የአውሮጳ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተቃራኒ አቋም
ማክሰኞ፣ ሰኔ 17 2017
የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ትናንት ብራስልስ ባደረጉት ጉባኤ ሩሲያ በዩክሬን ሕዝብ ላይ ትፈፅመዋለች ያሉትን ጥቃት በድጋሚ አዉግዘዉ በሩሲያ ላይ ለ18ኛ ጊዜ ማዕቀብ ለመጣል ወስነዋል።ይሁንና እስራኤል በጋዛ ሕዝብ ላይ የምትፈፅመዉን ግድያ፣የምግብና የመድሐኒት እቀባን ከተሰብሳቢዎቹ አንዳዶቹ ቢቃወሙትም በጋራ ለማዉገዝ አልቃጡም።ኢራንና እስራኤል የገጠሙትን ዉጊያ እንዲያቆሙም ሚንስትሮቹ ጠይቀዉ ነበር።
ውጥረትን የማርገብና ጦርነትን የማስወገድ ጥሪ
የስብሰባው መሪና የህብረቱ የውጭ ጉዳይ ሀላፊ ወይዘሮ ካያ ካላስ በጋዜጣዊ መግለጫቸው አዲስ የተጀመረው ያእስራኤልና ኢራን ጦርነት ከሁሉም በላይ አሳስቢ መሆኑን አውስተው፤ ኢራን ለአመታት ስጋት ሆና እንደቆየችና በምንም አይነት የኒውክለር መሳሪያ እንዲኖራት ሊፈቀድ እንደማይገባ ህብረቱ ሲገልጽና ሲያሳስብ እንደቆየ አስረድተዋል። ያም ሆኖ ግን ወታደራዊ እርምጃ ችግሮችን ከሚያባብስና ከሚያስፋ በስትቀር መፍትሄ ሊያመጣ የማይችል መሆኑን በማመን ተፋላሚዎቹ ወገኖች ውጥረቱን እንዲያበርዱና ጦርነትን እንዲያስቀሩ ሚኒስትሮቹ ጥሪ ያቀረቡ መሆኑን አስታውቀዋል፤ “ አሁን መደረግ ያለብት ሁኔታውን ማርገብና ውጥረቱን መቀንስ ነው። ዛሬ ሁሉም ሚኒስትሮች ሁሉም ወገኖች ጦርነቱን እንያቆሙና ወደ ውይይት ጠረንጴዛ በመምጣት ጦርነቱ እንዳይሰፋ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል” በማለት ጦርነት ለማንንም የማይጠቅም መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኢራን-እስራኤል ጦርነትና የአሜሪካ ጣልቃገብነት የፈጠረው ስጋት
ያውሮፓ ህብረትና ብዙዎቹ አባላቱ ኢራንና ኢስራኤል ቅድሚያ ለዲፕሎማሲ በመስጠት ችግሮችን በውይይት እንዲፈቱ ሲያሳስቡ ቢሰሙም፤ የአሚሪካንን የቦምብ ደብደባ ግን በግልጽ ሲያወግዙ አልተሰሙም። ሆኖም ትናንት እኩለ ሌሊት ላይ ፕረዝዳንት ትራምፕ እራሳቸው ከዛሬ ማለዳ ጀምሮ ኢራንና ኢስራኤል የተኩስ ማቆም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አሳታውቀዋል። የስምምነቱን ተግባራዊነት፤ቀጣይነትና ዘላቂነት ሁሉም በአንክሮ እየተከታትለው ቢሆንም ዜናው ግን ለብዙዎች እፎይታን የፈጠረ ሁኗል።
በጋዛ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች
ሚኒስትሮቹ እስራኤል በጋዛ በክፍተችው ጦርነትና እየፈጸመችው ባለው የሰባዊ መብት ጥሰት በተለይም የሰባዊ እርዳታ እንዳይገባ በመክልከል ህዝብን በረሀብ የመቅጣት እርምጃን በማውገዝ ሊወሰዱ በሚገባቸው እርምጃዎች ላይ መወያየታቸው ተገልጿል። ወይዘሮ ካያ በዚህ አጀንዳ ህብረቱ ቅድሚያ የሚስጣቸውን ሲገልጹ “ ወደተሟላ የተኩስ ማቆም ስምምነት መመለስ፣ የተሟላ የሰባዊ እርዳታን ተድራሽነት ማረጋገጥና የሁሉም ታጋቾች መለቀቅ መሆናቸውን ገልጸው፤ የአውርፓ ህብረትና ኢስራኤል የጋራ ስምምነት መርሆቻቸው የተጣሱ መሆን አለመሆናቸውን የሚገልጽ ሪፖርት ለካውንስሉ ያቀረቡ መሆኑን አስታውቀዋል። የስምምነቱ አንቀጽ ሁለት የሰባዊ መብትቶችን ማክበርንና ማስከበርን በዋናነት የሚጠይቅ ሲሆን፤ ይህ ግን በከፊልም ይሁን በሙሉ ከተጣሰ የማዕቀብና ከአባልነት እስክመታገድ የሚያደርስ እርምጃ ሊያስወስድ እንደሚችል ይገልጻል። ሆኖም ግን ውሳኔው የአባል አገራቱን ሙሉ ስምምነት የሚጠይቅ በመሆኑንና በዚህ አጀንዳ ላይ የህብረቱ አባል አገሮች የተክፋፈሉ በመሆናቸው በእራኤል ላይ ጥብቅ እርምጃ ይወሰዳል ተብሎ አይጠበቅም ነው የሚባለው ። በዚህም የአውሮፓ ህብረት በዩክሬንና ሌሎችም አካባቢዎች የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችንና የህግ መተላለፎችን የሚቃወመውንን ያህል እስራኤል በጋዛ ላይ ያደርሰችውን ሰባዊ ቀውስና ውድመት ችላ ብሏል ወይም ተገቢውን ትኩረት አላደረገም በመባል ይወቀሳል።
የዩክሬንና መካክለኛው ምስራቅ አጀንዳነት ቀጣይነት
የሚኒስትሮቹ ስብሰባ ሩሲያ በዩክሬን ላይ እየፈጸመች ያለዉን ጥቃት ዛሬም አውግዞ፤ በሩሲያ ላይ ለአስራ ስምንተኛ ግዜ ማዕቀብ ለመጣል መስማማቱ ተገልጿል።፡ የመካክለኛው ምስራቅና የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት አጀንዳዎች፤ ዛሬና ነገ በነዘርላንድስ ዘሄግ እየተካሄደ ባለው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ስብስብና በብራስልስ ደግሞ ነገና ከነገ ወዲያ በሚካሄደው የአውሮፓ ህብረት የመሪዎች ጉባኤም የመነጋገሪያ ኣጀንዳ ሆኖ እንደሚቀጥል ታውቋል።
ገበያው ንጉሴ