የአዲሱ የጀርመን የፍልሰት ፖሊሲና ተግዳሮቶቹ
ማክሰኞ፣ ግንቦት 26 2017ዘንድሮ በየካቲት የተካሄደው የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ የህዝቡን ትኩረት ከሳቡት ጉዳዮች መካከል የፍልሰተኞች ጉዳይ አንዱ ነበር። በዚህ መነሻነትም አዲሱ የጀርመን የጀርመን ጥምር መንግስት ሲመሰረት ጠንከር ያለ የፍልሰት ፖሊሲ እንደሚከተል አሳውቆ ነበር። በዚሁ መሠረትም በብሔራዊ ድንበሮች ላይ ቁጥጥሩን አጥብቋል ፤ ተገን ጠያቂዎችን ጨምሮ ሕገ ወጥ የሚላቸውን ስደተኞች ከጀርመን ድንበሮች ወደ መጡበት እየመለሰ ነው። በስራም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ከኅብረተሰቡ ጋር ፈጥነው የተዋሀዱ ስደተኞች ከሦስት ዓመት የጀርመን ቆይታ በኋላ የጀርመን ዜግነት እንዲያገኙ የፈቀደውንና ባለፈው መንግሥት ጸድቆ የነበረውን ሕግ በማንሳት የውጭ ዜጎች የጀርመን ዜጋ መሆን የሚችሉት ከዚያ በፊት እንደነበረው ከአምስት ዓመት በኋላ እንዲሆን ተስማምቷል። የስደተኞች ቤተሰብ አባላትን መልሶ ማገኛትንም ለማገድ አቅዷል። እነዚህን ማሻሻያዎች ያካተተውን አዲሱን የጀርመን የፍልሰት ሕግ የጀርመን ካቢኔ ባለፈው ሳምንት አጽድቋል።
የጀርመን መራኄ መንግስት ፍሪድሪሽ ሜርስ ፣ፖሊስ ሕገ ወጥ የሚባሉፍልሰተኞችን ከጀርመን ድንበር መመለስ እንደሚችል የተናገሩት ስልጣን በያዙ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነበር። ፖሊስ ፍልሰተኞቹ ተገን ቢጠይቁም እንኳን ከጀርመን ድንበር ላይ ወደመጡበት እንዲመልሱ ነው ያዘዙት። ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ከስደተኞች ጠበቆች እንዲሁም ከአንዳንድ የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራትም ጭምር ጠንካራ ተቃውሞ የገጠመው ይህ የመንግስት እርምጃ በዚህ ሳምንት ደግሞ በአንድ የጀርመን ፍርድ ቤት ሕገ ወጥ የሚል ውሳኔ ተላልፎበታል። ትናንት ያስቻለው የበርሊን ስድስተኛ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ፖሊስ በቅርቡ ጀርመን ድንበር ላይ ተገን የጠየቁ ስደተኞችን ወደ መጡበት መመለሱን ሕገ ወጥ ሲል ውሳኔ አሳልፏል። ፍርድቤቱ እርምጃውን አስፈላጊ የሆኑትን ሕጋዊ ደረጃዎች ወደ ጎን የተወና ተገን የማግኘት መብትንም የጣሰ ብሎታል። ፍርድ ቤቱ «በጀርመን የድንበር ኬላ ላይ ሆነው ተገን እንዲሰጣቸው እንደሚፈልጉ የሚገልጹ ሰዎች ጉዳይ በደብሊን ስምምነት መሠረት ፣ የትኛው ሀገር ጥያቄአቸውን ማየት እንዳለበት ሳይታወቅ መመለስ ላይኖርባቸው ይችላል።»ም ብሏል።
ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያሳለፈው ከዛሬ 3 ሳምንት በፊት በጎርጎሮሳዊው ግንቦት 9 ከፖላንድ በበባር ተጉዘው ጀርመን እንደደረሱ፣ ጀርመን ተገን እንዲሰጣቸው ማመልከት እንደሚፈልጉ የተናገሩ ሁለት ወንዶችና አንዲት ሴት ሶማሌያውያንን የጀርመን ፖሊስ በዚያው እለትወደ ፖላንድ እንዲመለሱ በማድረጉ ነው። ፖሊስ ይህን ለምን እንዳደረገ ሲጠየቅ ጀርመን የመጡት ደኅንነቱ ከተጠበቀ ሶስተኛ ሀገር ነው ሲል ሰዎቹን መመለሱ ትክክለኛ መሆኑን አሳውቋል። ሆኖም ፍርድ ቤቱ ተገን ለመጠየቅ መጣን ያሉ ሰዎች ጀርመን መግባት አለብን ብለው መጠየቅ እንደማይፈቀድላቸው ጉዳያቸው ግን በደብሊን የተገን አሰጣጥ ሂደቶች በድንበሩ ላይ ወይም በድንበሩ አቅራቢያ ሊታይ ይገባ ነበር ሲል በይኗል።
አዲሱን የጀርመን የፍልሰት ፖሊሲ የመተግበር ሃላፊነቱ የየወደቀባቸው የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ዶብሪንድት ትናንት ማምሻውን በሰጡት መግለጫ ለዚህ ሕጋዊ ማረጋገጫ አለን ብለዋል። ዶብሪንድት በመግለጫቸውው ስደተኞቹ ከግንቦት 9 በፊትም ጀርመን ድንበር ላይ ሁለት ጊዜ መምጣታቸውን አስረድተዋል። « በአንድ ጉዳይ ላይ ብቻ የተላለፈው ይህ ውሳኔ በጎርጎሮሳዊው ግንቦት 2 ቀን ጀርመንን ከፖላንድ ጋር የሚያዋስነውን ድንበር አቋርጠው ከፖላንድ ወደ ጀርመን ለመግባት የሞከሩ ነገርግን እንዲመለሱ የተደረጉ 3 የሶማሊያ ስደተኞችን ይመለከታል።በዚያን ጊዜ የተገን ጥያቄ ማመልከቻ አላስገቡም።እነዚሁ ሰዎች ግንቦት 3 እንደገና እዚያው ድንበር ላይ መጥተው ያኔም ተገን እንዲሰጣቸው አላመለከቱም። ግንቦት 9 እንደገና መጥተው ተገን ጠየቁ። በወቅቱ በተለያዩ የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት በኩል ካለፉ በኋላ ነበር ጀርመን ተገን እንዲሰጣቸው የጠየቁት። »
