የአረብ ሊግ አባል ሐገራት የሶሪያን አባልነት በይፋ አፀደቁ
ዓርብ፣ ግንቦት 11 2015የአረብ ሊግ አባል ሐገራት መሪዎች ላለፉት 12 ዓመታት ከሊጉ የተገለለችዉን የሶሪያን ዳግም አባልነት ዛሬ በይፋ አፀደቁ።እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ2011 የተቀሰቀሰዉ የሶሪያ ሕዝባዊ አመፅ ባጭር ጊዜ ወደ ርስበርስ ጦርነት ከተቀየረ በኋላ የአረብ ሊግ ሶሪያን ከአባልነት አግዷት ነበር።ከቅርብ ዓመታት ወዲሕ በተለይም ሳዑዲ ረቢያና ኢራን ግንኙነታቸዉን ለማሻሻል ከተስማሙ ካለፈዉ መጋቢት ወዲሕ የደማስቆና የሌሎቹ የአረብ መንግስታት ግንኙነት ተሻሽሎ ሶሪያ ዳግም የሊጉ አባል ሆናለች።ዛሬ ጂዳ ሳዑዲ አረቢያ ዉስጥ በተጀመረዉ በአረብ ሊግ 32ኛ የመሪዎችc መደበኛ ጉባኤ ላይ የሶሪያዉ ፕሬዝደንት በሽር አል አሰድ ተገኝተዋል።አሰድ ለጉባኤዉ ንግግር ከማድረጋቸዉ በፊት ከቱኒዚያዉ ፕሬዝደንት ካይስ ሰዒድ ጋር ባደረጉት ዉይይት የዓረብ ሊግ ከዲፕሎማሲያዊ ማሕበርነትም የበለጠ ነዉ ብለዋል።
«ከአረብ ሊግ ልብ ዉስጥ ነን።በጣም ጠቃሚ ማሕበር ነዉ።ከዲፕሎማሲ የበለጠ፣ኃላፊነትን ከተቀበሉ ሰዎች፣ ከመሪዎች ግንኙነትም የበለጠ ጥልቅና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላይ የተመሰረተ ነዉ።ይሕን ግንኙነት በየመስኩ ማለትም በምጣኔ ሐብት፣በባሕል፣በእዉቀትና በሌሎችም መስኮች ይበልጥ ማዳበር አለብን።በአረብ ሊግ ዉስጥ በጋራ እንሰራረን ስንልም ይሕንን የጋራ ግንዛቤ ማስረፅ አለብን ማለታችን ነዉ።»
ሶሪያ፣ ባሁኑ ወቅት የፍልስጤም ራስ-ገዝ አስተዳደርን፣ ሶማሊያና ጅቡቲን የመሳሰሉ የአፍሪቃ ሐገራትን ጨምሮ 22 ሐገራትን የሚያስተናብረዉ የአረብ ሊግ መስራች ሐገር ናት።ዛሬ በተጀመረዉ ጉባኤ ላይ የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮልድሚየር ዜሌንስኪ ንግግር ለማድረግ ጂዳ-ሳዑዲ አረቢያ ገብተዋል።ዜሌንስኪ ጦራቸዉ ከሩሲያ ጠላቱ ጋር ለገጠመዉ ጦርነት ተጨማሪ ድጋፍ ለማሰባሰብ የተለያዩ ሐገራትን እየጎበኙ ነዉ።የዩክሬን መሪ በአረብ ሊግ ጉባኤ ላይ ንግግር ሲያደርግ ግን ዜሌንስኪ የመጀመሪያዉ ይሆናሉ።
ነጋሽ መሐመድ
አዜብ ታደሰ