የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሸቀጥ ለሚያስገቡና ለተጓዦች የሚፈቀደዉን የውጭ ምንዛሪ መጠን ጨመረ
ዓርብ፣ ግንቦት 15 2017የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክከዉጪ ለሚገቡ ሸቀጦች የሚያስፈልገዉን ቅድመ-ክፍያ መጨመሩን አስታወቀ።ባንኩ በደብዳቤና መግለጫ እንዳስታወቀዉ ወደ ዉጪ ለሚጓዙ መንገደኞችና ነጋዴዎች የሚፈቀደዉን የዉጪ ምንዛሪ መጠንም በእጥፍ አሳድጓል።የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባለፈዉ ማክሰኞ ይፋ ያደረገዉ ደንብ የዉጪ ምንዛሪ ገበያ ሥርዓትን ያሻሽላል ባይ ነዉ።የገንዘብና የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ደግሞ ማሻሻያዉ የመደበኛ እና የትይዩ ወይም የጥቁር ገቢያ የውጭ ምንዛሪ መጠን ልዩነትን ማጥበብ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ስዩም ጌቱ ዝርዝር ዘገባ ልኮልናል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ገቢያ ስርዓትን ይበልጥ ለማሻሻል በሚል ከማክሰኞ ግንቦት 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ እወስዳለሁ ባለው የለውጥ እርምጃ የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ገቢያን ከዓለም አቀፍ አሰራር ጋር ከማጣጣም ባለፈ ለአስመጪዎች እና ለውጭ ሀገር ተጓዦች ምቹ ያለውን ሁኔታ መዘርጋቱን አስታውቋል፡፡
ከባለፈው ዓመት ሀምሌ ወር ጀምሮ በተወሰደው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምቺት ከመቼውም ጊዜ በላይ ማደጉን ያመለከተው ብሔራዊ ባንኩ፤ የውጭ ምንዛሪ ገቢያ ስርዓቱን ይበልጥ ለማጠናከር ወሰድኩ ያሏቸው አድርምጃዎች፤ አንደኛው ለአስመጪዎች የቅድመ ክፍያ መጠንን ከፍ የማድረግ ውሳኔ ነው ብሏል፡፡ በዚህም ሸቀጦችን ከውጪ ለማስገባት ሊከፈል የሚችለውን የቅድመ ክፍያ መጠን ከ5 ሺህ ወደ 50 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ከፍ ማለቱ ነው ያስታወቀው፡፡
በሁለተኛነት ለውጭ ሀገር ተጓዦች የሚፈቀደውንም የውጭ ምንዛሪ ገንዘብ መጠንም ለግል ተጓዦች ወደ 10 ሺህ እንዲሁም ለንግድ ስራ መንገደኞች ወደ 15 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ከፍ ብሎ እንድከፈል የተላለፈው ውሳኔ ነው፡፡
የውሳኔዎቹ አንድምታ
