታቸውን ተከትሎ ነው፡፡
ለመሆኑ ኢትዮጵያ ከሶስት አስርት ዓመታት ግድም በፊት ያጣችውን የባህር በር መልሳ በቁጥጥሯ ስር ለማዋል የምታደርገውን ጥረት ዓለማቀፉ ህግ እንዴት ይመለከተዋል? በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ ያጋሩት የህግ ባለሙያና ደራሲ አወት ልጃለም በዓለማቀፍ የወሰን አስተዳደር ህግ ነገሮች ቀላል የሚሆኑ አይመስልም ይላሉ፡፡
“የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት ነጻ ስወጡ የቅን ግዛቱን ድንበር እናከብራለን የሚል ስምምነት አላቸው” ያሉት ባለሙያው ይህን ስምምነት ከነችግሩም ቢሆን ከመቀበል ይልቅ ወደ ሌላ አማራጭ ከተሄደ ችግሮች ልወሳሰቡ ይችላሉ የሚል ሃሳብ በበርካታ የአፍሪካ አገራት ውስጥ መኖሩን ጠቁመዋል፡፡ የኤርትራ እና ኢትዮጵያ አስተዳደራዊ ወሰን ጉዳይንም ከዚህ አኳያ ያነሱት የህግ ባለሙያው ትልቁ ችግር የሚታየው በቅኝ ግዛት አስተዳደራዊ ድንበር ላይ መሆኑን ነው ያመላከቱት፡፡
ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ባለስልጣናት እና በኤርትራ ባለስልጣት መካከል የቃላት መወራወርም ተሰምቷል፡፡ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የኢትዮጵያን ወሰን ወደ ቀይባህር በመመለስ አገሪቷን የወደብ ባለቤት አገር የማድረግ ፍትሃዊነት ስያነሱ በኤርትራ በኩል ይህንን አስተያየት የሚያጣጥል መግለጫ ተሰምቷል፡፡
የህግ ባለሙያው አቶ ዓወት የተሻለ መንገድ ሲሉ በሰጡት አስተያየታቸው፤ “አገራቱ ተስማምተው የሚደርጉት ውሳኔ ካለ ይቻላል” ያሉን ባለሙያው ከዚያ ውጭ ያለው መንገድ አከራካሪ ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ አገራቱ በዓለማቀፍ ህግ እንዳኝ ካሉ የቅጭ ግዛቱ ድንበር እንደሰነድ ልቀርብ ይችላልም ያሉን ባለሙያው ሁለቱ አገራት የጋራ ተጠቃሚነታቸውን በሚያረጋግጡበት ሁኔታ ላይ ብወያዩና ልዩነታቸውን በመፍታት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ብያተኩሩ የተሻለ እንደሆነም በአስተያየታቸው ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ የባህርበር ሰራዊቷን በማደራጀት የዝግጅት ስራዎችን ከወዲሁ መስራቷስ ምን ያመለክት ይሆን በሚል የተጠየቁት ባለሙያው፤ “የኢትዮጵያ ምንግስት በይፋ ይህንን ነገር አጀንዳ አድርገነዋል በማለት ወደፊት ማምጣቱ የማይታበል ነው” በማለት ከዚህ አኳያ አሁን ያለው አማራጭ ሁለት ብቻ ነው ብለዋል፡፡
አንድም ወታደራዊ አቅምን በማደራጀት የመደራደር አቅምን ከፍ ማድረግ ሲሆን ሌላኛው መንገድ ደግሞ ወደ ቀጥተኛው ጦርነት በመግባት ነገሮችን በሃይል የማስፈጸም አማራጭ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
እሸቴ በቀለ
ማንተጋፍቶት ስለሺ