የአዲስ አበባን ችግር ያቃልላል የተባለው የጀርመን ፕሮጀክት
ሐሙስ፣ የካቲት 20 2017የሳይንስ ምርምሮችን እና የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን በመደገፍ የሚታወቀው የዳይምለር እና ቤንዝ ሽቲፍቱንግ ፋውንዴሽን በጀርመን እና በአፍሪካ ተቋማት መካከል የምርምር ትብብርን ለማሳደግ እየሰራ ነው። ፋውንዴሽኑ በቅርቡ በአፍሪቃ ችግሮች ላይ ያተኮሩ ሁለት ሳይንሳዊ ፕሮጀክቶችን ለትግበራ መርጧል።
በፋውንዴሽኑ የንዘብ ድጋፍ የሚተገበሩት እነዚህ ፕሮጀክቶች ፤ ለአፍሪቃ ሀገራት ማህበራዊ ተግዳሮቶች አስቸኳይ ምላሽ የሚሰጡ የምርምር ፕሮጀክቶች ናቸው። የመጀመሪያው ፕሮጀክት በአፍሪቃ ጂኦፖሊቲካ እና የመገናኛ ብዙሃን ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪቃ ሀገራት በተለይም በኢትዮጵያ የሚታየውን የከተሞች ችግር ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ለመፍታት የሚያስችል ነው።
የፕሮጀክቱ ችግር ፈች መረጃዎችን ይሰበስባል
የምርምር ፕሮጀክቱ በጀርመን በካርልስሩሄ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ፕሮፌሰር በሆኑት በዶክተር. ዊልሄልም ስቶርክ የሚመራ ሲሆን፤እሳቸው እንደሚሉት የፕሮጀክቱ ሀሳብ ችግር ፈች የሆነ አዲስ የመረጃ ስብስብ መፍጠር ነው።
«በአፍሪቃ የሚገኙ አዳጊ ሀገራት በአብዛኛው በፍጥነት እያደጉ ነው።በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ለስራ ፍለጋ ወደ ከተሞች ይመጣሉ።ያ ማለት በአዳጊ ሀገራት በከተሞች አካባቢ ፈጣን የህዝብ ቁጥር እድገት አለ።ይህ እድገት ቁጥጥር አይደረግበትም። ማለትም በየአመቱ ወይም በየ ሩብ ዓመት ምን ያህል ሰዎች ወደ ከተማ እንደሚገቡ የከተማ አስተዳደሮች አያውቁም።ያማለት የከተማ የመሰረተ ልማት፣የሀይል እና የውሃ አቅርቦት፣የትራፊክ እንቅስቃሴን ወዘተ የመሳሰሉ ነገሮችን ዕቅድ እነዚህን ሰዎች አያካትትም ማለት ነው።ይህም ጎስቋላ አካባቢዎች እንዲፈጠሩ ያደርጋል።ስለዚህ ከኛ ፕሮጀክት ጀርባ ያለው ሃሳብ ትይዩ የዲጅታል ዳታ ለመፍጠር ነው።»
የኤለክትሪክ መስመር ዝርጋታ የፕሮጀክቱ አካል ነው
ፕሮጄክቱ እያደገ በመጣውከገጠር ወደ ከተማ ፍልሰትን በተመለከተ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት የከተሞች መስፋፋትን መከታተል እና ሞዴል ማድረግን ያጠቃልላል።
ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ፈጣን የከተማ መስፋፋት በመሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል። ከዕድገቱ ጋር ሊሄድ በማይችል የኤሌክትሪክ አቅርቦት፣ የመንገድ ፣ የሕዝብ ማመላለሻ፣ የውኃ አቅርቦትና የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ችግሮች ችግርም ይፈጥራል።
የፕሮፌሰር ሽቶርክ የምርምር ፕሮጀክት ታዲያ ከተለያዩ ዘርፎች የተውጣጡ ተዋናዮችን በማሰባሰብ ለዚህ መሰሉ ችግር የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማምጣት ያለመ ነው።በምርምሩ መፍትሄ ለሰጥ ከታሰበበቸው መካከልም የኤ,ለክትሪክ መስመር ዝርጋታ አንዱ ነው።
«ስለዚህ ለዚያ ስራ በመንገዶች ላይ በትራንስፎርመሮች ላይ በአንድ በኩል የመለኪያ ሥርዓቶችን መትከል እንፈልጋለን። እናም በመጀመሪያ በነባሩ ፍሰት ውስጥ ያለውን የኃይል ፍጆታ እንለካለን። እንዲሁም የኃይል መቆራረጦችን ቁጥር እንቀንሳለን ወይም ወይም መቆጣጠር እንደምንችል ተስፋ እናደርጋለን። ምክንያቱም በተለይ በኢትዮጵያ የሃይል ፍጆታ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ውስጥ 15 በመቶውን ይይዛል። ስለዚህ በጣም ውድ ነው። ምን ያህል ጥቅም ላይ እንደዋለ የበለጠ ማወቅ ከቻልን ግን በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ በቂ ኃይል አለ። ማከፋፈያው ፈጣን በሆነ ፍሰት ማስተላለፍ አይችልም።»ብለዋል።
መረጃን የሚመዘግቡ ቴክኖሎጅዎች