ሰደተኞቹ ደጋግመውጀርመን ለመግባት መሞከራቸውን ያስረዱት ዶብሪንድት መንግስታቸው መሰል ተገን ጠያቂዎችን መመለሱን እንደማያቆምም ተናግረዋል።
«የበርሊን አስተዳደር ፍርድ ቤት ዛሬ ያሳለፈው ውሳኔ ጉዳዩ በደብሊን ስምምነት መሠረት መጣራት ነበረበት ይላል። ያም ማለት ስደተኞቹ ድንበር ተሻግረው ይገባሉ። ጀርመን የትኛው ሀገር ፣የተገን አሰጣጥ ሂደቱን ሃላፊነት መውሰድ እንዳለበት ማጣራት አለባት። በሌላ አባባል በዚህ ጉዳይ ላይ የትኛው የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገር ሃላፊነቱን እንደሚወስድ እኛ ማጣራት እንዳለብን ውሳኔው ይገልጻል። ፍርድ ቤቱ በዚህ ውሳኔ ላይ ለዕርምጃችን የሚሰጠው ምክንያት የበለጠ ግልጽ መሆን ነበረበት ብሏል። እኛም ይህንን ፍላጎት እያከበርን እና የበለጠ ዝርዝር ምክንያቶችን እያቀረብን ነው ማለት ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ስደተኞችን በመመለሱ ሂደት እንጸናለን። በዚህ የግለሰቦች ጉዳይ ላይ ውሳኔ ቢሰጥም ፣ ሕጋዊው መሰረቶች ስለማናይ በዚህ መንገድ እንቀጥላለን።»
የሶስቱን ስደተኞች ጉዳይ የተመለከተው የበርሊኑ ፍርድ ቤት የስደተኞቹ ጉዳይ የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት ተግባራዊ ማድረግ ባለባቸው በደብሊን ስምምነት መሠረት አልታየም ሲል ነው ሕገ ወጥ ያለው።
በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን ጀርመን የሚኖሩትን የሕግ ባለሞያና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶክተር ለማ ይፍራሸዋን የጠየቅናቸው ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ በደብሊኑ ስምምነት መሠረት ሦስቱ ስደተኞች ከጀርመን ድንበር ላይ ወዲያውኑ እንዲመለሱ መደረግ አልነበረበትምሲሉ ተናግረዋል።
የጀርመን መራኄ መንግስት ፍሪድሪሽ ሜርስ መንግስታቸው እርምጃውን የሚወስደው የህዝብ ደኅንነት ለመጠበቅ አስፈላጊ በመሆኑ ነው በማለት የበርሊኑ ፍርድ ቤት በሦስቱ ስደተኞች ጉዳይ ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከላክለዋል። ሜርስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ መንግስት የህዝቡን ደኅንነት ለመጠበቅ እና በሀገሪቱም ስርዓት ለማስከበር እንዲሁም በከተሞች የሚፈጠሩ መጨናነቆችን ለማስቀረት እርምጃውን መውሰዱን ይቀጥላል ብለዋል። ከዚሁ ጋር በጀርመን ጎረቤት ሀገራት ላይ ውጥረት የፈጠረውን ፖሊሲውን በአውሮፓ ኅብረት በሚሰራበት የሕግ ማዕቀፍ መሠረት እንደሚተገበርም ተናግረዋል። ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ሜርስ ዛሬ ያቀረቡት መከላከያ ተቀባይነት ሊኖረው እንደሚችል ሆኖም በዘላቂ መፍትሄነት ሊሰራ እንደማይችል አስረድተዋል።
በጀርመን ሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ መሠረት ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ 1676 ፍልሰተኞች ጀርመን መግባት ተከልከለዋል። ከመካከላቸው 32ቱ ጀርመን ጥገኝነት መጠየቅ የሚፈልጉ ነበሩ። የጀርመን ካቢኔ በቅርቡ ያጸደቀውን አዲሱን የጀርመን የፍልሰት ሕግ ማሻሻያ የሀገሪቱ የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በመጪው ሐምሌ ወር ተነጋግሮ ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