የኢትዮጵያ የሲቪል ድርጅቶች ምክር ቤት የሰላም ጥሪ
ዓርብ፣ ነሐሴ 16 2017ኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት፣ ግጭት እና ኃይል የታከለበት ውጊያ እንዲቆም የሚጠይቅ ተከታታይ ጉባኤ ሊያደርግ መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አስታወቀ።የሰላም ጥሪዎች ይተላለፉበታል የተባለው መድረክ አዲስ አበባን ጨምሮ በስድስት ክልሎች ይደረጋል ያለው ምክር ቤቱ የትጥቅ ግጭት ውስጥ የሚገኙ አካላት በመድረኩ ይሳተፋ እንደሆን ተጠይቆ ማረጋገጫ አልሰጠም።
ምክር ቤቱ "ጦርነትና ግጭት ማብቃት አለበት" የሚለውን ጥሪ ይፋ ሲያደርግ ለተፈጻሚነቱ ኃላፊነት ያለባቸው አካላት "ውሳኔ አሁን ያስፈልጋል" ሲል የንቅናቄ ግቡ የማኅበረሰቡን ስቃይና እንግልት ማስቆም መሆኑን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አሕመድ ሁሴን "ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ማስቻል ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቅድሚያ የሚሰጠው" ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው በአዲስ አበባ ይካሄዳል በተባለው መድረክ ላይ "ለሁሉም የግጭት ተፋላሚ ወገኖች ወደ ሰላማም እንዲቀርቡ፣ የትጥቅ ግጭቶች እንዲቆሙ እና ሁሉንም ያሳተፈ ሀገራዊ ምክክር እንዲቀጥል ጥሪ ይቀርበታል" ብለዋል።
ሁሉንም የሲቪል ድርጅቶች የሚያቅፈውምክር ቤቱ የዚህ ጥሪ ግብ የቀጠሉ "ጦርነት እና ግጭቶች እንዲያበቁ" የእርስ በርስ ግጭቶችን ተከትሎ በሕዝብ ላይ እየደረሱ ያሉ ተደራራቢ ጉዳቶች እንዲቆሙ ተፋላሚዎችን የማቀራረብ፣ የማነጋገር፣ የማደራደር ኃላፊነት ያለባቸው አካላት ሥራቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ግፊት ማድረግ መሆኑን አቶ አሕመድ ገልፀዋል።
በሌላ በኩል የውጭ ድርጅቶች እና ኢትዮጵያ ውስጥ በሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች የተመሰረቱ ሀገር በቀል [ሲቪክ] ድርጅቶች የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማግባባትም ሆነ ግፊት በማድረግ ተፅዕኖ መፍጠር፣ በመራጮች ትምህርት ወይም በምርጫ መታዘብ ሥራ ላይ መሠማራት አይችሉም" በሚል በረቂቅነት ቀርቦ የነበረው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ በተደረገ ውትወታ ከረቂቁ እንዲወጣ መደረጉን የምክር ቤታ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተረፈ ደጌቲ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።
ይህ የሰላም ጥሪ ይቀርብበታል የተባለው የአዲስ እበባው መድረክ ከሁለት ሳምንት በኋላ ነሐሴ 29 ይደረጋል ተብሏል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ልዩ ልዩ የሲቪል ድርጅቶች በአዲስ ዓመት ዋዜማ ተከታታይ የሰላም ጥሪዎችን ከመፍትሔ አማራጮች ጋራ ጭምር ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል።ይሁንና በአማራ ክልል ያለው ጦርነት፣ በኦሮሚያ ክልል ያለው ግጭት፣ በትግራይ ክልል የሚታየው የሌላ ዙር የግጭት አዝማሚያ ብሎም የዜጎች እገታ እና ስወራ ሲቀረፍ አልተስተዋለም።
ሰዎች በነፃነትት የመንቀሳቀስ እና የመሥራት መብታቸውም በዚሁ ምክንያት አደጋ እንደገጠመው ጥናት የማያሻው ተጨባጭ ፈተና መኖሩን የገለፀው የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የሰላም ጥሪው ዓላማም ይህንን በማስወገድ ሰላማዊ ሕይወት እንዲኖር ለማድረግ መሆኑን በመግለጫው ጠቅሷል።
ሰለሞን ሙጬ
ነጋሽ መሐመድ
ልደት አበበ