በዚህ ፕሮጄክት ትግበራ የከተማዋን የትራፊክ ፍሰትመረጃን የሚመዘግቡ እንደ ካሜራ እና ሴንሰር ያሉ ቴክኖሎጅዎችን የሚጠቀሙ ሲሆን፤የተሰበሰበው መረጃም ለከተማው አስተዳደር የመሠረተ ልማት እቅድ ግብዓት ሆኖ ሊያገለግል ይችላል።
በመጭው ሚያዚያ መጀመሪያ ወደ ስራ ሊገባ ይችላል የተባለው ይህ ፕሮጀክት፤ ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ፣ከከተማ ልማት እና ከአውሮፓ ህብረት ጋር በትብብር የሚሰራ ሲሆን፤ በሶስት አመታት ውስጥ የሚጠናቀቅ ነው።ሲጠናቀቅም የሚሰበሰበው መረጃ በርካታ ነገሮችን ለማሻሻል ያግዛል ተብሎ ይጠበቃል።
«እኔ እንደማስበው በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት በኤለክትሪክ ማስተላለፊያ ፍርግርጎች ላይ ችግር አለ። ፣ታውቃላችሁ ፣ በሁሉም ቦታ ብዙ የኃይል መቆራረጥ አለ። በእኛ ገጠመኝ ለምሳሌ ሀረር ውስጥ በቂ ኃይል ነበረ። ነገር ግን ፍርግርጉ በትክክል ጥቅም ላይ አልዋለም ነበር። ስለዚህ ይህ መረጃ ሁሉንም ነገር ለማሻሻል ይጠቅማል።» ብለዋል።
ከተለያዩ አጋሮች ጋር በትብብር የሚሰራ ነው
ይህ ፕሮጄክት በዋናነት በአዲስ አበባ ከተማየሚተገበር መሆኑንም ፕሮፈሰር ሽቶርክ ገልፀዋል። ያም ሆኖ በኢትዮጵያ መረጃን በቀላሉ ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ በመረጃ አሰባሰብ ላይ ተግዳሮት ሊገጥም እንደሚችል ፕሮፌሰሩ አመልክተዋል። ይህንን ችግር ለመቋቋም ከተለያዩ አጋሮች ጋር አብሮ መስራቱ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
«በእርግጥ ይህንን ከፈለግን፤ ሴንሰሮችን እና ስርዓታቸውን ለመጫን ከ ኢኢዩ /EEU/ የተገኘው መረጃ ያስፈልገናል። ሁለተኛ ፣ ዩኒቨርሲቲዎች ማለትም ከሥነ-ሕንፃ ትምህርት ክፍል የከተማ ልማት ዘርፍ በአንድ በኩል እንዲሁም በኤሌክትሪካል ምህንድስና እኛ አለን። ስለዚህ እንዲህ አይነት ትብብር ካላ በመጨረሻ፣ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን ምርምርን እንደግፋለን።ከዚያም ምርምሩን እነሱ በራሳቸው ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ተስፋ እናደርጋለን።»ብለዋል በትብብር የመሥራቱን አስፈላጊነት ሲገልፁ።
ለማቀድ እና አስተዳደርን ለማሻሻል ይጠቅማል
ቀደም ሲል በሐረር በኤለክትሪክ ፍርግርግ ስርጭቶች ላይ ተመሳሳይ ፕሮጀክት እንደነበረ የገለፁት ሃላፊው ያንን መረጃ ከአዲስ አበባው ፕሮጄክት ጋር ማስተሳሰር እንደሚፈልጉ ገልፀዋል።የተሰበሰበውን ዳታ በመጠቀም የመሠረተ ልማትን በተሻለ ሁኔታ ለማቀድ እና አስተዳደርን ለማሻሻል እንደሚጠቅም ገልፀዋል።
«መጨረሻ ላይ የኃይል መቆራረጥን መቀነስ እንፈልጋለን። ይህ አንዱ ግብ ሲሆን ሌላው ግብ በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች በየሩብ ዓመቱ ያለውን እድገት ላይ ለከተማው አስተዳደር ተጨማሪ መረጃ እንስጣለን። ስለዚህ በመረጃ ላይ ተመስርተው መወሰን እንዲችሉ ያደርጋል።»በማለት ገልፀዋል።
ለኑሮ ምቹ የሆኑ ከተሞችን ለመፍጠር ያግዛል
ፕሮጀክቱ የኤሌክትሪክ ስርዓት እና የትራፊክ ፍሰት መረጃን ብቻ ሳይሆን የከተሞችን የህዝብ ቁጥር እድገት ጭምር ስለሚሰበስብ መረጃው ለከተማው አስተዳደር ብቻ ሳይሆን ለአውሮፓ ህብረትም ጠቃሚ መሆኑን ገልፀዋል።
እንደ ፕሮፌሰሩ በአጠቃላይ የከተሞች ዋናው ችግር ወደ ከተማ የሚጎርፈውን ህዝብ በተመለከተ የመረጃ እጥረት መኖሩ ነው።ስለሆነም የጀርመን ሳይንቲስቶች በኢትዮጵያ ከሚገኙ የተለያዩ አጋሮች ጋር በመተባበር ለስማርት ከተሞች እየተዘጋጁ ያሉ ኢንተርኔት እና ሴንሰሮችን በመጠቀም የሀይል ፍጆታ እና የትራፊክ ፍሰት መረጃን ይሰበስባሉ።
ይህም ከተለያዩ ዘርፎች እና ከአካባቢያዊ መረጃ ጋር ተዳምሮ የአዲስ አበባ ከተማን ዲጂታል መንትያ/Digital twin/ ለማዳበር መሰረት ይሆናል። ንድፉ በመጨረሻ ብዙ ሰዎች የሚጎርፉባቸውን አካባቢዎች እና ተዛማጅ የመዋዕለ ንዋይ ፍላጎትን ለመለየት እና ለወደፊቱ ለኑሮ ምቹ ከተሞችን ለመንደፍ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል ተብሏል።ልላል የተባለው የጀርመን ፕሮጀክት።
ፀሐይ ጫኔ
ዮሀንስ ገብረእግዚአብሄር