በእነዚህ የብሔራዊ ባንኩ ውሳኔ አንድምታ ላይ አስተያየታቸውን የተጠየቁት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያ አቶ አብዱልመናን መሀመድ የውሳኔዎቹ ዋና ነጥብ የባንኮች ይፋዊ የምንዛሪ መጠን ከትይዩ ገቢያ (ጥቁር ገቢያ) ጋር ያላቸውን ልዩነት ማጥበብ ላይ ያተኮረ ይመስላል ብለዋል፡፡ “ገደቡ ምን ችግር አለው መሰለህ፤ አንድ አስመጪ ሆነህ የቅድመ ክፍያው 5000 ብቻ የሚፈቀድልህ ከሆነ ለተጨማሪው ወደ ሌላ አማራጭ (ወደ ጥቁር ገቢያ) ለመሄድ ትገደዳለህ” የሚሉት ባለሙያው፤ ያ የትይዩ ገቢያን ተፈላጊነት ስለሚያሳድገው ጥቁር ገቢያውና መደበኛ የባንኮች ምንዛሪ መካከል ልዩነቱ እንዲሰፋ ያስገድዳል የሚለውን ምልከታቸውን አጋርተዋል፡፡ አሁን ላይ በኢትዮጵያ በትይዩና የባንኮች ምንዛሪ መካከል ልዩነቱ እየሰፋ መምጣቱንም በማመልከት የብሔራዊ ባንክ ጥረት እሱን ክፍተት ለመድፈን ነው እየጣረ ያለው ብለዋልም፡፡
ባንኮች የአገልግሎት ክፍያ በሚል የሚያስከፍሉትና ተጽእኖው
ብሔራዊ ባንክ በአዲስ አሰራሩ በሶስተኝነት የወሰደው እርምጃ የባንኮች የውጭ ምንዛሪ ክፍያዎች ስርዓት ማስያዝ ባለው አቅጣጫው ባንኮች ለውጪ ምንዛሪ አገልግሎት የሚያስከፍሏቸው ማናቸውም አስተዳደራዊ ክፍያዎች ከፊታችን ሰኞ ግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ከአራት በመቶ እንዳይበልጥ መወሰኑ ነው፡፡ በዚህም ላይ አስተያየታቸውን ያከሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሃመድ፤ “ባንኮች የውጭ ምንዛሪ የሚገዙበትንና የሚሸጡበትን ልዩነት ወደ ሁለት በመቶ ብያወርዱም የአገልግሎት እያሉ የሚያስከፍሉት ወጪ አለ” በማለት ይህም የምንዛሪውን ዋጋ እንዳናረው አስረድተዋል፡፡ እናም ብሔራዊ ባንክ መጠኑ በአራት በመቶ በተወሰነ የአገለግሎት ክፍያ እና ግልጽነት ባለው አሰራር ይህንንም ክፍተት ለመድፈን ወትኗል ነው ያሉት፡፡
ማሻሻያዎቹ ገቢራዊ ሊሆኑ የማይችሉበት ስጋት…
በዓለምአቀፍ ልምድ የትይዩ ገቢያን ከናካተው ማጥፋት እንደማይቻልም የገለጹት ባለሙያው ዋናው ትክረቱ ልዩነቱን ማጥበብ ላይ ማተኮር ብሆንም በስኬታማነቱ ላይ ግን አሁንም ጥርጣሬ አላቸው፡፡ ጥርጣሪያቸውም በቂ የሆነው የውጭ ምንዛሪ ክምችት በኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች አለ ወይ ከሚል እንደሚነሳ በማስገንዘብ፡፡ “በመደበኛውና በትቁር ገቢያው መካከል አሁንም ልዩነቱ እየሰፋ መጥቷል” ያሉት አብዱልመናን፤ “ይህ ልዩነት እየሰፋ ከሄደ እንደ ሀዋላ ያሉትን የውጭ ምንዛሪ አስተላላፊዎችን ከመደበኛው መስመር ሊያስወጣቸው ይችላል” በማለት ተግዳሮቹን አንስተዋል፡፡ በዋናነትም ባንኮች የውጪ ተጓዦችም ሆኑ ለንግድ ስራ የሚመላለሱ የፈለጉትን ያህል ከባንክ ያገኛሉ ወይ የሚለውን በጥርጣሬ በማንሳት አይመስለኝም በማለት ማብራሪያቸውን ቋጭተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አገሪቱ ባለፈው ኣመት ሀምሌ ወር ያከናወነችውን የኢኮኖሚ ማሻሻያን ተከትሎ የውጭ ምንዛሪ በገቢያው እንዲመራ ከተወሰነ በኋላ አመርቂ ያለውን የውጭ ምንዛሪ ክምችት ማግኘቱን በተደጋጋሚ ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡
ሥዩም ጌቱ
ነጋሽ መሐመድ
አዜብ ታደሰ