የአሜሪካ የተራድዖ ድርጅት ድጋፍ መቆም በሲቪል ማሕበራት ላይ ያሳረፈው ጫና
ሰኞ፣ የካቲት 24 2017የአሜሪካ የተራድዖ ድርጅት ድጋፍ መቆም በሲቪል ማሕበራት ላይ ያሳረፈው ጫና
የአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት (UDAID) ድጋፍ በድንገት መቋረጥ በአብዛኞቹ ሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ሥራ ላይ ብርቱ ጫና ማድረሱ ተነገረ። የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት እንዳለው በጤና፣ በሰላም እና በዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ሲሰሩ የነበሩ የተራድዖ ድርጅቱ ወኪሎች የፕሮጀክት ስረዛ ስለተደረገባቸው በሁሉም ክልሎች የሚሠሩ የሲቪል ማህበራት የዚህ ችግር ቀጥተኛ ተጎጂ ሆነዋል። በሲቪክ ድርጅቶች አማካኝነት ከሚከናወኑ የትምህርት፣ የጤና፣ የግብርና ተግባራት አብዛኛዎቹ ከአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት በሚገኝ የሀብት ድጋፍ የሚሠሩ መሆኑን ያስታወቀው ምክር ቤቱ፣ ዴሞክራሲ ላይ የሚሰሩ ሲቪክ ድርጅቶች በቀጣይ ምርጫ ላይ የሚኖራቸው ሚና እንዳይዳከም ከወዲሁ መፍትሔዎችን ለማበጀት ጥረት እንደሚያደርግ አስታውቋል።የአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት እርዳታ መቋረጥ በአማራ ክልል የሚፈጥረው ጫና
አብዛኞቹ ሲቪክ ድርጅቶች ሥራቸው ተደናቅፏል
ኢትዮጵያ ውስጥ በልዩ ልዩ ዘፍርፎች ለመሥራት የተመዘገቡ ከ 4000 በላይ ሲቪክ ድርጅቶችን፣ ጥምረቶችን እና ማህበራትን የሚያስተባብረውና የሚወክለው የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት እና ወኪሎቹ ለሦስት ወራት የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ መታገዱን ተከትሎ አብዛኛውን የገንዘብ ድጋፍ ከዚሁ ተቋም ያገኙ የነበሩ ሲቪክ ድርጅቶች ላይ ብርቱ ጫና መፍጠሩን ለዶቼ ቬለ አስታውቋል። የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ አህመድ ሁሴን እንዳሉት በሰብአዊ መብት፣ በሰላም፣ በአስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ፣ በጤና፣ በግብርና እና በልማት ሥራዎች ላይ ይሰሩ የነበሩ ሲቪክ ድርጅቶች ድጋፉ በመቆሙ ምክንያት አብዛኞቹ ሥርቸውን አቁመዋል።
"በተለይ በ ኤች አይ ቪ፣ በሳንባ ነቀርሳ - ቲቪ፣ በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ላይ ይሠሩ የነበሩ ድርጅቶች በሙሉ ከ 90 በመቶ በላይ ተሰርዘዋል። ባለን ክትትልም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በርካታ ክልሎች ላይ መጠነ ሰፊ የሆነ ፕሮጀክት ይዘው አንዳንዶቹ 10 ሚሊየን ዶላር፣ ሰባትም፣ አምስትም የሦስት አራት ዓመት ተከታታይ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችል ውለታ ገብተው እየሠሩ ነው የነበረው።" ለእነዚህ ተቋማት ሕጋዊ እውቅና የሚሰጠው የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ጥር 27 ቀን 2017 ዓ. ም ባወጣው አስቸኳይ መግለጫ የድጋፉን መቋረጥ ተከትሎ "ያለ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ግልፅ ፍቃድ ንብረት የማስተላለፍ፣ የማስወገድ ወይም የመሸጥ ወይም ከመደበኛ ሥራዎች ጋር ተያያዥ ከሆኑ ጉዳዮች ውጭ በማናቸውም መልኩ ሐብትና ገንዘብን ለሦስተኛ ወገን ማስተላለፍ"ን በጥብቅ ከልክሏል። የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አህመድ ሁሴን በተለይ የግጭት እና ጦርነት ሰለባዎችን ለመደገፍ ይደረግ የነበረው ሥራ ላይ የደረሰው ጫና ምንም እንኳን ገና እየተጠና ቢሆንም ጉዳቱ ከፍተኛ እንደሚሆን ይጠበቃል ብለዋል። "በጦርነት ወይም ግጭት ሰለባ የሆኑ አካባቢዎች ደግሞ ምን ያህል ሊጎዱ እንደሚችሉ ማየት ይቻላል፤ እና ጉዳቱ ከባድ ነው።"የUSAID የ 6 ዓመታት ስራዎች እና ዉጤታቸዉ
ሲቪክ ድርጅቶች ለቀጣዩ ምርጫ የሚያበረክቱት በጎ ሥራ እንዳይዳከም ያሰጋል
በውጭ ድጋፍ እና እርዳታ ጥገኛ የሆነው የሲቪክ ማህበረሰብ ምህዳር ዋናው ደጋፊ አሜሪካ ድጋፉን ሲያቋርጥ ኢትዮጵያ በቀጣዩ ዓመት በምታደርገው ምርጫ ሊኖራቸው የሚችለውን ሚኖ እንዳይዳከም ያሰጋል። በሌላ በኩል መሰል የሰብአዊ መብት እና የዴሞክራሲ ዕድገት ላይ ደጋፊ ተግባራትን የሚያከናውኑ የሲቪክ ድትጅቶች እየታገዱ ነው። ባለፈው ሳምንት ከዶቼ ቬለ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ አዴሎ ሲቪክ ተቋማቱ ለምርጫው የሚኖራቸው ሚና ሊጎላ እንደሚገባ አሳስበው ነበር። "ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከዚህ በኋላ በስፋት መንቀሳቀስ አለባቸው። የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ይህን ሲቪክ ምህዳሩን ማጥበብ የለባቸውም።" አቶ አህመድ ሁሴን አሜሪካ ሙሉ በሙሉ ድጋፍ አቋርጣ ትቀራለች የሚል ግምት እንደሌላቸው ገልፀዋል። ሆኖም ግን ድጋፉ እስከቀነሰ ድረስ ሲቪክ ድርጅቶች ለቀጣይ ምርጫ የሚኖራቸው ሚና መቀዛቀዙ አይቀርም ብለዋል። ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጡ የገለፁት ኃላፉው ምርጫ ላይ የአውሮፓ ሕብረት፣ ከኤምባሲዎች እና ሌሎች የተራድዖ ድርጅቶች ድጋፍ እምደሚያደርጉና ሥራውን ለማጠናከር ጊዜ መኖሩን ጠቁመዋል።
"የአውሮፓ ሀገራትም፣ ሌሎችም ተራድዖ ድርጅቶች ይህንን ክፍተት [የአሜሪካው ድጋፍ መቋረጥን] አይተው እንዲሞሉ በተለያዩ በምናደርጋቸው ስብሰባዎች፣ በሚጠይቋቸው መጠይቆች ለመመለስ እየተሞከረ ነው። ስለዚህ ምርጫንም በሚመለከት ታሳቢ እንዲያደርጉ ወይም በሚያወጧቸው ፕሮጀክቶች፣ ውድድሮች ውስጥ ታሳቢ እንዲያደርጓቸው ጊዜውም ፋታ የሚሰጥ ነው።"
ዘላቂ መፍትሔዎችን ለመትለም ውይይቶች እየተደረጉ ነው
የአሜሪካው የእርዳታ ድርጅት ድጋፍ በማቆሙ ምን ያህል ሲቪክ ድርጅት ሥራ አቆሙ? ምን ያህል ሠራተኞች የችግሩ ሰለባ ሆኑ? ተፅዕኖው ምንድን ነው? እንዴት ሥራችንን እንቀጥል በሚለው ላይ ውይይይት መደረጉንና ጥናቱ ሲጠናቀቅ መረጃውን እንደሚያጋሩን የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አህመድ ሁሴን ተናግረዋል። የተከሰተውን ድንገተኛ የድጋፍ መቋረጥ ግን በሌሎች ሀገራት ድጋፍ የሚመራ ሕይወት እስከመቼ ይቀጥላል? የሚለውን ለመመለስ በቂ ምክንያት የሆነና በራስ የመቆም አቋም ለመያዝ የመጣ "የማንቂያ ደውል ነው" ብለውታል።
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
ታምራት ዲንሳ