የአፍሪካ አንድነት ድርጅት 60ኛ ዓመት ሲታሰብ
ረቡዕ፣ ግንቦት 9 2015የአፍሪካ አንድነት ድርጅት 60ኛ ዓመት ሲታሰብ
የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ህብረት አንድነት ድርጅት በሚል ስያሜ ከተመሰረተ 60 ዓመታትን ደፍኗል፡፡
የህብረቱ 60ኛ ዓመት በጎርጎሳውያኑ ግንቦት 25 ቀን 2023 በህብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ ውስጥ ሲታወስ አፍሪካን በኢኮኖሚ ማስተሳሰርና አፍሪካ ከኢኮኖሚ ጥገኝነት የምትላቀቅበትን መንገድ መቀየስ አንደኛው ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው ተብሏል፡፡
ከህብረቱ 60ኛ ዓመት አከባበር ጎን ለጎን በዚሁ በአህጉሪቱ የኢኮኖሚ ትስስር ላይ ያተኮረ ትርዒት እንደሚዘጋጅ ነው የተገለጸው፡፡
የቅኝ ግዛት እና የአፓርታይድ ስርዓትን በመቃወም በጋራ መቆምን ዋና ዓለማው አድርጎ በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር ግንቦት 25 ቀን 1963 በአዲስ አበባ በ32 አገራት ተሳታፊነት የተመሰረተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት 60ኛ ዓመቱን የሚደፍነው ግንቦት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ነው፡፡ ይህ ቀን በአዲስ አበባ ሲዘከር በጉልህ ህብረቱ ሊያተኩርበት ይገባል የተባለውም ጠንካራ የኢኮኖሚ መስተጋብራዊ ትስስር መፍጠር ነው ተብሏል፡፡ በእነዚህ 60 ዓመታት የአህጉሪቱ የፖለቲካ እና ዲፕሎማሲ ማዕከል ሆና ጉልህ ድርሻ የተጫወተች የኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባም በቀጣይ የአህጉሪቱ የኢኮኖሚ ማዕከል እንድትሆን ማንቀሳቀስ ከወዲሁ ታስቦበታል ተብሏል፡፡
ይህንኑን የህብረቱ 60ኛ ዓመት ማክበርን ምክኒያት በማድረግም የአፍሪካ የፈጠራ እና የተለያዩ የተፈጥሮ ፀጋም ሆነ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሚቀርቡበት ነው የተባለ “ዋን አፍሪካ ኤክስፖ” የተሰኘ የንግድ ትርዕት እንደሚካሄድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአዘጋጅ አካላት ጋር ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተብራርቷል፡፡
አምባሳደር አብዶ ያሲን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል እና የዋን አፍሪካ ኤክስፖ አስተባባሪ ናቸው፡፡ “ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 እንዲሳካ አበክራ እየሰራች ነው፡፡ የዚህ ኤክስፖ አንዱ ዓላማም የህብረቱ 60ኛ ዓመት ሲከበር አፍሪካን በኢኮኖሚ የማስተሳሰር አንዱ ግን ላይ በትኩረት መስራት ነው” ሲሉም የህብረቱ 60ኛ ዓመት ላይ የኢኮኖሚ ትስስር አስፈላጊነቱን አጉልተው አንስተዋል፡፡
አምባሳደር አባቢ ደምሴ ደግሞ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢኮኖሚክ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል ናቸው፡፡ “ህብረቱ የ2063 አጀንዳ ላይ ቢያስቀምጥም እስካሁን የመጣው ኢኮኖሚያዊ እምርታ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ለህብረቱ አባል ሃገራት ለጋራ ጥቅም ስትሰራ ቆይታለች፡፡ አዲስ አበባ ደግሞ እንደ አህጉሪቱ የፖለቲካ እና ዲፕሎማሲ መቀመጫነቷ ለኢኮኖሚ ትስስርም ጉልህ ሚና እንድትጫወት ነው ከህብረቱ 60ኛ ዓመት ምስረታ ጎን ለጎን ይህን ዓለማቀፍ ኤክስፖ እንድታዘጋጅ የተፈለገው፡፡”
መሰል የንግድ፣ ቴክኖሎጂ እና ባህል ልውውጥ ኢትዮጵያን እንደ ሃገር እና አፍሪካን እንደ አህጉል መንደር እየሆነች በመጣችው ዓለም ባላቸው እምቅ የመልማት አቅም ተወዳዳሪ ለማድረግ ይረዳልም ተብሏል፡፡ ይህ ደግሞ አፍሪካን ከእጅ አዙር የምጣኔ ሃብቱ ቅኝ ግዢ ለማላቀቅ ጥሩ ጅማሮ ሊሆን እንደሚችልም እንዲሁ፡፡ አምባሳደር አባቢ ደምሴ እንዳሉትም፤ “ሃብት፣ እድል እና ገበያን በማስተሳሰር ከኢትዮጵያ ባሻገር የአፍሪካን ገጽታ በዓለም ፊት ከመገንባት ባሻገር፤ የአፍረካን ኢኮኖሚ ከዓለም ኢኮኖሚ ጋር ለማስተሳሰርም አንዱን እድል የሚፈጥር ሆናል፡፡”
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአዘጋጅ አካላት ጋር በመተባበር እያዘጋጀ ባለው ዋን አፍሪካ ኤክስፖ፤ የዋን አፍሪካ ኤክስፖ መስራቾች እና የቦርድ አባላት በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ተሳትፈዋል፡፡ አቶ ሳሙኤል መብራቱ የኤክስፖው ኮሚቴ አባል ናቸው፡፡ “ኤክስፖው የተዘጋጀው የአፍሪካን ምርት ለአፍሪካውያን ማስተሳሰር እና ከሌላውም ዓለም ጋር በንግድና አምራችነት ለማገናኘት ነው፡፡ አፍሪካን በንግድ የማስተሳሰሩ ጊዜው ደግሞ አሁን ነው፡፡”
የአፍሪካ ህብረት ከተመሰረተ 60 ዓመታት ቢቆጠሩም በበርካቶች ዘንድ በህብረቱ ተጽእኖ ላይ ጥያቄ ሲያነሱ ይስተዋላል፡፡
ስዩም ጌቱ
ታምራት ዲንሳ
ኂሩት መለሰ